ኤርምያስ 31:3-6
ኤርምያስ 31:3-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “በዘለዓለም ፍቅር ወድጄሃለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁህ። የእስራኤል ድንግል ሆይ እንደ ገና እሠራሻለሁ፤ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ትወጫለሽ። እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ተክሎችን ትተክሊአለሽ፤ የምትተክሉ ትከሉ፤ አመስግኑም፤ በኤፍሬም ተራሮች ላይ የሚከራከሩ፦ ተነሡ፤ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጠሩባት ቀን ትመጣለችና።”
ኤርምያስ 31:3-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ከሩቅ ተገለጠልን፤ እንዲህም አለን፤ “በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህም በርኅራኄ ሳብሁሽ። የእስራኤል ድንግል ሆይ፤ እንደ ገና ዐንጽሻለሁ፤ አንቺም ትታነጺአለሽ፤ ከበሮችሽንም እንደ ገና አንሥተሽ፣ ከሚፈነጥዙት ጋራ ትፈነድቂአለሽ። እንደ ገናም በሰማርያ ኰረብቶች ላይ፣ ወይን ትተክያለሽ፤ አትክልተኞች ይተክሏቸዋል፤ በፍሬውም ደስ ይላቸዋል። ጠባቂዎች፣ በኤፍሬም ኰረብቶች ላይ፣ ‘ኑ፤ ወደ ጽዮን፣ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ!’ ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣል።”
ኤርምያስ 31:3-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፥ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ። የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፥ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ። እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ቦታዎችን ትተክሊአለሽ፥ አትክልተኞች ይተክላሉ በፍሬውም ደስ ይላቸዋል። በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቆች፦ ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣልና።
ኤርምያስ 31:3-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እኔ ለእነርሱ ከሩቅ ተገለጥኩላቸው፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፥ እነሆ እናንተን ለዘለዓለም ወደድኳችሁ፤ ዘለዓለማዊ ቸርነቴም ለእናንተ የጸና ይሆናል። ሕዝቤ እስራኤል ሆይ፥ እንደገና ትገነባላችሁ፤ ትገነቢአለሽም፥ እንደገና ከበሮ ትይዢአለሽ፤ ከሚደሰቱት ጋር አብረሽ በመውጣት ትጨፍሪአለሽ። እንደገናም በሰማርያ ኰረብቶች ላይ ወይን ትተክዪአለሽ ፍሬውንም የደከሙበት ሰዎች ይበሉታል፤ ጠባቂዎች በኤፍሬም ተራራ ላይ ሆነው ‘ኑ አምላካችን እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጽዮን እንሂድ’ የሚሉበት ጊዜ ይመጣል።”
ኤርምያስ 31:3-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ “በዘለዓለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በጽኑ ፍቅር ሳብሁሽ። የእስራኤል ድንግል ሆይ! እንደገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ሐሤት በሚያደርጉ ዘፋኞች ሽብሸባ እያሸበሸብሽ ትወጫለሽ። እንደገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ ወይንን በወይን እርሻዎች ትተክዪአለሽ፤ አትክልተኞች ይተክላሉ እነርሱም በፍሬው ይደሰታሉ። በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቂዎች፦ ‘ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ ጌታ እንውጣ’ ብለው የሚጣሩበት ቀን ይመጣልና።”