“ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? አንቺም ከብዙ እረኞች ጋር አመንዝረሻል፤ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። ዐይኖችሽን አቅንተሽ አንሺ፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ እንዳለም ተመልከች። እንደ ምድረ በዳ ቍራዎች በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ በዝሙትሽና በክፋትሽ ምድሪቱን አርክሰሻታልና። ለጕስቍልናሽ ከብዙዎች እረኞች ጋር ኖርሽ የአመንዝራም ሴት ፊት ነበረብሽ፥ በሁሉም ዘንድ ያለ ኀፍረት ሄድሽ። ስለዚህ የመከርና የበልግ ዝናም ተከለከለ። አሁንም፦ እንደ ጌታሽና እንደ አባትሽ፥ እንደ ልጅነት ባልሽም አልጠራሽኝምን? ቍጣው ለዘለዓለም ይኖራልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን? እነሆ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፤ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገር አደረግሽ።” እግዚአብሔርም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፥ “ከዳተኛዪቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ፥ ወደ ለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች፤ በዚያም አመነዘረች። ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ፦ ወደ እኔ ተመለሽ አልኋት፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅቷ ይሁዳም አየች። ከዳተኛዪቱም እስራኤል እንዳመነዘረች አየሁ፤ የፍችዋንም ደብዳቤ በእጅዋ ሰጥቼ ሰደድኋት፤ ጎስቋላ እኅቷ ይሁዳ ግን በዚያ አልፈራችም፤ እርስዋም ደግሞ ሄዳ አመነዘረች። ዝሙቷም ከንቱ ሆነ፤ እርስዋም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። በዚህም ሁሉ ከዳተኛዪቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ከጎስቋላዋ ይሁዳ ይልቅ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ራስዋን አጸደቀች። ሂድና ይህን ቃል ወደ ሰሜን ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ሆይ! ወደ እኔ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ መሓሪ ነኝና፥ ለዘለዓለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላጸናም፥” ይላል እግዚአብሔር። በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኀጢአትሽን ብቻ ዕወቂ ይላል እግዚአብሔር። ከዳተኞች ልጆች ሆይ! እኔ እገዛችኋለሁና ተመለሱ፤ ይላል እግዚአብሔር። አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፤ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤ እንደ ልቤም የሚሆኑ ጠባቂዎችን እሰጣችኋለሁ፤ በዕውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል። “በበዛችሁ ጊዜ፥ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥” ይላል እግዚአብሔር፤ በዚያ ዘመን፦ የእስራኤል ቅዱስ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት እነኋት አይሉም፤ በልባቸውም አያስቧትም፤ በአፋቸውም አይጠሯትም፤ ከእንግዲህ ወዲህም አይሿትም። ያንጊዜም ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፤ አሕዛብም ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።
ትንቢተ ኤርምያስ 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 3:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች