የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 3

3
የእስራኤል አለመታመን
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ እርስዋም ከእርሱ ተለይታ ሌላ ወንድ ካገባች በኋላ እንደገና መልሶ ሊያገባት ይችላልን? ይህ ቢደረግማ ፈጽሞ ምድርን የሚያረክስ ይሆናል። እስራኤል ሆይ! አንቺ ግን ብዙ ጣዖቶችን ወደሽ ነበር፤ አሁን ደግሞ እንደገና ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽ። 2እስቲ ቀና ብለሽ ወደ ኰረብቶች ራስ ተመልከቺ፤ ከቶ አንቺ ለጣዖቶች ያልሰገድሽበት ስፍራ ይገኛልን? ቀማኛ፥ ሸማቂ፥ ዘላን በበረሓ ተቀምጦ ሊዘርፈው የሚፈልገውን መንገደኛ እንደሚጠባበቅ፥ አንቺም ፍቅረኛዋን ለማጥመድ በየመንገዱ ዳር እንደምትጠባበቅ ሴት ሆነሽ በአምልኮ ዝሙትሽ ኃጢአት ምድርን አረከስሽ። 3የበልጉም ሆነ የክረምት ዝናብ ሊቀር የቻለው በዚህ ምክንያት ነው፤ አንቺ ዐይነ ዐፋርነትን አስወግደሽ እንደ አመንዝራ ሴት ኀፍረተቢስ ሆነሻል።
4“አሁን ‘አባቴ፥ የልጅነት ጓደኛዬ’ ብለሽ አልጠራሽኝምን? 5አንቺ፦ ‘እርሱ ዘወትር ይቈጣልን? ኀይለኛ ቊጣውስ ዘላቂ ነውን?’ ብለሽ ተናግረሻል፤ ነገር ግን የምትችዪውን ክፉ ሥራ ትሠሪያለሽ።”
እስራኤልና ይሁዳ ለንስሓ መጠራታቸው
6ኢዮስያስ በነገሠበት ዘመን እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “እምነት አጒዳይ የሆነችው እስራኤል ምን እንዳደረገች አይተሃልን? እርስዋ ከእኔ ተለይታ በየከፍተኛው ተራራና በየለመለመው ዛፍ ሥር ጣዖትን በማምለክ ርኲሰትን ፈጽማለች። #2ነገ. 22፥1—23፥30፤ 2ዜ.መ. 34፥1—35፥27። 7ይህን ሁሉ ከፈጸመች በኋላ እንደገና ወደ እኔ የምትመለስ መስሎኝ ነበር፤ እርስዋ ግን አልተመለሰችም፤ እምነት የማይጣልባት የእርስዋ እኅት ይሁዳም ይህን ሁሉ አይታለች። 8እስራኤል እኔን ማምለክዋን ትታ የጣዖት አምልኮን ተከተለች፤ ይህንንም ስታደርግ የተውኳት መሆኔን ይሁዳ ተመልክታለች፤ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት ይሁዳ ፍርሀት አላደረባትም፤ እርስዋም በበኩልዋ ጣዖት አምላኪ ሆናለች። 9ከቶም አላፈረችም፤ ይልቁንም ድንጋይና ዛፍ በማምለክ ምድሪቱን አረከሰች። 10ይህን ሁሉ ከፈጸመች በኋላ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት የሆነችው ይሁዳ፥ እንደገና ወደ እኔ ለመመለስ የምትሞክር መስላ የታየችው ከልብዋ ሳይሆን ከአንገት በላይ ነበር፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
11ምንም እንኳ እስራኤል ከእርሱ ብትለይ፥ እምነት ከማይጣልባት ከይሁዳ የምትሻልበት መንገድ መኖሩን እግዚአብሔር ነገረኝ። 12ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ ሰሜን ሄጄ ለእስራኤል እንድነግራት ያዘዘኝ ይህ ነው፤ “እምነት የማይጣልብሽ እስራኤል ሆይ! ወደ እኔ ተመለሺ፤ እኔ ምሕረቴ የበዛ ስለ ሆነ አልቈጣም፤ በአንቺ ላይ የምቈጣውም ለዘለዓለም አይደለም። 13አንቺ በደለኛ መሆንሽንና በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅሽን ብቻ እመኚ፤ ከባዕዳን አማልክት ጋር በየለምለሙ ዛፍ ሥር የጣዖት አምልኮ ርኲሰት መፈጸምሽንና ለሕጌም ያለመታዘዝሽን ተናዘዢ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
14“እናንተ እምነት የማይጣልባችሁ ሕዝብ ሆይ! የእኔ ስለ ሆናችሁ ተመለሱ፤ ከእናንተ መካከል ከየአንዳንዱ ከተማ አንዳንድ፥ ከእያንዳንዱም ቤተሰብ ሁለት ሁለት መርጬ ወደ ጽዮን ተራራ አመጣችኋለሁ። 15ለእኔ የሚታዘዙ ጠባቂዎችን እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በጥበብና በማስተዋል ይመሩአችኋል። 16በዚያችም ምድር ቊጥራችሁ በሚበዛበት ጊዜ ስለ ኪዳኔ ታቦት የሚናገሩ ሰዎች አይኖሩም፤ ከዚያን በኋላ ስለ እርሱ አያስቡም፤ ሊያስታውሱትም አይችሉም፤ አስፈላጊነቱ ስለማይታያቸው እንደገና ሌላ ለመሥራት አይሞክሩም። 17በዚያን ዘመን ኢየሩሳሌም ራስዋ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ተብላ ትጠራለች፤ ሕዝብም ሁሉ እኔን ለማምለክ በዚያ ይሰበሰባሉ። ከዚያን በኋላ እልኸኛና የክፉ ሐሳብ ምንጭ የሆነውን ልባቸውን አይከተሉም። 18እስራኤልና ይሁዳ አንድ ይሆናሉ፤ ሁለቱም በአንድነት በስተሰሜን ካለው አገር ከምርኮ ይመለሳሉ፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የዘለዓለም ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ተመልሰው ይገባሉ።”
የእግዚአብሔር ሕዝብ የፈጸሙት ባዕድ አምልኮ
19እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እስራኤል ሆይ! አንቺን እንደ ልጅ አድርጌ በመቀበል፥
ከዓለም እጅግ የተዋበችውንና ለም የሆነችውን ምድር ልሰጥሽ ፈለግኹ፤
‘አባት’ ብለሽ እንድትጠሪኝና ዳግመኛ ከእኔ እንዳትርቂ በመጠበቅ ነበር።
20አንቺ ግን ባልዋን እንደ ከዳች ሚስት ለእኔ ታማኝ አልሆንሽም፤
ይህን እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”
21ልምላሜ በሌለባቸው ኰረብቶች ራስ ላይ ድምፅ ይሰማል፤
ይህም ድምፅ፥ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር
አምላካቸውን በመርሳት ኃጢአት ሲሠሩ ኖረው፥
አሁን በመጸጸት የሚያሰሙት የለቅሶና የልመና ድምፅ ነው።
22እናንተ ከእግዚአብሔር ርቃችሁ የነበራችሁ ሁሉ ተመለሱ፤
እርሱ ይፈውሳችኋል፤ ታማኞችም ያደርጋችኋል።
እናንተም እንዲህ ብላችኋል፦ “አዎ! እግዚአብሔር አምላካችን ስለ ሆነ ወደ እርሱ እንመለሳለን፤ 23በኮረብቶች ራስ ላይ ቅጥ ያጣ የባዕድ አምልኮ ፈንጠዝያ መፈጸማችን ምንም አልጠቀመንም፤ ለእስራኤል መዳን የሚገኘው ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። 24ነገር ግን አሳፋሪ ለሆኑ ጣዖቶች መስገዳችን፥ የበግና የከብት መንጋዎቻችንን ሁሉ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን ሁሉ፥ ከጥንት ጀምሮ የቀድሞ አባቶቻችን ደክመው ያፈሩልንን ሀብት ሁሉ እንድናጣ አድርጎናል። 25እኛና የቀድሞ አባቶቻችን በመደጋገም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔር አምላካችንን አሳዝነናል፤ ትእዛዞቹንም አልፈጸምንም፤ ስለዚህ በዕፍረት ልንወድቅና ውርደትም እንደ ልብስ ሊሸፍነን ይገባል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ