የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 2

2
እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ የሚያደርገው እንክብካቤ
1የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 2“ሂድና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በመጀመሪያ በምድረ በዳ ምንም በማያበቅልበት ትከተሉኝ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ሙሽራይቱ ለሙሽራው የምታሳየውን ፍቅርና ታማኝነት ለኔም ታሳይ እንደ ነበረ አስታውሳለሁ።
3እስራኤል ሆይ! አንቺ እንደ መከር መጀመሪያ ፍሬ ለእኔ የተለየሽ ነበርሽ፤
ለእኔም የተቀደስሽ ርስት ሆነሽ ነበር፤
ስለዚህም አንቺን መጒዳት በሚፈልጉት ሁሉ ላይ
መከራና መቅሠፍት አመጣሁባቸው።’
ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
የእስራኤል የቀድሞ አባቶች የሠሩት ኃጢአት
4እናንተ የያዕቆብ ልጆች የሆናችሁ፤
የእስራኤል ነገድ ሁሉ!
እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ስሙ፤
5እነሆ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኔ ርቀው የሄዱት በኔ ላይ ምን ጥፋት አግኝተው ነው?
እነርሱም ከንቱ የሆኑትን ጣዖቶች በማምለካቸው ራሳቸውን ከንቱዎች አደረጉ።
6እኔ እነርሱን ከምድረ ግብጽ አወጣኋቸው፤
በምድረ በዳ መራኋቸው፤
ጐድጓዳማ በሆነ መንገድ ድርቅና ጨለማ በበዛበት በረሓ፥
ማንም በማይኖርበትና በማይመላለስበት ምድር አሳለፍኳቸው፤
እነርሱ ግን ‘ይህን ሁሉ ያደረገልን አምላክ ወዴት ነው?’ ብለው እንኳ አልጠየቁም።
7የምታስገኘውን ሰብልና ሌሎችን መልካም ነገሮች ሁሉ አግኝተው እንዲደሰቱ
ለም ወደ ሆነች ምድር አገባኋቸው፤
እነርሱ ግን ምድሬን አበላሹ፤
የሰጠኋቸውን አገር አረከሱ።
8ካህናቱ ‘እግዚአብሔር ወዴት አለ?’ ብለው አልጠየቁም፤
የሕግ ምሁራን እንኳ አላወቁኝም፤
የሕዝብ ገዢዎች በእኔ ላይ ዐመፁ፤
ነቢያትም በበዓል ስም ትንቢት ተናገሩ፤
ከንቱ የሆኑ ጣዖቶችንም አመለኩ።”
እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያቀረበው ወቀሳ
9“ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር ገና እናንተን ሕዝቤን እወቅሳለሁ፤
በልጆቻችሁም ላይ ወቀሳ አቀርባለሁ፤
10ይህን የመሰለ ነገር ከዚህ በፊት ከቶ ተደርጎ እንደማያውቅ ታስተውሉ ዘንድ፥
እስቲ በስተ ምዕራብ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ሂዱ፤
በስተ ምሥራቅም ወደ ቄዳር ምድር መልእክተኞች ልካችሁ መርምሩ።
11ሐሰተኞች አማልክት ቢሆኑም እንኳ
አማልክቱን የሚቀያይር ሕዝብ የለም፤
ሕዝቤ ግን ክብር ያጐናጸፍኳቸውን እኔን አምላካቸውን
ምንም ሊያደርጉላቸው በማይችሉ ከንቱ አማልክት ለውጠውኛል።”
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሰማያት ሆይ! ከዚህ የተነሣ ደንግጡ፤
በታላቅ ፍርሀትም ተንቀጥቀጡ።
13ሕዝቤ ሁለት ኃጢአት ሠርተዋል፤
ይኸውም የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንኩትን እኔን ትተውኛል፤
ውሃ መቋጠር የማይችሉ የተሸነቈሩ ጒድጓዶችን ለራሳቸው ቆፍረዋል።”
የእምነተቢስነት ውጤት
14“እስራኤል የተገዛች ባሪያ አይደለችም፤ የቤት ውልድም ባሪያ አይደለችም፤
ታዲያ፥ ጠላቶችዋ (በምርኮ እንደ አውሬ የሚያድኑአት) ለምንድን ነው?
15ጠላቶችዋ እንደ ደቦል አንበሳ ያገሡባታል፤
አገርዋን ወደ ምድረ በዳ ለውጠውባታል፤
ከተሞችዋም ተቃጥለው ሰው የማይኖርባቸው ወና ሆነዋል።
16የሜምፊስና የጣፊናስ ሰዎች፥
መኻል አናትሽን ይላጩሻል።
17እስራኤል ሆይ! ይህ ሁሉ የደረሰብሽ በገዛ እጅሽ ነው፤
በመንገድ የምመራሽን እኔን አምላክሽን እግዚአብሔርን በመተውሽ ነው።
18ወደ ግብጽ ወርደሽ ከዓባይ ወንዝ ውሃ መጠጣት የፈለግሽው ምን ጥቅም ለማግኘት ነው?
ወደ አሦርስ ወርደሽ ከኤፍራጥስ ወንዝ
ውሃ መጠጣት የፈለግሽው ምን የምታተርፊ መስሎሽ ነው?
19እነሆ የራስሽ ክፋት ይቀጣሻል፤
ክሕደትሽ ይፈርድብሻል፤
እኔን አምላክሽን እግዚአብሔርን መተውሽና
ለእኔም የምታሳዪውን ክብር ማስቀረትሽ
ምን ያኽል ከባድና መራራ በደል እንደ ሆነ ትረጂአለሽ፤
ይህን የተናገርኩ እኔ ጌታ የሠራዊት አምላክ ነኝ።”
እግዚአብሔርን ለማምለክ የእስራኤል እምቢተኛነት
20ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እስራኤል ሆይ! ከብዙ ጊዜ በፊት ለኔ መታዘዝና
እኔን ማገልገል ትተሻል፤
በእርግጥም በተራራው ላይና በየዛፉ ጥላ ሥር
ሌሎች አማልክትን በማምለክ አመንዝረሻል።
21እኔ ከተመረጠ ዘር መልካም የወይን ተክል አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤
አንቺ ግን ተለውጠሽ እንደ ተበላሸ የበረሓ የወይን ተክል ሆነሻል።
22የቱንም ያኽል በእንዶድና በብዙ ሳሙና ብትታጠቢ፥
በደልሽ ግልጥ ሆኖ ይታየኛል።
23ታዲያ ‘ራሴን ከቶ አላረክስም፤
ለበዓልም ከቶ አልሰግድም’ ብለሽ ለማስተባበል እንዴት ትችያለሽ?
በሸለቆ ውስጥ ኃጢአት በመሥራት ያደረግሽውን ርኲሰት እስቲ ተመልከቺ፤
በፍትወት እንደ ተቃጠለች የበረሓ ግመል፥
ወዲያና ወዲህ ትባዝኚአለሽ።
24በበረሓ መኖርን የለመደች የሜዳ አህያ፥
ፍትወት በተቀሰቀሰባት ጊዜ ማን ሊቈጣጠራት ይችላል?
ወንዶች የሜዳ አህዮች ያሉበትን ስፍራ፥
ራስዋ አነፍንፋ ስለምትደርስበት፥
እነርሱ እርስዋን በመፈለግ መድከም አያስፈልጋቸውም።
25እስራኤል ሆይ! ከሌሎች አማልክት ጋር ለማመንዘር
በየስፍራው በመዞር ጫማሽን አትጨርሺ፤
ጉሮሮሽም በውሃ ጥም አይድረቅ፤
አንቺ ግን ‘እኔ ባዕዳን አማልክትን ስለ ወደድኩና
እነርሱን ለመከተል ስለ ቈረጥኩ ወደ ኋላ አልመለስም!’ ” ብለሻል።
የእስራኤል መቀጣት
26እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሌባ በሚያዝበት ጊዜ እንደሚያፍር፥ እናንተም የእስራኤል ሕዝብ ነገሥታትና መኳንንት፥ ካህናትና ነቢያት ሁሉ የምታፍሩበት ጊዜ ይመጣል። 27ዛፍን ‘አባታችን’፥ አለትንም ‘የወለድሽን እናታችን’ የምትሉ ሁሉ ኀፍረት ይደርስባችኋል፤ ይህም የሚሆነው ወደ እኔ በመመለስ ፈንታ ከእኔ ስለ ራቃችሁ ነው፤ መከራ ሲደርስባችሁ ግን መጥቼ እንዳድናችሁ ትጠይቁኛላችሁ።
28“በእጃችሁ የሠራችኋቸው አማልክት እስቲ የት አሉ? የሚችሉ ከሆነ መከራ ሲደርስባችሁ ተነሥተው ያድኑአችሁ፤ ይሁዳ ሆይ! ከተሞችህ ብዙዎች በሆኑ መጠን አማልክትህም በዝተዋል።” 29እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “ሁላችሁም ዐምፃችሁብኛል፤ ታዲያ ከእኔ ጋር የምትከራከሩት ስለምንድን ነው? 30ከቶ የምትታረሙ ስላልሆናችሁ፥ እኔ እናንተን መቅጣቴ ከንቱ ነው፤ እንደ ተቈጣ አንበሳ ሆናችሁ ነቢያቶቻችሁን በሰይፍ ገደላችሁ። 31እናንተ በዚህ ዘመን ያላችሁ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እኔ እግዚአብሔር የምላችሁን አድምጡ፤ እኔ ለእናንተ እንደ በረሓ፥ ወይም በድቅድቅ ጨለማ እንደ ተሞላ ምድር ሆንኩባችሁን? ታዲያ ‘እኛ የፈለግነውን እናደርጋለን እንጂ ከቶ ወደ አንተ አንመለስም’ የምትሉን ለምንድን ነው? 32ለመሆኑ ኰረዳ ጌጣጌጥዋን፥ ሙሽራም የሙሽርነት ልብስዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን ሊቈጠሩ ለማይችሉ ለብዙ ዘመናት ረስተውኛል። 33አንቺ ፍቅረኞችሽን ተከትለሽ ለመሮጥ ምንኛ ብልኅ ሆንሽ? እጅግ ብልሹ የሆኑት ሴቶች እንኳ በአካሄድሽ ይመራሉ። 34-35ልብሶችሽ በንጹሖችና በድኾች ደም ተበክለዋል።
“ነገር ግን ይህን ሁሉ አድርገሽ፥ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤ በእርግጥ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አይቈጣም!’ ትያለሽ፤ ነገር ግን ‘እኔ ኃጢአት አልሠራሁም’ ብለሽ በመካድሽ ምክንያት እኔ እግዚአብሔር እፈርድብሻለሁ። 36ወደ ባዕዳን ሕዝብ አማልክት ዘወር በማለትሽ ራስሽን አቃለሻል፤ ከዚህ በፊት በአሦር ምክንያት ኀፍረት እንደ ደረሰብሽ አሁን ደግሞ በግብጽ ምክንያት ኀፍረት ይደርስብሻል። 37እጅሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ በዕፍረት ከዚያ ቦታ ትሄጂአለሽ፤ እኔ እግዚአብሔር አንቺ የምትታመኝባቸውን ሁሉ ስላስወገድኩ ከእነርሱ የምታገኚው ምንም ነገር አይኖርም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ