እነሆ፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ብትሄድ ሌላም ወንድ ብታገባ፥ በውኑ በድጋሚ ወደ እርሷ ይመለሳልን? ያች ምድር እጅግ የረከሰች አትሆንምን? አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል ጌታ። ወደ ተራቈቱ ኮረብቶች አይኖችሽን አንሺ፥ ተመልከቺም፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ልክ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አረባዊ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸዋለሽ፤ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የበልጉም ዝናብ ጠፋ፤ የጋለሞታም ሴት ፊት ቢኖርሺም እንኳ ለማፈር ግን እንቢ አልሽ። አሁን፦ ‘አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ’ ብለሽ አልጠራሽኝምን? ‘ለዘለዓለምስ ይቈጣልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን?’ እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገሮች አደረግሽ።” ጌታም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፦ “ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም አመነዘረች። ‘ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደ እኔ ትመለሳለች’ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች። ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ፤ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፤ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርሷም ደግሞ ሄዳ እንደ አመነዘረች አየሁ። አመንዝራነትዋንም እንደ ቀላል በመቁጠሩዋ ምድሪቱን አረከሰች፤ እርሷም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። በዚህም ሁሉ ግን አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም፥ ይላል ጌታ። “ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች። ሂድና ይህን ቃላት ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ! ተመለሽ፥ ይላል ጌታ፤ መሐሪ ነኝና፥ ለዘለዓለምም አልቈጣም፥ በአንቺ ላይ ፊቴን አላጠቁርም፥ ይላል ጌታ። በአምላክሽ በጌታ ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ድምፄንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል ጌታ። ከዳተኞች ልጆች ሆይ! እኔ ጌታችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል ጌታ፤ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤” እንደ ልቤም የሆኑ እረኞችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ያሰማርዋችኋል። በምድርም ላይ በበዛችሁና በበረከታችሁ ጊዜ፥ ይላል ጌታ፥ በዚያ ዘመን፦ “የጌታ የቃል ኪዳኑ ታቦት” ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስታውሱትም፥ አይሹትምም፤ በድጋሚም አይሠራም። በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የጌታ ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ በጌታ ስም አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሷ ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልኸኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳሉ፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።
ትንቢተ ኤርምያስ 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 3:1-18
10 ቀናት
"ሰዎች በትዳር ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች ኋላ ቀር ሀሳብ አድርገው ይመለከቱታል፤ ሌሎች ደግሞ ጥልቅ የሆነ የፍቅር ስሜት ነው ብለው ይገልጹታል፤ ሌሎች ደግሞ በትዳር ጓደኛቸው ታማኝ አለመሆን ወይም በወላጆቻቸው መፋታት ጉዳት የደረሰባቸው ከሆኑ ለትዳር ያላቸው አመለካከት መልካምነት የሌለው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሁሉ አስተያየቶች ወይም ልምምዶች በላይ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ጋብቻ ብዙ የሚናገረው ነገር አለው። በዚህ የንባብ እቅድ ውስጥ እግዚአብሔር ስለ ጋብቻ ያለው አመለካከት ምን እንደሆነ መረዳት ትችላለህ።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች