ትንቢተ ኤርምያስ 3
3
የእስራኤል አለመታመን
1እነሆ፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ብትሄድ ሌላም ወንድ ብታገባ፥ በውኑ በድጋሚ ወደ እርሷ ይመለሳልን? ያች ምድር እጅግ የረከሰች አትሆንምን? አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል ጌታ። 2ወደ ተራቈቱ ኮረብቶች አይኖችሽን አንሺ፥ ተመልከቺም፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ልክ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አረባዊ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸዋለሽ፤ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። 3ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የበልጉም ዝናብ ጠፋ፤ የጋለሞታም ሴት ፊት ቢኖርሺም እንኳ ለማፈር ግን እንቢ አልሽ። 4አሁን፦ ‘አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ’ ብለሽ አልጠራሽኝምን? 5‘ለዘለዓለምስ ይቈጣልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን?’ እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገሮች አደረግሽ።”
የንስሐ ጥሪ
6 #
2ነገ. 22፥1—23፥30፤ 2ዜ.መ. 34፥1—35፥27። ጌታም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፦ “ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም አመነዘረች። 7‘ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደ እኔ ትመለሳለች’ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች። 8ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ፤ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፤ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርሷም ደግሞ ሄዳ እንደ አመነዘረች አየሁ። 9አመንዝራነትዋንም እንደ ቀላል በመቁጠሩዋ ምድሪቱን አረከሰች፤ እርሷም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። 10በዚህም ሁሉ ግን አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም፥ ይላል ጌታ።
11“ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች። 12ሂድና ይህን ቃላት ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ! ተመለሽ፥ ይላል ጌታ፤ መሐሪ ነኝና፥ ለዘለዓለምም አልቈጣም፥ በአንቺ ላይ ፊቴን አላጠቁርም፥ ይላል ጌታ። 13በአምላክሽ በጌታ ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ድምፄንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል ጌታ። 14ከዳተኞች ልጆች ሆይ! እኔ ጌታችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል ጌታ፤ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤” 15እንደ ልቤም የሆኑ እረኞችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ያሰማርዋችኋል። 16በምድርም ላይ በበዛችሁና በበረከታችሁ ጊዜ፥ ይላል ጌታ፥ በዚያ ዘመን፦ “የጌታ የቃል ኪዳኑ ታቦት” ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስታውሱትም፥ አይሹትምም፤ በድጋሚም አይሠራም። 17በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የጌታ ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ በጌታ ስም አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሷ ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልኸኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። 18በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳሉ፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ። 19እኔ ግን፦ “‘ከወንዶች ልጆች ጋር እንዴት አስቀምጥሻለሁ? ያማረችውንስ ምድር እጅግ የከበረችውን የአሕዛብን ርስት እንዴት እሰጥሻለሁ? ብዬ ነበር። ደግሞ፦ አባቴ ብለሽ ትጠሪኛለሽ፤ እኔንም ከመከተል አትመለሽም ብዬ ነበር። 20የእስራኤል ቤት ሆይ! በእውነት ሚስት ባልዋን እንደምታታልል እንዲሁ አታለላችሁኝ ይላል ጌታ።’” 21የእስራኤል ልጆች መንገዳቸውን አጣምመዋልና፥ አምላካቸውንም ጌታን ረስተዋልና በተራቈቱ ኮረብቶች ላይ የልመናቸው የለቅሶ ድምፅ ተሰማ።
22“ከዳተኞች ልጆች ሆይ! ተመለሱ፥ ከዳተኛነታችሁንም እፈውሳለሁ።” “እነሆ፥ አንተ አምላካችን ጌታ ነህና ወደ አንተ መጥተናል። 23በእውነት ኮረብቶች ሐሰት ናቸው፥ በተራሮችም ላይ ሁከት ነው፤ በእውነት የእስራኤል መዳን በአምላካችን በጌታ ነው።” 24“ነገር ግን ከትንሽነታችን ጀምሮ የአባቶቻችን ድካም፥ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም፥ አሳፋሪ ነገር በልቶባቸዋል። 25ከትንሽነታችን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኛና አባቶቻችን በአምላካችን በጌታ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና፥ የአምላካችንንም የጌታን ድምፅ አልሰማንምና፥ በእፍረታችን እንጋደም፥ ውርደታችንም ይሸፍነን።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ