እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው፦ ከፍርሃት፣ ከጭንቀትና ከግራ መጋባት ጋር መጋፈጥናሙና
“የእግዚአብሔርን መልካምነት እናያለን. . .”
በዙሪያችን እየተፈጠረ ያለውን ማወቅ ራሳችንን ለመጠበቅ የሚጠቅም ቢሆንም፣ በፍርሃት እንዳንዋጥ መጠንቀቅ ይኖረብናል። ትኩረታችንን ግን ምን ላይ እንደሆነ ማስተዋል አለብን።
ዳዊት በመዝሙር 27 እኛ ያለንበት ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን “እግዚአብሔር ብርሃንኔና መድሀኒቴ ነው የሚያስፈራኝ ማነው” ሲል እናየዋለን። እንዲህ ዓይነት ንግግር በኛ ቋንቋ ‘ዘራፍ’ እንደማለት ነው።
ዳዊት በፍርሃት ተውጦ ሲዋጋ ወይንም ሲገስፅ አናየውም፥ ይልቁን ትኩረቱን ሁሉ በትክክለኛው ስፍራ አኖረ። ቁጥር 4 ላይ “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኩት እሷንም እሻለሁ . . . በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፣ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።" እነዚህ በደማቅ የተፃፉት ቃላት ትኩረት በሚለው ቃል ልንተካቸው እንችላለን። ዳዊት ፍርሀትን ያላስተናገደበት ምክንያት ትኩረቱን በዙሪያው በተፈጠረው ቀውስ ላይ ስላላደረገው ነው። ትኩረቱን በሙሉ በአምላኩ መልካምነትና ታማኝነት ላይ በማድረጉ ፍርሃትን መዋጋት ችሏል።
በዚህ ምክንያት ቁጥር 3 ላይ ልዩ ነገር ሲፈጠር እናያለን ". . . በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሰዋሁ፥ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ እዘምርለታለሁ”። ዳዊት በጠላቶቹ ተከብቦ ማምለክ ጀመረ፤ እግዚአብሔርን ያየ ሰው የሚሰጠው ምላሽ ይህ ነውና።
አምልኮ ሰማያትን ይከፍታል። ሰማያት ሲከፈቱልን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እና አላማ የማየት ዕድል ይሰጠናል። ለዚህም ነው በቁጥር 13 ዳዊት “የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር አይ ዘንድ አምናለሁ” የሚለው። ተስፋ በሚያስቆርጥ ጊዜ እንኳን ዳዊት በአምልኮ ስለነበር እግዚአብሔር ‘ፍጻሜና ተስፋ ይሰጠው ዘንድ የሰላም አሳብ’ እንዳለው ማየት ችሏል። ኤር 29:11
የሕይወት ተዛምዶ
በዚህ ወቅት ምን እንደምሰማ፣ እንዴት እንደምሰማና ምን ያህል እንደምሰማ እንዴት ልጠንቀቅ?
ፀሎት
ጌታ ሆይ፣ ከምንም እና ከማንም በላይ ቀልቤን እንድታቀና፣ ፍርሃት ሁሉ ከውስጤ እንዲወገድ እለምንሃለሁ። በእምነት መበርታት እንድችል ለእኔ፣ ለቤተሰቤ እና ለምድሬ ያለህን መልካም ሃሳብ እንድታሳየኝ እለምንሃለሁ።
ቅዱሳት መጻሕፍት
ስለዚህ እቅድ
በዚህ የ6 ቀን ጥናት ውስጥ ፍርሃት፣ ግራ መጋባትና ጭንቀትን ለማስወገድ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር መኖር ምን ያህል ማድረግ እንደሚችል እናያለን። ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በማሳለፍና ከቃሉ በመማር እነዚህን ተግዳሮቶች እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል፣ ትኩረታችንን እንዴት እንደምናስተካክልና አስተሳሰባችንን እንደምንለውጥ እናያለን።
More
ቤዛ ዓለም አቀፍ ሚኒስትሮችን ይህንን እቅድ ስላቀረቡልን እናመሰግናለን ፡፡ ለበለጠ መረጃ ይጎብኙ http://www.bezachurch.org |