ትንቢተ ኤርምያስ 6
6
1እናንተ የብንያም ልጆች፥ ክፉ ነገር ታላቅም ጥፋት ከሰሜን ይጐበኛልና ከኢየሩሳሌም ውስጥ ሽሹ፥ በቴቁሔ መለከቱን ንፉ፥ በቤትሐካሪም ላይ ምልክት አንሡ። 2የተዋበችውንና የተሰባቀለችውን የጽዮንን ልጅ አጐሰቍላለሁ። 3እረኞችና መንጐቻቸው ወደ እርስዋ ይመጣሉ፥ በዙሪያዋም ድንኳኖቻቸውን ይተክሉባታል፥ እያንዳንዱም በስፍራው መንጋውን ያሰማራል። 4በእርስዋ ላይ ሰልፍ አዘጋጁ ተነሡ፥ በቀትርም እንውጣ። ቀኑ መሽቶአልና፥ የማታውም ጥላ ረዝሞአልና ወዮልን። 5ተነሡ በሌሊትም እንውጣ፥ አዳራሾችዋንም እናፍርስ። 6የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ዛፎችዋን ቍረጡ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ አፈርን ደልድሉ፥ ይህች ከተማ የምትቀሠፍ ናት፥ መካከልዋ ሁሉ ግፍ ብቻ ነው። 7በጕድጓድ ውኃ እንደሚፈልቅ፥ እንዲሁ ክፋትዋ ከእርስዋ ዘንድ ይፈልቃል፥ ግፍና ቅሚያ በእርስዋ ዘንድ ይሰማል፥ ደዌና ቍስልም ሁልጊዜ በፊቴ አለ። 8ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ወና እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበዪ።
9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰው ወይኑን እንደሚቃርም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የቀሩትን ፈጽሞ ይቃርሙአቸዋል፥ እጅህንም እንደ ለቃሚ ወደ እንቅብ ዘርጋ። 10ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት ለመስማትም አይችሉም፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም። 11ስለዚህ በእግዚአብሔር ቍጣ ተሞልቻለሁ፥ ከመታገሥ ደክሜአለሁ፥ በሜዳ በሕፃናት ላይ በጕልማሶችም ጉባዔ ላይ በአንድነት አፍስሰው፥ ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም ከጎበዙ ጋር ይያያዛልና። 12እጄን በምድር በሚኖሩ ላይ እዘረጋለሁና ቤቶቻቸው እርሻዎቻቸውም ሴቶቻቸውም በአንድነት ለሌሎች ይሆናሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 13ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና። 14የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፥ ሰላም ሳይሆን፦ ሰላም ሰላም ይላሉ። 15ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፥ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፥ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፥ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፥ እነርሱ ግን፦ አንሄድባትም አሉ። 17እኔም፦ የመለከቱን ድምፅ አድምጡ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፥ እነርሱ ግን፦ አናደምጥም አሉ። 18አሕዛብ ሆይ፥ ስለዚህ ስሙ፥ ማኅበር ሆይ፥ እነዚያ የሚያገኛቸውን እወቁ። 19ምድር ሆይ፥ ስሚ፥ እነሆ፥ ቃሌን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉ፥ በዚህ ሕዝብ ላይ የአሳባቸውን ፍሬ፥ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ። 20ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም አገር ቀረፋን ታቀርቡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም ሌላ መሥዋዕታችሁም ደስ አያሰኘኝም። 21ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከዚህ ሕዝብ ፊት ዕንቅፋቶችን አደርጋለሁ፥ አባቶችና ልጆች በአንድነት ይሰናከሉባቸዋል፥ ጎረቤትና ባልንጀራም ይጠፋሉ።
22እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን አገር ይመጣል፥ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻ ይነሣል። 23ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፥ ጨካኞች ናቸው፥ ምሕረትንም አያደርጉም፥ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል፥ በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፥ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፥ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ። 24ወሬውን ሰምተናል፥ እጃችን ደክማለች፥ ምጥ ወላድን ሴት እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞናል። 25የጠላት ሰይፍና ድንጋጤ ከብበዋችኋልና ወደ ሜዳ አትውጡ በመንገድም ላይ አትሂዱ። 26የሕዝቤ ልጅ ሆይ፥ ማቅ ልበሺ በአመድም ውስጥ ተንከባለዪ፥ አጥፊ በላያችን በድንገት ይመጣብናልና ለአንድያ ልጅ እንደሚደረግ ልቅሶ፥ መራራ ልቅሶ አልቅሺ።
27መንገዳቸውን እንድታውቅና እንድትፈትን በሕዝቤ መካከል ፈታኝ አድርጌሃለሁ። 28እነርሱ ሁሉ እጅግ ዓመፀኞች ናቸው፥ በጠማማነት ይሄዳሉ፥ ናስና ብረት ናቸው፥ ሁሉ ርኵሰትን ያደርጋሉ። 29ወናፉ አናፋ እርሳሱም በእሳት ቀለጠ፥ አንጥረኛውም መልሶ በከንቱ ያቀልጠዋል፥ ኃጢአተኞች አልተወገዱም። 30እግዚአብሔር ጥሎአቸዋልና የተጣለ ብር ብለው ይጠሩአቸዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 6: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ