ትንቢተ ኤርምያስ 3
3
የእስራኤል እምነት ጐደሎነት
1“ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? አንቺም ከብዙ እረኞች ጋር አመንዝረሻል፤ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። 2ዐይኖችሽን አቅንተሽ አንሺ፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ እንዳለም ተመልከች። እንደ ምድረ በዳ ቍራዎች በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ በዝሙትሽና በክፋትሽ ምድሪቱን አርክሰሻታልና። 3ለጕስቍልናሽ ከብዙዎች እረኞች ጋር ኖርሽ#ዕብ. “ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ የኋለኛውም ዝናም ጠፋ” የሚል ይጨምራል። የአመንዝራም ሴት ፊት ነበረብሽ፥ በሁሉም ዘንድ ያለ ኀፍረት ሄድሽ። ስለዚህ የመከርና የበልግ ዝናም ተከለከለ። 4አሁንም፦ እንደ ጌታሽና እንደ አባትሽ፥ እንደ ልጅነት ባልሽም አልጠራሽኝምን? 5ቍጣው ለዘለዓለም ይኖራልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን? እነሆ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፤ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገር አደረግሽ።”
6እግዚአብሔርም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፥ “ከዳተኛዪቱ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ቤተ እስራኤል” ይላል። እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ፥ ወደ ለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች፤ በዚያም አመነዘረች። 7ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ፦ ወደ እኔ ተመለሽ አልኋት፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅቷ ይሁዳም አየች። 8ከዳተኛዪቱም እስራኤል እንዳመነዘረች አየሁ፤ የፍችዋንም ደብዳቤ በእጅዋ ሰጥቼ ሰደድኋት፤ ጎስቋላ እኅቷ ይሁዳ ግን በዚያ አልፈራችም፤ እርስዋም ደግሞ ሄዳ አመነዘረች። 9ዝሙቷም ከንቱ ሆነ፤ እርስዋም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። 10በዚህም ሁሉ ከዳተኛዪቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም” ይላል እግዚአብሔር።
11እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ከጎስቋላዋ ይሁዳ ይልቅ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ራስዋን አጸደቀች። 12ሂድና ይህን ቃል ወደ ሰሜን ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ሆይ! ወደ እኔ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ መሓሪ ነኝና፥ ለዘለዓለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላጸናም፥” ይላል እግዚአብሔር። 13በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኀጢአትሽን ብቻ ዕወቂ ይላል እግዚአብሔር። 14ከዳተኞች ልጆች ሆይ! እኔ እገዛችኋለሁና ተመለሱ፤ ይላል እግዚአብሔር። አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፤ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤ 15እንደ ልቤም የሚሆኑ ጠባቂዎችን እሰጣችኋለሁ፤ በዕውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል።
16“በበዛችሁ ጊዜ፥ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥” ይላል እግዚአብሔር፤ በዚያ ዘመን፦ የእስራኤል ቅዱስ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት እነኋት አይሉም፤ በልባቸውም አያስቧትም፤ በአፋቸውም አይጠሯትም፤ ከእንግዲህ ወዲህም አይሿትም። 17ያንጊዜም ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፤ አሕዛብም ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። 18በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።
የሕዝቡ ባዕድ አምልኮ
19“እኔም፦ ይሁን አልሁ፤ በወንዶች ልጆች መካከል እሾምሃለሁ፤ አሕዛብን የሚገዛ ሁሉን ቻይ የሆነ የእግዚአብሔርን ርስት የተመረጠችውን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ አባቴ ትለኛለህ፤ ከእኔም አትመለስም አልሁ ብለሃልና። 20ሚስት ባልዋን እንደምትከዳ እንዲሁ የእስራኤል ቤት ከዱኝ” ይላል እግዚአብሔር። 21የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ዐምጸዋልና፥ ቅዱስ አምላካቸውንም ረስተዋልና ከብዙ ሰዎች ድምፅ ተሰማ፤ የእስራኤል ልጆች ልቅሶና ጩኸትም ተሰማ።
22“ከዳተኞች ልጆች ሆይ! ተመለሱ፤ ቍስላችሁንም#ዕብ. “ከዳተኝነታችሁን” ይላል። እፈውሳለሁ። እነሆ እኛ አገልጋዮችህ እንሆናለን፤ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና። 23በእውነት የተራሮች ኀይል፥ የኮረብቶችም ኀይል ሐሰት ነው፤ ነገር ግን የእስራኤል መዳን በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ነው። 24ነገር ግን ከትንሽነታችን ጀምሮ የአባቶቻችንን ሥራ፥ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም፥ እፍረት በልቶባቸዋል። 25ከትንሽነታችን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኛና አባቶቻችን በአምላካችን በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርተናልና፥ የአምላካችንንም የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማንምና በእፍረታችን ተኝተናል፤ ውርደታችንም ሸፍኖናል።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ