ትንቢተ ኤርምያስ 3
3
1በሰው ዘንድ፦ ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? ይባላል። አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። 2ዓይንሽን አንሥተሽ ወደ ወናዎች ኮረብቶች ተመልከቺ፥ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ዓረባዊ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸው ነበር፥ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። 3ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የኋለኛውም ዝናብ ጠፋ፥ የጋለሞታም ሴት ፊት ነበረብሽ፥ ታፍሪም ዘንድ እንቢ ብለሻል። 4አሁንም፦ አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ ብለሽ አልጮኽሽልኝምን? ለዘላለም ይቈጣልን? 5እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን? እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገር አደረግሽ።
6እግዚአብሔርም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም ጋለሞተች። 7ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ፦ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፥ ነገር ግን አልተመለሰችም፥ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች። 8ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፥ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርስዋም ደግሞ ሄዳ እንደ ጋለሞተች አየሁ። 9በግልሙትናዋም በመቅለልዋም ምድሪቱ ረከሰች፥ እርስዋም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። 10በዚህም ሁሉ አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም።
11እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች። 12ሂድና ይህን ቃል ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፥ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ መሐሪ ነኝና፥ ለዘላለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላደርግም፥ ይላል እግዚአብሔር። 13በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል እግዚአብሔር። 14ከዳተኞች ልጆች ሆይ፥ እኔ ባላችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል እግዚአብሔር፥ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፥ 15እንደ ልቤም በግ ጠባቆችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል። 16በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን፦ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፥ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም። 17በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርስዋ ይሰበሰባሉ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። 18በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፥ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።
19እኔ ግን፦ ከወንዶች ልጆች ጋር እንዴት አደርግሻለሁ? ያማረችውንስ ምድር የከበረችውን የአሕዛብን ሠራዊት ርስት እንዴት እሰጥሻለሁ? ብዬ ነበር። ደግሞ፦ አባቴ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እኔንም ከመከተል አትመለሽም ብዬ ነበር። 20የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ሚስት ባልዋን እንደምታታልል እንዲሁ አታለላችሁኝ ይላል እግዚአብሔር። 21የእስራኤል ልጆች መንገዳቸውን አጣምመዋልና፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተዋልና በወናዎች ኮረብቶች ላይ የልመናቸውና ልቅሶአቸው ድምፅ ተሰማ።
22ከዳተኞች ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከዳተኛነታችሁንም እፈውሳለሁ። እነሆ፥ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና ወደ አንተ እንመጣለን። 23በእውነት የኮረብቶችና የተራሮች ፍጅት ከንቱ ናት፥ በእውነት የእስራኤል መዳን በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ነው። 24ነገር ግን ከትንሽነታችን ጀምሮ የአባቶቻችን ድካም፥ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም፥ እፍረት በልቶባቸዋል። 25ከትንሽነታችን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኛና አባቶቻችን በአምላካችን በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርተናልና፥ የአምላካችንንም የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማንምና በእፍረታችን እንጋደም፥ ውርደታችንም ይክደነን።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 3: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ