ኤርምያስ 3:1-18
ኤርምያስ 3:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ እርስዋም ከእርሱ ተለይታ ሌላ ወንድ ካገባች በኋላ እንደገና መልሶ ሊያገባት ይችላልን? ይህ ቢደረግማ ፈጽሞ ምድርን የሚያረክስ ይሆናል። እስራኤል ሆይ! አንቺ ግን ብዙ ጣዖቶችን ወደሽ ነበር፤ አሁን ደግሞ እንደገና ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽ። እስቲ ቀና ብለሽ ወደ ኰረብቶች ራስ ተመልከቺ፤ ከቶ አንቺ ለጣዖቶች ያልሰገድሽበት ስፍራ ይገኛልን? ቀማኛ፥ ሸማቂ፥ ዘላን በበረሓ ተቀምጦ ሊዘርፈው የሚፈልገውን መንገደኛ እንደሚጠባበቅ፥ አንቺም ፍቅረኛዋን ለማጥመድ በየመንገዱ ዳር እንደምትጠባበቅ ሴት ሆነሽ በአምልኮ ዝሙትሽ ኃጢአት ምድርን አረከስሽ። የበልጉም ሆነ የክረምት ዝናብ ሊቀር የቻለው በዚህ ምክንያት ነው፤ አንቺ ዐይነ ዐፋርነትን አስወግደሽ እንደ አመንዝራ ሴት ኀፍረተቢስ ሆነሻል። “አሁን ‘አባቴ፥ የልጅነት ጓደኛዬ’ ብለሽ አልጠራሽኝምን? አንቺ፦ ‘እርሱ ዘወትር ይቈጣልን? ኀይለኛ ቊጣውስ ዘላቂ ነውን?’ ብለሽ ተናግረሻል፤ ነገር ግን የምትችዪውን ክፉ ሥራ ትሠሪያለሽ።” ኢዮስያስ በነገሠበት ዘመን እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “እምነት አጒዳይ የሆነችው እስራኤል ምን እንዳደረገች አይተሃልን? እርስዋ ከእኔ ተለይታ በየከፍተኛው ተራራና በየለመለመው ዛፍ ሥር ጣዖትን በማምለክ ርኲሰትን ፈጽማለች። ይህን ሁሉ ከፈጸመች በኋላ እንደገና ወደ እኔ የምትመለስ መስሎኝ ነበር፤ እርስዋ ግን አልተመለሰችም፤ እምነት የማይጣልባት የእርስዋ እኅት ይሁዳም ይህን ሁሉ አይታለች። እስራኤል እኔን ማምለክዋን ትታ የጣዖት አምልኮን ተከተለች፤ ይህንንም ስታደርግ የተውኳት መሆኔን ይሁዳ ተመልክታለች፤ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት ይሁዳ ፍርሀት አላደረባትም፤ እርስዋም በበኩልዋ ጣዖት አምላኪ ሆናለች። ከቶም አላፈረችም፤ ይልቁንም ድንጋይና ዛፍ በማምለክ ምድሪቱን አረከሰች። ይህን ሁሉ ከፈጸመች በኋላ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት የሆነችው ይሁዳ፥ እንደገና ወደ እኔ ለመመለስ የምትሞክር መስላ የታየችው ከልብዋ ሳይሆን ከአንገት በላይ ነበር፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ምንም እንኳ እስራኤል ከእርሱ ብትለይ፥ እምነት ከማይጣልባት ከይሁዳ የምትሻልበት መንገድ መኖሩን እግዚአብሔር ነገረኝ። ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ ሰሜን ሄጄ ለእስራኤል እንድነግራት ያዘዘኝ ይህ ነው፤ “እምነት የማይጣልብሽ እስራኤል ሆይ! ወደ እኔ ተመለሺ፤ እኔ ምሕረቴ የበዛ ስለ ሆነ አልቈጣም፤ በአንቺ ላይ የምቈጣውም ለዘለዓለም አይደለም። አንቺ በደለኛ መሆንሽንና በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅሽን ብቻ እመኚ፤ ከባዕዳን አማልክት ጋር በየለምለሙ ዛፍ ሥር የጣዖት አምልኮ ርኲሰት መፈጸምሽንና ለሕጌም ያለመታዘዝሽን ተናዘዢ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “እናንተ እምነት የማይጣልባችሁ ሕዝብ ሆይ! የእኔ ስለ ሆናችሁ ተመለሱ፤ ከእናንተ መካከል ከየአንዳንዱ ከተማ አንዳንድ፥ ከእያንዳንዱም ቤተሰብ ሁለት ሁለት መርጬ ወደ ጽዮን ተራራ አመጣችኋለሁ። ለእኔ የሚታዘዙ ጠባቂዎችን እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በጥበብና በማስተዋል ይመሩአችኋል። በዚያችም ምድር ቊጥራችሁ በሚበዛበት ጊዜ ስለ ኪዳኔ ታቦት የሚናገሩ ሰዎች አይኖሩም፤ ከዚያን በኋላ ስለ እርሱ አያስቡም፤ ሊያስታውሱትም አይችሉም፤ አስፈላጊነቱ ስለማይታያቸው እንደገና ሌላ ለመሥራት አይሞክሩም። በዚያን ዘመን ኢየሩሳሌም ራስዋ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ተብላ ትጠራለች፤ ሕዝብም ሁሉ እኔን ለማምለክ በዚያ ይሰበሰባሉ። ከዚያን በኋላ እልኸኛና የክፉ ሐሳብ ምንጭ የሆነውን ልባቸውን አይከተሉም። እስራኤልና ይሁዳ አንድ ይሆናሉ፤ ሁለቱም በአንድነት በስተሰሜን ካለው አገር ከምርኮ ይመለሳሉ፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የዘለዓለም ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ተመልሰው ይገባሉ።”
ኤርምያስ 3:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? አንቺም ከብዙ እረኞች ጋር አመንዝረሻል፤ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። ዐይኖችሽን አቅንተሽ አንሺ፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ እንዳለም ተመልከች። እንደ ምድረ በዳ ቍራዎች በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ በዝሙትሽና በክፋትሽ ምድሪቱን አርክሰሻታልና። ለጕስቍልናሽ ከብዙዎች እረኞች ጋር ኖርሽ የአመንዝራም ሴት ፊት ነበረብሽ፥ በሁሉም ዘንድ ያለ ኀፍረት ሄድሽ። ስለዚህ የመከርና የበልግ ዝናም ተከለከለ። አሁንም፦ እንደ ጌታሽና እንደ አባትሽ፥ እንደ ልጅነት ባልሽም አልጠራሽኝምን? ቍጣው ለዘለዓለም ይኖራልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን? እነሆ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፤ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገር አደረግሽ።” እግዚአብሔርም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፥ “ከዳተኛዪቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ፥ ወደ ለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች፤ በዚያም አመነዘረች። ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ፦ ወደ እኔ ተመለሽ አልኋት፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅቷ ይሁዳም አየች። ከዳተኛዪቱም እስራኤል እንዳመነዘረች አየሁ፤ የፍችዋንም ደብዳቤ በእጅዋ ሰጥቼ ሰደድኋት፤ ጎስቋላ እኅቷ ይሁዳ ግን በዚያ አልፈራችም፤ እርስዋም ደግሞ ሄዳ አመነዘረች። ዝሙቷም ከንቱ ሆነ፤ እርስዋም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። በዚህም ሁሉ ከዳተኛዪቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ከጎስቋላዋ ይሁዳ ይልቅ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ራስዋን አጸደቀች። ሂድና ይህን ቃል ወደ ሰሜን ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ሆይ! ወደ እኔ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ መሓሪ ነኝና፥ ለዘለዓለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላጸናም፥” ይላል እግዚአብሔር። በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኀጢአትሽን ብቻ ዕወቂ ይላል እግዚአብሔር። ከዳተኞች ልጆች ሆይ! እኔ እገዛችኋለሁና ተመለሱ፤ ይላል እግዚአብሔር። አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፤ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤ እንደ ልቤም የሚሆኑ ጠባቂዎችን እሰጣችኋለሁ፤ በዕውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል። “በበዛችሁ ጊዜ፥ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥” ይላል እግዚአብሔር፤ በዚያ ዘመን፦ የእስራኤል ቅዱስ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት እነኋት አይሉም፤ በልባቸውም አያስቧትም፤ በአፋቸውም አይጠሯትም፤ ከእንግዲህ ወዲህም አይሿትም። ያንጊዜም ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፤ አሕዛብም ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።
ኤርምያስ 3:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ሰው ሚስቱን ቢፈታ፣ እርሷም ሄዳ ሌላ ሰው ብታገባ፣ ወደ እርሷ ይመለሳልን? ምድሪቱስ ፈጽማ አትረክስምን? አንቺ ግን ከብዙ ወዳጆችሽ ጋራ አመንዝረሻል፤ ታዲያ አሁን ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽን?” ይላል እግዚአብሔር። “እስኪ ቀና ብለሽ ጭር ያሉትን ኰረብቶች ተመልከቺ፣ በርኩሰት ያልተጋደምሽበት ቦታ ይገኛልን? በበረሓ እንደ ተቀመጠ ዘላን ዐረብ፣ በየመንገዱ ዳር ተቀምጠሽ ወዳጆችሽን ጠበቅሽ። በዝሙትሽና በክፋትሽ፣ ምድሪቱን አረከስሽ። ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፤ ኋለኛው ዝናብም ጠፋ። አንቺ ግን አሁንም የጋለሞታ ገጽታ አለብሽ፤ ዐይንሽን በዕፍረት አልሰብር ብለሻል። አሁንም ወደ እኔ ተጣርተሽ፣ ‘አባቴ፣ የልጅነት ወዳጄ፣ ሁልጊዜ ትቈጣለህን? ቍጣህስ ለዘላለም ነውን?’ አላልሽኝም? የምትናገሪው እንዲህ ነው፤ ይሁን እንጂ የቻልሽውን ክፋት ሁሉ ታደርጊያለሽ።” እግዚአብሔር በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፤ “ከዳተኛዪቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ከፍ ወዳለው ኰረብታ ሁሉ ወጥታ፣ ወደ ለመለመው ዛፍ ሥር ሁሉ ሄዳ በዚያ አመነዘረች። ይህን ሁሉ ካደረገች በኋላ፣ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፤ ሆኖም አልተመለሰችም፤ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አየች። ለከዳተኛዪቱ እስራኤል ስለ ምንዝርናዋ ሁሉ የፍች ወረቀቷን ሰጥቼ አባረርኋት። ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አይታ እንዳልፈራች አየሁ፤ ወጥታም አመነዘረች። በቅሌቷም ምድሪቱን አረከሰች፤ ከድንጋይና ከግንድ ጋራ አመነዘረች፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳ ወደ እኔ የተመለሰችው በማስመሰል እንጂ በሙሉ ልቧ አልነበረም” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ከከሓዲዋ ይሁዳ ይልቅ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ጻድቅ ሆና ተገኘች። ሂድና ይህን መልእክት ወደ ሰሜን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ “ ‘ከዳተኛዪቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሽ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እኔ መሓሪ ስለ ሆንሁ፣ ከእንግዲህ በቍጣ ዐይን አላይሽም’ ይላል እግዚአብሔር። ‘ለዘላለም አልቈጣም። በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅሽ፣ ክብርሽንም ለእንግዶች አማልክት፣ በየለምለሙ ዛፍ ሥር አሳልፈሽ በመስጠት፣ ለእኔ ባለመታዘዝሽ፣ በደለኛ መሆንሽን ይህን አንድ ነገር ብቻ እመኚ’ ” ይላል እግዚአብሔር። “ከዳተኛ ልጆች ሆይ፤ እኔ ባለቤታችሁ ነኝና ተመለሱ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከአንድ ከተማ አንድ፣ ከአንድ ነገድ ሁለት መርጫችሁ ወደ ጽዮን አመጣችኋለሁ። እንደ ልቤም የሆኑ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የሚመሯችሁን እረኞች እሰጣችኋለሁ። ቍጥራችሁ በምድሪቱ እጅግ በሚበዛበት ጊዜም” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚያ ዘመን፣ ‘የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት’ ብለው ከእንግዲህ አይጠሩም፤ ትዝ አይላቸውም፤ አያስታውሱትምም፤ አይጠፋም፤ ሌላም አይሠራም። በዚያ ጊዜ ኢየሩሳሌምን፣ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ብለው ይጠሯታል፤ መንግሥታትም ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ለማክበር በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ የክፉ ልባቸውንም እልኸኝነት ከእንግዲህ አይከተሉም። በዚያ ዘመን የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት በአንድነት ሆነው ከሰሜን ምድር ለአባቶቻቸው ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይመጣሉ።
ኤርምያስ 3:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሰው ዘንድ፦ ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? ይባላል። አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። ዓይንሽን አንሥተሽ ወደ ወናዎች ኮረብቶች ተመልከቺ፥ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ዓረባዊ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸው ነበር፥ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የኋለኛውም ዝናብ ጠፋ፥ የጋለሞታም ሴት ፊት ነበረብሽ፥ ታፍሪም ዘንድ እንቢ ብለሻል። አሁንም፦ አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ ብለሽ አልጮኽሽልኝምን? ለዘላለም ይቈጣልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን? እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገር አደረግሽ። እግዚአብሔርም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም ጋለሞተች። ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ፦ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፥ ነገር ግን አልተመለሰችም፥ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች። ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፥ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርስዋም ደግሞ ሄዳ እንደ ጋለሞተች አየሁ። በግልሙትናዋም በመቅለልዋም ምድሪቱ ረከሰች፥ እርስዋም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። በዚህም ሁሉ አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች። ሂድና ይህን ቃል ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፥ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ መሐሪ ነኝና፥ ለዘላለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላደርግም፥ ይላል እግዚአብሔር። በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል እግዚአብሔር። ከዳተኞች ልጆች ሆይ፥ እኔ ባላችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል እግዚአብሔር፥ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፥ እንደ ልቤም በግ ጠባቆችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል። በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን፦ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፥ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም። በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርስዋ ይሰበሰባሉ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፥ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።
ኤርምያስ 3:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ እርስዋም ከእርሱ ተለይታ ሌላ ወንድ ካገባች በኋላ እንደገና መልሶ ሊያገባት ይችላልን? ይህ ቢደረግማ ፈጽሞ ምድርን የሚያረክስ ይሆናል። እስራኤል ሆይ! አንቺ ግን ብዙ ጣዖቶችን ወደሽ ነበር፤ አሁን ደግሞ እንደገና ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽ። እስቲ ቀና ብለሽ ወደ ኰረብቶች ራስ ተመልከቺ፤ ከቶ አንቺ ለጣዖቶች ያልሰገድሽበት ስፍራ ይገኛልን? ቀማኛ፥ ሸማቂ፥ ዘላን በበረሓ ተቀምጦ ሊዘርፈው የሚፈልገውን መንገደኛ እንደሚጠባበቅ፥ አንቺም ፍቅረኛዋን ለማጥመድ በየመንገዱ ዳር እንደምትጠባበቅ ሴት ሆነሽ በአምልኮ ዝሙትሽ ኃጢአት ምድርን አረከስሽ። የበልጉም ሆነ የክረምት ዝናብ ሊቀር የቻለው በዚህ ምክንያት ነው፤ አንቺ ዐይነ ዐፋርነትን አስወግደሽ እንደ አመንዝራ ሴት ኀፍረተቢስ ሆነሻል። “አሁን ‘አባቴ፥ የልጅነት ጓደኛዬ’ ብለሽ አልጠራሽኝምን? አንቺ፦ ‘እርሱ ዘወትር ይቈጣልን? ኀይለኛ ቊጣውስ ዘላቂ ነውን?’ ብለሽ ተናግረሻል፤ ነገር ግን የምትችዪውን ክፉ ሥራ ትሠሪያለሽ።” ኢዮስያስ በነገሠበት ዘመን እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “እምነት አጒዳይ የሆነችው እስራኤል ምን እንዳደረገች አይተሃልን? እርስዋ ከእኔ ተለይታ በየከፍተኛው ተራራና በየለመለመው ዛፍ ሥር ጣዖትን በማምለክ ርኲሰትን ፈጽማለች። ይህን ሁሉ ከፈጸመች በኋላ እንደገና ወደ እኔ የምትመለስ መስሎኝ ነበር፤ እርስዋ ግን አልተመለሰችም፤ እምነት የማይጣልባት የእርስዋ እኅት ይሁዳም ይህን ሁሉ አይታለች። እስራኤል እኔን ማምለክዋን ትታ የጣዖት አምልኮን ተከተለች፤ ይህንንም ስታደርግ የተውኳት መሆኔን ይሁዳ ተመልክታለች፤ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት ይሁዳ ፍርሀት አላደረባትም፤ እርስዋም በበኩልዋ ጣዖት አምላኪ ሆናለች። ከቶም አላፈረችም፤ ይልቁንም ድንጋይና ዛፍ በማምለክ ምድሪቱን አረከሰች። ይህን ሁሉ ከፈጸመች በኋላ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት የሆነችው ይሁዳ፥ እንደገና ወደ እኔ ለመመለስ የምትሞክር መስላ የታየችው ከልብዋ ሳይሆን ከአንገት በላይ ነበር፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ምንም እንኳ እስራኤል ከእርሱ ብትለይ፥ እምነት ከማይጣልባት ከይሁዳ የምትሻልበት መንገድ መኖሩን እግዚአብሔር ነገረኝ። ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ ሰሜን ሄጄ ለእስራኤል እንድነግራት ያዘዘኝ ይህ ነው፤ “እምነት የማይጣልብሽ እስራኤል ሆይ! ወደ እኔ ተመለሺ፤ እኔ ምሕረቴ የበዛ ስለ ሆነ አልቈጣም፤ በአንቺ ላይ የምቈጣውም ለዘለዓለም አይደለም። አንቺ በደለኛ መሆንሽንና በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅሽን ብቻ እመኚ፤ ከባዕዳን አማልክት ጋር በየለምለሙ ዛፍ ሥር የጣዖት አምልኮ ርኲሰት መፈጸምሽንና ለሕጌም ያለመታዘዝሽን ተናዘዢ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “እናንተ እምነት የማይጣልባችሁ ሕዝብ ሆይ! የእኔ ስለ ሆናችሁ ተመለሱ፤ ከእናንተ መካከል ከየአንዳንዱ ከተማ አንዳንድ፥ ከእያንዳንዱም ቤተሰብ ሁለት ሁለት መርጬ ወደ ጽዮን ተራራ አመጣችኋለሁ። ለእኔ የሚታዘዙ ጠባቂዎችን እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በጥበብና በማስተዋል ይመሩአችኋል። በዚያችም ምድር ቊጥራችሁ በሚበዛበት ጊዜ ስለ ኪዳኔ ታቦት የሚናገሩ ሰዎች አይኖሩም፤ ከዚያን በኋላ ስለ እርሱ አያስቡም፤ ሊያስታውሱትም አይችሉም፤ አስፈላጊነቱ ስለማይታያቸው እንደገና ሌላ ለመሥራት አይሞክሩም። በዚያን ዘመን ኢየሩሳሌም ራስዋ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ተብላ ትጠራለች፤ ሕዝብም ሁሉ እኔን ለማምለክ በዚያ ይሰበሰባሉ። ከዚያን በኋላ እልኸኛና የክፉ ሐሳብ ምንጭ የሆነውን ልባቸውን አይከተሉም። እስራኤልና ይሁዳ አንድ ይሆናሉ፤ ሁለቱም በአንድነት በስተሰሜን ካለው አገር ከምርኮ ይመለሳሉ፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የዘለዓለም ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ተመልሰው ይገባሉ።”
ኤርምያስ 3:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ብትሄድ ሌላም ወንድ ብታገባ፥ በውኑ በድጋሚ ወደ እርሷ ይመለሳልን? ያች ምድር እጅግ የረከሰች አትሆንምን? አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል ጌታ። ወደ ተራቈቱ ኮረብቶች አይኖችሽን አንሺ፥ ተመልከቺም፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ልክ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አረባዊ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸዋለሽ፤ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የበልጉም ዝናብ ጠፋ፤ የጋለሞታም ሴት ፊት ቢኖርሺም እንኳ ለማፈር ግን እንቢ አልሽ። አሁን፦ ‘አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ’ ብለሽ አልጠራሽኝምን? ‘ለዘለዓለምስ ይቈጣልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን?’ እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገሮች አደረግሽ።” ጌታም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፦ “ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም አመነዘረች። ‘ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደ እኔ ትመለሳለች’ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች። ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ፤ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፤ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርሷም ደግሞ ሄዳ እንደ አመነዘረች አየሁ። አመንዝራነትዋንም እንደ ቀላል በመቁጠሩዋ ምድሪቱን አረከሰች፤ እርሷም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። በዚህም ሁሉ ግን አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም፥ ይላል ጌታ። “ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች። ሂድና ይህን ቃላት ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ! ተመለሽ፥ ይላል ጌታ፤ መሐሪ ነኝና፥ ለዘለዓለምም አልቈጣም፥ በአንቺ ላይ ፊቴን አላጠቁርም፥ ይላል ጌታ። በአምላክሽ በጌታ ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ድምፄንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል ጌታ። ከዳተኞች ልጆች ሆይ! እኔ ጌታችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል ጌታ፤ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤” እንደ ልቤም የሆኑ እረኞችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ያሰማርዋችኋል። በምድርም ላይ በበዛችሁና በበረከታችሁ ጊዜ፥ ይላል ጌታ፥ በዚያ ዘመን፦ “የጌታ የቃል ኪዳኑ ታቦት” ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስታውሱትም፥ አይሹትምም፤ በድጋሚም አይሠራም። በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የጌታ ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ በጌታ ስም አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሷ ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልኸኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳሉ፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።