የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 4

4
1እስራኤል ሆይ፥ ብትመለስ፥ ወደ እኔ ተመለስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ርኵሰትህንም ከፊቴ ብታስወግድ፥ ባትናወጥም፥ 2ሕያው እግዚአብሔርን! ብለህም በእውነትና በቅንነት በጽድቅም ብትምል፥ አሕዛብ በእርሱ ይባረካሉ በእርሱም ይመካሉ።
3እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲህ ይላልና፦ ጥጋቱን እርሻ እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ። 4እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ፥ ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፥ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፥ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ።
5በይሁዳ ዘንድ ተናገሩ በኢየሩሳሌምም ላይ አውሩና፦ በአገሪቱ ላይ መለከት ንፉ በሉ፥ ጮኻችሁም፦ ሁላችሁ ተሰብሰቡ ወደ ተመሸጉትም ከተሞች እንግባ በሉ። 6ከሰሜን ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁና ወደ ጽዮን ዓላማን አንሡ፥ ሽሹ፥ አትዘግዩ። 7አንበሳ ከጭፍቅ ዱር ወጥቶአል፥ አሕዛብንም የሚዘርፍ ተነሥቶአል፥ ምድርሽን ባድማ ያደርግ ዘንድ ከስፍራው ወጥቶአል፥ ከተሞችሽም ሰው የሌለባቸው ፍርስራሾች ይሆናሉ። 8የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ከእኛ ዘንድ አልተመለሰምና ማቅ ልበሱ፥ አልቅሱም ዋይም በሉ። 9በዚያም ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የንጉሡና የመኳንንቱ ልብ ይጠፋል፥ ካህናቱም ይደነቃሉ ነቢያቱም ይደነግጣሉ።
10እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ፥ አንተ ሰይፍ እስከ ነፍስ ድረስ በደረሰ ጊዜ፦ ሰላም ይሆንላችኋል ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን እጅግ አታለልህ አልሁ።
11በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም፦ ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን የሚያቃጥል ነፋስ በምድረ በዳ ካሉ ከወናዎች ኮረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ ይመጣል፥ 12ስለ እኔ ጽኑ የሆነ ነፋስ ከእነዚህ ይመጣል ይባላል። አሁንም እኔ ደግሞ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። 13እነሆ፥ እንደ ደመና ይወጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ፥ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ጠፍተናልና ወዮልን። 14ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ አሳብ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? 15የተናጋሪ ድምፅ ከዳን ዘንድ ይናገራልና፥ ከኤፍሬምም ኮረብቶች መከራን ያወራልና። 16ለአሕዛብ አሰሙና፦ እነሆ፥ ጠባቂዎች ከሩቅ አገር ይመጣሉ፥ በይሁዳም ከተሞች ላይ ይጮኻሉ ብላችሁ በኢየሩሳሌም ላይ አውሩ። 17በእኔ ላይ ዓመፀኛ ሆናለችና በዙሪያዋ ከብበው እንደ እርሻ ጠባቂዎች ሆነውባታል፥ ይላል እግዚአብሔር። 18መንገድሽና ሥራሽ ይህን አድርጎብሻል፥ ይህ ክፋትሽ መራር ነው፥ ወደ ልብሽም ደርሶአል።
19አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፥ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል፥ ነፍሴ ሆይ፥ የመለከትን ድምፅና የሰልፍን ውካታ ሰምተሻልና ዝም እል ዘንድ አልችልም። 20መከራ በመከራ ላይ ተጠርቶአል፥ ምድርም ሁሉ ተበዝብዛለችና፥ በድንገትም ድንኳኔ በቅጽበት ዓይንም መጋረጃዎቼ ጠፉ። 21ዓላማውን የምመለከት፥ የመለከቱንስ ድምፅ የምሰማ እስከ መቼ ነው? 22ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም፥ ሰነፎች ልጆች ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም፥ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፥ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም።
23ምድሪቱን አየሁ፥ እነሆም፥ ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም፥ ሰማያትንም አየሁ፥ ብርሃንም አልነበረባቸውም። 24ተራሮችን አየሁ፥ እነሆም፥ ተንቀጠቀጡ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ተናወጡ። 25አየሁ፥ እነሆም፥ ሰው አልነበረም፥ የሰማይም ወፎች ሁሉ ሸሽተው ነበር። 26አየሁ፥ እነሆም፥ ፍሬያማ እርሻ ምድረ በዳ ሆነች፥ ከተሞችም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ከጽኑ ቍጣው የተነሣ ፈርሰው ነበር።
27እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፥ ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም። 28ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፥ በላይም ሰማይ ይጠቍራል፥ ተናግሬአለሁና፥ አስቤአለሁም፥ አልጸጸትም ከእርሱም አልመለስም። 29ከፈረሰኞችና ከቀስተኞች ድምፅ የተነሣ ከተማ ሁሉ ሸሽታለች፥ ወደ ችፍግ ዱርም ይገባሉ በቋጥኝ ላይም ይወጣሉ፥ ከተማ ሁሉ ተለቅቃለች የሚቀመጥባትም ሰው የለም። 30አንቺም የተበዘበዝሽ ሆይ፥ ምን ታደርጊአለሽ? ቀይ በለበስሽ ጊዜ፥ በወርቅ አንባርም ባጌጥሽ ጊዜ፥ ዓይንሽንም በኵል በተኳልሽ ጊዜ፥ በከንቱ ታጌጫለሽ፥ ውሽሞችሽ አቃለሉሽ፥ ነፍስሽን ይሹአታል። 31እንደምታምጥ የበኵርዋንም እንደምትወልድ ሴት ድምፅ ሰምቻለሁና፥ የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ በድካም ይሰልላል፥ እጆችዋንም ትዘረጋለችና፦ ተገድለው ከሞቱት የተነሣ ነፍሴ ዝላለችና ወዮልኝ! አለች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ