ትንቢተ ኤርምያስ 3:1-18

ትንቢተ ኤርምያስ 3:1-18 አማ05

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ እርስዋም ከእርሱ ተለይታ ሌላ ወንድ ካገባች በኋላ እንደገና መልሶ ሊያገባት ይችላልን? ይህ ቢደረግማ ፈጽሞ ምድርን የሚያረክስ ይሆናል። እስራኤል ሆይ! አንቺ ግን ብዙ ጣዖቶችን ወደሽ ነበር፤ አሁን ደግሞ እንደገና ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽ። እስቲ ቀና ብለሽ ወደ ኰረብቶች ራስ ተመልከቺ፤ ከቶ አንቺ ለጣዖቶች ያልሰገድሽበት ስፍራ ይገኛልን? ቀማኛ፥ ሸማቂ፥ ዘላን በበረሓ ተቀምጦ ሊዘርፈው የሚፈልገውን መንገደኛ እንደሚጠባበቅ፥ አንቺም ፍቅረኛዋን ለማጥመድ በየመንገዱ ዳር እንደምትጠባበቅ ሴት ሆነሽ በአምልኮ ዝሙትሽ ኃጢአት ምድርን አረከስሽ። የበልጉም ሆነ የክረምት ዝናብ ሊቀር የቻለው በዚህ ምክንያት ነው፤ አንቺ ዐይነ ዐፋርነትን አስወግደሽ እንደ አመንዝራ ሴት ኀፍረተቢስ ሆነሻል። “አሁን ‘አባቴ፥ የልጅነት ጓደኛዬ’ ብለሽ አልጠራሽኝምን? አንቺ፦ ‘እርሱ ዘወትር ይቈጣልን? ኀይለኛ ቊጣውስ ዘላቂ ነውን?’ ብለሽ ተናግረሻል፤ ነገር ግን የምትችዪውን ክፉ ሥራ ትሠሪያለሽ።” ኢዮስያስ በነገሠበት ዘመን እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “እምነት አጒዳይ የሆነችው እስራኤል ምን እንዳደረገች አይተሃልን? እርስዋ ከእኔ ተለይታ በየከፍተኛው ተራራና በየለመለመው ዛፍ ሥር ጣዖትን በማምለክ ርኲሰትን ፈጽማለች። ይህን ሁሉ ከፈጸመች በኋላ እንደገና ወደ እኔ የምትመለስ መስሎኝ ነበር፤ እርስዋ ግን አልተመለሰችም፤ እምነት የማይጣልባት የእርስዋ እኅት ይሁዳም ይህን ሁሉ አይታለች። እስራኤል እኔን ማምለክዋን ትታ የጣዖት አምልኮን ተከተለች፤ ይህንንም ስታደርግ የተውኳት መሆኔን ይሁዳ ተመልክታለች፤ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት ይሁዳ ፍርሀት አላደረባትም፤ እርስዋም በበኩልዋ ጣዖት አምላኪ ሆናለች። ከቶም አላፈረችም፤ ይልቁንም ድንጋይና ዛፍ በማምለክ ምድሪቱን አረከሰች። ይህን ሁሉ ከፈጸመች በኋላ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት የሆነችው ይሁዳ፥ እንደገና ወደ እኔ ለመመለስ የምትሞክር መስላ የታየችው ከልብዋ ሳይሆን ከአንገት በላይ ነበር፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ምንም እንኳ እስራኤል ከእርሱ ብትለይ፥ እምነት ከማይጣልባት ከይሁዳ የምትሻልበት መንገድ መኖሩን እግዚአብሔር ነገረኝ። ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ ሰሜን ሄጄ ለእስራኤል እንድነግራት ያዘዘኝ ይህ ነው፤ “እምነት የማይጣልብሽ እስራኤል ሆይ! ወደ እኔ ተመለሺ፤ እኔ ምሕረቴ የበዛ ስለ ሆነ አልቈጣም፤ በአንቺ ላይ የምቈጣውም ለዘለዓለም አይደለም። አንቺ በደለኛ መሆንሽንና በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅሽን ብቻ እመኚ፤ ከባዕዳን አማልክት ጋር በየለምለሙ ዛፍ ሥር የጣዖት አምልኮ ርኲሰት መፈጸምሽንና ለሕጌም ያለመታዘዝሽን ተናዘዢ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “እናንተ እምነት የማይጣልባችሁ ሕዝብ ሆይ! የእኔ ስለ ሆናችሁ ተመለሱ፤ ከእናንተ መካከል ከየአንዳንዱ ከተማ አንዳንድ፥ ከእያንዳንዱም ቤተሰብ ሁለት ሁለት መርጬ ወደ ጽዮን ተራራ አመጣችኋለሁ። ለእኔ የሚታዘዙ ጠባቂዎችን እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በጥበብና በማስተዋል ይመሩአችኋል። በዚያችም ምድር ቊጥራችሁ በሚበዛበት ጊዜ ስለ ኪዳኔ ታቦት የሚናገሩ ሰዎች አይኖሩም፤ ከዚያን በኋላ ስለ እርሱ አያስቡም፤ ሊያስታውሱትም አይችሉም፤ አስፈላጊነቱ ስለማይታያቸው እንደገና ሌላ ለመሥራት አይሞክሩም። በዚያን ዘመን ኢየሩሳሌም ራስዋ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ተብላ ትጠራለች፤ ሕዝብም ሁሉ እኔን ለማምለክ በዚያ ይሰበሰባሉ። ከዚያን በኋላ እልኸኛና የክፉ ሐሳብ ምንጭ የሆነውን ልባቸውን አይከተሉም። እስራኤልና ይሁዳ አንድ ይሆናሉ፤ ሁለቱም በአንድነት በስተሰሜን ካለው አገር ከምርኮ ይመለሳሉ፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የዘለዓለም ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ተመልሰው ይገባሉ።”