ትንቢተ ኤርምያስ 5
5
1በኢየሩሳሌም መንገድ እየተመላለሳችሁ ሩጡ፥ ተመልከቱም፥ እወቁም፥ በአደባባይዋም ፈልጉ፥ ፍርድን የሚያደርገውን እውነትንም የሚሻውን ሰው ታገኙ እንደሆነ ይቅር እላታለሁ። 2እነርሱም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ቢሉ የሚምሉት በሐሰት ነው። 3አቤቱ፥ ዓይንህ እውነትን የምትመለከት አይደለችምን? አንተ ቀሥፈሃቸዋል ነገር ግን አላዘኑም፥ ቀጥቅጠሃቸውማል ነገር ግን ተግሣጽን እንቢ አሉ፥ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠንክረዋል፥ ይመለሱ ዘንድ እንቢ አሉ።
4እኔም፦ የእግዚአብሔርን መንገድና የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና እነዚህ በእውነት ድሆችና ሰነፎች ናቸው፥ 5ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ እናገራቸውማለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንገንድና የአምላካቸውን ሕግ ያውቃሉና አልሁ። እነዚህ ግን ቀንበሩን በአንድነት ሰብረዋል፥ እስራቱንም ቈርጠዋል። 6ስለዚህ ኃጢአታቸው በዝቶአልና፥ የክዳታቸውም ብዛት ጸንቶአልና ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰብራቸዋል፥ የበረሀም ተኵላ ያጠፋቸዋል፥ ነብርም በከተሞቻቸው ላይ ይተጋል፥ ከዚያም የሚወጣ ሁሉ ይነጠቃል።
7በእነዚህ ነገሮች ይቅር የምልሽ እንዴት አድርጌ ነው? ልጆችሽ ትተውኛል አማልክትም ባልሆኑ ምለዋል፥ ካጠገብኋቸውም በኋላ አመነዘሩ በጋለሞቶቹም ቤት ተሰበሰቡ። 8እንደ ተቀለቡ ፈረሶች ሆኑ፥ እያንዳንዳቸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ኋላ አሽካኩ። 9በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፥ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?
10ወደ ቅጥርዋ ወጥታችሁ አፍርሱ፥ ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉ፥ ለእግዚአብሔር አይደሉምና ቅርንጫፍዋን ውሰዱ። 11የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በእኔ ላይ እጅግ ወንጅለዋል ይላል እግዚአብሔር። 12እነርሱም፦ እርሱ አይደለም፥ ክፉ ነገርም አይመጣብንም ሰይፍንና ራብንም አናይም፥ ነቢያትም ነፋስ ይሆናሉ፥ 13የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ የለም፥ እንዲህም ይደረግባቸዋል ብለው እግዚአብሔርን ክደዋል።
14ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህ ቃል ተናግራችኋልና እነሆ፥ በአፍህ ውስጥ ቃሌን እሳት ይህንም ሕዝብ እንጨት አደርጋለሁ፥ ትበላቸውማለች። 15የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እነሆ፥ ሕዝብን ከሩቅ አመጣባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ኃያል ጥንታዊ ሕዝብ ነው፥ ቋንቋቸውንም የማታውቀው የሚናገሩትንም የማታስተውለው ሕዝብ ነው። 16የፍላጻቸውም ሰገባ እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ ሁሉም ኃያላን ናቸው። 17መከርህንና እንጀራህን ይበላሉ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህንም ይበሉአቸዋል፥ በጎችህንና ላሞችህንም ይበላሉ፥ ወይንህንና በለስህንም ይበላሉ፥ የምትታመናቸውን የተመሸጉ ከተሞችን በሰይፍ ይደበድባሉ። 18ነገር ግን በዚያ ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈጽሜ አላጠፋችሁም።
19እንዲህም ይሆናል፥ እናንተ፦ አምላካችን እግዚአብሔር ይህን ነገር ሁሉ ስለምን አደረገብን? ብትሉ፥ አንተ፦ እንደ ተዋችሁኝ በአገራችሁም ሌሎችን አማልክት እንዳመለካችሁ፥ እንዲሁ ለእናንተ ባልሆነ አገር ለሌሎች ሰዎች ትገዛላችሁ ትላቸዋለህ።
20ይህን በያዕቆብ ቤት አውሩ፥ በይሁዳም አሰሙ፦ 21እናንተ ሰነፎች ልበ ቢሶች፥ ዓይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ ሕዝብ ሆይ፥ ይህን ስሙ። 22በውኑ እኔን አትፈሩምን? ከፊቴስ አትደነግጡምን? ይላል እግዚአብሔር፥ እንዳያልፍ አሸዋን በዘላለም ትእዛዝ ለባሕር ዳርቻ አድርጌአለሁ፥ ሞገዱም ቢናወጥ አያሸንፍም፥ ቢጮኽም አያልፍበትም። 23ለዚህ ሕዝብ ግን የሸፈተና ያመፀ ልብ አላቸው፥ ዐምፀዋል ሄደውማል። 24በልባቸውም፦ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ አላሉም። 25በደላችሁ እነዚህን አስቀርታለች፥ ኃጢአታችሁም መልካምን ነገር ከለከለቻችሁ። 26በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፥ እንደ አጥማጆችም ያደባሉ፥ ወጥመድንም ይዘረጋሉ ሰዎችንም ያጠምዳሉ። 27ቀፎ ወፎችን እንደሚሞላ፥ እንዲሁ ቤታቸው ሽንገላን ሞልታለች፥ እንዲሁም ከብረዋል ባለ ጠጎችም ሆነዋል። 28ወፍረዋል ሰብተውማል፥ ክፋታቸውንም ያለ ልክ አብዝተዋል፥ የድሀ አደጎች ነገር መልካም እንዲሆን አልተምዋገቱላቸውም፥ የችግረኞችንም ፍርድ አልፈረዱላቸውም። 29በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፥ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?
30የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች፥ 31ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፥ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 5: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ