የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 2

2
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2ሂድ፥ በኢየሩሳሌም ጆሮ ጩኽ፥ እንዲህም በል፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የብላቴንነትሽን ምሕረት የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተልሽኝ አስቤአለሁ። 3እስራኤል ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነበረ፥ የቡቃያውም በኵራት ነበረ፥ የበሉት እንደ በደለኞች ይቈጠራሉ፥ ክፉም ነገር ያገኛቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።
4የያዕቆብ ቤት የእስራኤልም ቤት ወገኖች ሁሉ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁ ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ ከንቱነትንም የተከተሉ፥ ከንቱም የሆኑ ምን ክፋት አግኝተውብኝ ነው? 6እነርሱም፦ ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በምድረ በዳም በባድማ ጕድጓድም ባለበት ምድር፥ በውኃ ጥምና በሞት ጥላ ምድር፥ ማንም በማያልፍበትና ማንም በማይቀመጥበት ምድር የመራን እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም። 7ፍሬዋንና በረከትዋንም ትበሉ ዘንድ ወደ ፍሬያማ ምድር አገባኋችሁ፥ ነገር ግን በገባችሁ ጊዜ ምድሬን አረከሳችሁ፥ ርስቴንም አጐሳቈላችሁ። 8ካህናቱም፦ እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም፥ ባለ ኦሪቶችም አላወቁኝም፥ ገዢዎችም ዐመፁብኝ፥ ነቢያትም በበኣል ትንቢት ተናገሩ፥ የማይረባንም ነገር ተከተሉ።
9ስለዚህ ከእናንተ ጋር እከራከራለሁ፥ ከልጆቻችሁም ልጆች ጋር እከራከራለሁ። 10ወደ ኪቲም ደሴቶች እለፉና ተመልከቱ፥ ወደ ቄዳርም ላኩና እጅግ መርምሩ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ሆኖ እንደ ሆነ እዩ። 11በውኑ አማልክት ያልሆኑትን አማልክቱን የለወጣቸው አንድ ሕዝብ አለን? ነገር ግን ሕዝቤ ክብሩን ለማይረባ ነገር ለወጠ። 12ሰማያት ሆይ፥ በዚህ ተደነቁ፥ እጅግም ደንግጡና ተንቀጥቀጡ ይላል እግዚአብሔር። 13ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና፥ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም ጕድጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጕድጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል።
14በውኑ እስራኤል ባሪያ ነውን? ወይስ የቤት ውላጅ ነውን? ስለምን ብዝበዛ ሆነ? 15የአንበሳ ደቦሎች በእርሱ ላይ አገሡ፥ ድምፃቸውንም ሰጡ፥ ምድሩንም ባድማ አደረጉ፥ ከተሞቹም ተቃጠሉ የሚቀመጥባቸውም የለም። 16የሜምፎስና የጣፍናስ ልጆች አስነወሩሽ አላገጡብሽም። 17ይህ ሁሉ የሆነብሽ እኔን ስለ ተውሽ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር አምላክሽ። 18አሁንስ የሺሖርን ውኃ ትጠጪ ዘንድ በግብጽ መንገድ ምን ጉዳይ አለሽ? የኤፍራጥስንም ውኃ ትጠጪ ዘንድ በአሦር መንገድ ምን ጉዳይ አለሽ? 19ክፋትሽ ይገሥጽሻል ክዳትሽም ይዘልፍሻል፥ አምላክሽንም እግዚአብሔርን የተውሽ እኔንም መፍራት የሌለብሽ ክፉና መራራ ነገር እንደ ሆነ እወቂ፥ ተመልከቺ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
20ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰብሬአለሁ እስራትሽንም ቈርጫለሁ፥ አንቺም፦ አላገለግልም አልሽ፥ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ። 21እኔ የተመረጠች ወይን ፍጹምም እውነተኛ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፥ አንቺ ግን ክፉ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆነሽ እንዴት ተለወጥሽብኝ? 22በእንዶድ ብትታጠቢም፥ ለራስሽም ሳሙና ብታበዢ፥ በእኔ ፊት በኃጢአትሽ ረክሰሻል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 23አንቺስ፦ አልረከስሁም በአሊምንም አልተከተልሁም እንዴት ትያለሽ? በቈላ ያለውን መንገድሽን ተመልከቺ፥ ያደረግሽውንም እወቂ፥ በመንገድም ላይ እንደ ተለቀቀች እንደ ፈጣን ግመል ሆነሻል፥ 24በምኞትዋ ነፋስን እንደምታሸትት፥ በምድረ በዳ እንደ ለመደች እንደ ሜዳ አህያ ነሽ፥ ከምኞትዋ የሚመልሳት ማን ነው? የሚሹአት ሁሉ አይደክሙም፥ በወራትዋ ያገኙአታል። 25እግርሽን ከሸካራ መንገድ ጕሮሮሽንም ከውኃ ጥም ከልክዪ፥ አንቺ ግን፦ እጨክናለሁ፥ እንግዶችን ወድጄአለሁና፥ እከተላቸዋለሁም አልሽ።
26ሌባ በተያዘ ጊዜ እንደሚያፍር እንዲሁ የእስራኤል ቤት፥ እነርሱና ንጉሦቻቸውም አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነቢያቶቻቸውም ያፍራሉ። 27ግንዱን፦ አንተ አባቴ ነህ፥ ድንጋዩንም፦ አንተ ወለድኸኝ ይላሉ፥ ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፥ በመከራቸው ጊዜ ግን፦ ተነሥተህ አድነን ይላሉ። 28ለአንተ የሠራሃቸው አማልክትህ ወዴት ናቸው? ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸውና ይነሡ በመከራህም ጊዜ ያድኑህ።
29ከእኔ ጋር የምትከራከሩ ለምንድር ነው? ሁላችሁ ዐምፃችሁብኛል ይላል እግዚአብሔር። 30ልጆቻችሁን በከንቱ ቀሥፌአቸዋለሁ፥ ተግሣጽን አልተቀበሉም፥ ሰይፋችሁ እንደሚሰብር አንበሳ ነቢያቶቻችሁን በልቶአል። 31ትውልድ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ተመልከቱ። በውኑ ለእስራኤል ምድረ በዳ ወይስ የጨለመች ምድር ሆንሁባትን? ሕዝቤስ ስለ ምን፦ እኛ ፈርጥጠናል፥ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ አንመለስም ይላል? 32በውኑ ቆንጆ ጌጥዋን ወይስ ሙሽራ ዝርግፍ ጌጥዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን የማይቈጠር ወራት ረስቶኛል። 33ፍቅርን ለመሻት መንገድሽን እንዴት ታቀኛለሽ! ስለዚህ ለክፉዎች ሴቶች እንኳ መንገድሽን አስተምረሻል። 34በእጆችሽም የንጹሐን ድሆች ደም ተገኝቶአል፥ በእነዚህ ሁሉ ላይ በግልጥ አገኘሁት እንጂ በስውር ፈልጌ አላገኘሁትም። 35አንቺ ግን፦ ንጹሕ ነኝ፥ በእውነት ቍጣው ከእኔ ተመልሶአል አልሽ። እነሆ፦ ኃጢአት አልሠራሁም ብለሻልና በፍርድ እከስስሻለሁ። 36መንገድሽን ትለውጪ ዘንድ ለምን እጅግ ትሮጫለሽ? አሦር እንዳሳፈረሽ ግብጽ ያሳፍርሻል። 37እግዚአብሔር የታመንሽባቸውን ጥሎአልና፥ በእነርሱም አይከናወንልሽምና እጅሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ ከዚያ ደግሞ ትወጫለሽ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ