የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 1

1
1በብንያም አገር በዓናቶት ከነበሩ ካህናት የሆነ የኬልቅያስ ልጅ የኤርምያስ ቃል። 2በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን በመንግሥቱ በአሥራ ሦስተኛው ዓመት የእግዚአብሔር ቃል መጣለት። 3በይሁዳም ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን፥ እስከ ይሁዳ ንጉሥ እስከ ኢዮስያስ ልጅ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ፍጻሜ፥ ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት እስከ አምስተኛው ወር ድረስ መጣ።
4የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ። 6እኔም፦ ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም አልሁ። 7እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፦ ወደምሰድድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና፦ ብላቴና ነኝ አትበል። 8እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና ከፊታቸው አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም፦ እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፥ 10እነሆ፥ ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ አድርጌሃለሁ አለኝ።
11ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል፦ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም፦ የለውዝ በትር አያለሁ አልሁ። 12እግዚአብሔርም፦ እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ።
13ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል፦ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም፦ የሚፈላ አፍላል አያለሁ፥ ፊቱም ከሰሜን ወገን ነው አልሁ። 14እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ከሰሜን ወገን ክፉ ነገር በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ ይገለጣል። 15እነሆ፥ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋ በቅጥርዋ ሁሉ ላይ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። 16ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተዉ ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። 17አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፥ ተነሥም፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ንገራቸው፥ በፊታቸው እንዳላስፈራህ አትፍራቸው። 18እነሆ፥ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በይሁዳም ነገሥታት በአለቆችዋና በካህናትዋ ላይ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ እንደ ተመሸገ ከተማ እንደ ብረትም ዓምድ እንደ ናስም ቅጥር ዛሬ አድርጌሃለሁ። 19ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፥ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፥ ይላል እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ