ትንቢተ ኢሳይያስ 66
66
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፥ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? 2እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፥ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። 3በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፥ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፥ የእህልን ቍርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፥ እጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፥ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል፥ 4እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን መርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ፥ በፊቴ ክፉ ነገርን አደረጉ፥ ያልወደድሁትንም መረጡ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝምና። 5በቃሉ የምትንቀጠቀጡ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፦ የጠሉአችሁ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ ወንድሞቻችሁ፦ ደስታችሁን እናይ ዘንድ እግዚአብሔር ይክበር ብለዋል፥ ነገር ግን ያፍራሉ። 6የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል። 7ሳታምጥ ወለደች፥ ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጅን ወለደች። 8ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና። 9በውኑ ወደ መውለድ የማደርስ እኔ አላስወልድምን? ይላል እግዚአብሔር፥ የማስወልድስ ማኅፀንን እኔ እዘጋለሁን? ይላል አምላክሽ። 10እናንተ የምትወድዱአት ሁሉ፥ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሤትን አድርጉ፥ ስለ እርስዋም ደስ ይበላችሁ፥ እናንተም የምታለቅሱላት ሁሉ፥ ከእርስዋ ጋር በደስታ ሐሤትን አድርጉ፥ 11ትጠቡ ዘንድ ከማጽናናትዋም ጡት ትጠግቡ ዘንድ፥ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ ይላችሁ ዘንድ። 12እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆም፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፥ ከዚያም ትጠባላችሁ፥ በጫንቃ ላይ ይሸከሙአችኋል በጕልበትም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሉአችኋል። 13እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ። 14ታያላችሁ፥ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፥ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፥ የእግዚአብሔርም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፥ በጠላቶቹም ላይ ይቈጣል። 15እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ። 16እግዚአብሔርም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ ይፈርዳል፥ በእግዚአብሔርም ተወግተው የሞቱት ይበዛሉ። 17በመካከላቸው ያለውን እንዱን ተከትለው ወደ ገነቱ ይገቡ ዘንድ ሰውነታቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፥ የእሪያንም ሥጋ አስጸያፊ ነገርንም አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 18ሥራቸውንና አሳባቸውን አውቄአለሁና፥ አሕዛብንና ልሳትን ሁሉ የምሰበስብበት ጊዜ ይደርሳል፥ እነርሱም ይመጣሉ ክብሬንም ያያሉ። 19በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ ወደ ፉጥ ወደ ሉድ ወደ ሞሳሕ ወደ ቶቤል ወደ ያዋን በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፥ በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ። 20የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁም ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር። 21ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 22እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 23እንዲህ ይሆናል፥ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 24ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፥ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፥ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 66: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ