የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 31

31
የእስራኤል ሕዝብ ወደ አገራቸው መመለስ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የእስራኤል ነገዶች ሁሉ አምላክ የምሆንበትና እነርሱም ሕዝቤ የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል፤ 2እስራኤል ዕረፍትን ለማግኘት ወደ ፊት በመጣ ጊዜ ከጦርነት የተረፉት በምድረ በዳ የእኔን የእግዚአብሔርን ምሕረት ያገኛሉ። 3እኔ ለእነርሱ ከሩቅ ተገለጥኩላቸው፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፥ እነሆ እናንተን ለዘለዓለም ወደድኳችሁ፤ ዘለዓለማዊ ቸርነቴም ለእናንተ የጸና ይሆናል። 4ሕዝቤ እስራኤል ሆይ፥ እንደገና ትገነባላችሁ፤ ትገነቢአለሽም፥ እንደገና ከበሮ ትይዢአለሽ፤ ከሚደሰቱት ጋር አብረሽ በመውጣት ትጨፍሪአለሽ። 5እንደገናም በሰማርያ ኰረብቶች ላይ ወይን ትተክዪአለሽ ፍሬውንም የደከሙበት ሰዎች ይበሉታል፤ 6ጠባቂዎች በኤፍሬም ተራራ ላይ ሆነው ‘ኑ አምላካችን እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጽዮን እንሂድ’ የሚሉበት ጊዜ ይመጣል።”
7እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ከሕዝቦች ሁሉ ስለምትበልጥ ስለ እስራኤል በደስታ ዘምሩ፤
‘እግዚአብሔር ሕዝቡን አድኖአል፤
በእስራኤል ምድር የቀሩትን ሁሉ ተቤዥቶአል’
እያላችሁ የምስጋና መዝሙር አቅርቡ።”
8“እኔ ከሰሜን አመጣቸዋለሁ፤
ከምድር ዳርቻም እሰበስባቸዋለሁ፤
ዕውሮች፤ አንካሶች፥ ነፍሰጡሮችና በምጥ የተያዙ ሴቶች ሁሉ
ከእነርሱ ጋር አብረው ይመጣሉ፤
ታላቅ ሕዝብ ሆነው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ፤
9እኔ ወደ አገራቸው ስመራቸው
ሕዝቤ ከደስታ የተነሣ እያለቀሱና እየጸለዩ ይመለሳሉ።
በማይሰናከሉበት የተስተካከለ መንገድ
ወደ ጥሩ ውሃ ምንጭ እመራቸዋለሁ።
እኔ ለእስራኤል አባት ነኝ፤
ኤፍሬምም የበኲር ልጄ ነው።”
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሕዝቦች ሆይ! አድምጡኝ፤
በሩቅ ጠረፎችም ቃሌን ዐውጁ፤
እኔ ሕዝቤን በትኜ ነበር፤
አሁን ግን እሰበስባቸዋለሁ፤
እረኛ መንጋውን እንደሚጠብቅም እጠብቃቸዋለሁ።
11እኔ የእስራኤልን ሕዝብ ነጻ አውጥቼአቸዋለሁ፤
ከኀያል መንግሥትም እጅ በመታደግ አድኛቸዋለሁ፤
12ስለዚህም ተመልሰው መጥተው በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤
በምሰጣቸውም የእህል፥ የወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥
የበግና የቀንድ ከብት በረከት ሁሉ ተድላ ደስታ ያደርጋሉ፤
በቂ ውሃ እንዳገኘች የተክል ቦታ ይሆናሉ፤
ከእንግዲህ ወዲያም አያዝኑም።
13ልጃገረዶቻቸውም በደስታ ይጨፍራሉ፤
ወንዶች ወጣቶችና ሽማግሌዎችም ደስ ይላቸዋል፤
አጽናናቸዋለሁ፤ ለቅሶአቸውን ወደ ደስታ፥
ሐዘናቸውንም ወደ ሐሴት እለውጣለሁ፤
14ካህናቱን በምድሪቱ በረከት አጠግባቸዋለሁ፤
ለሕዝቤም ቸርነቴን አትረፈርፍላቸዋለሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
የእግዚአብሔር ምሕረት በእስራኤል ላይ
15እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የዋይታና የመራራ ለቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤
ራሔል ስለ ልጆችዋ ታለቅሳለች፤
ልጆችዋ በሕይወት ስለሌሉ መጽናናትን እምቢ አለች። #ዘፍ. 35፥16-19፤ ማቴ. 2፥18።
16ለቅሶአችሁን አቁማችሁ እንባችሁን ጥረጉ፤
ስለ ልጆቻችሁ ያደረጋችኹት ነገር ሁሉ ያለ ዋጋ አይቀርም፤
እነርሱ ከጠላት አገር ተመልሰው ይመጣሉ።
17ልጆቻችሁ ወደ አገራቸው ተመልሰው ስለሚመጡ፥
የወደፊት ተስፋ አላችሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
18“የእስራኤል ሕዝብ በሐዘን እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፤
‘እግዚአብሔር ሆይ! እኛ እንዳልተገራ ወይፈን ነበርን፤
አንተ ግን መታዘዝን አስተማርከን፤
አንተ አምላካችን ስለ ሆንክ
አሁንም ወደ አንተ ወደ አምላካችን መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን።
19ከአንተ ርቀን ብንሄድም እንኳ አሁን ንስሓ ገብተናል፤
በዕፍረትና በጸጸት ራሳችንን ዝቅ አድርገን ደረታችንን እንመታለን፤
በወጣትነት ዘመናችን ለፈጸምነው ኃጢአት
ራሳችንን እንወቅሳለን።’
20“እስራኤል ሆይ! እናንተ የተወደዳችሁ ልጆቼ ናችሁ፤
ከሁሉ አስበልጬ የምወዳችሁ አይደለምን?
ምሕረት አደርግላችሁ ዘንድ ወደ እኔ ላቀርባችሁ እፈቅዳለሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
21ለራሳችሁ የመንገድ ምልክቶችን አድርጉ፤
መንገድንም የሚመሩ ዐምዶችን ትከሉ፤
የሄዳችሁበትን ዐውራ ጐዳና አተኲራችሁ ተመልከቱ፤
ሕዝቤ እስራኤል ሆይ!
ወደ እነዚህ ከተሞቻችሁ ተመለሱ።
22እናንተ እምነት የጐደላችሁ ሕዝብ፥
እስከ መቼ ታመነታላችሁ?
እኔ እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገርን ፈጥሬአለሁ፤
ይኸውም ሴት ለወንድ ትከላከላለች።
ልዩ የሆነ አዲስ ነገር ፈጥሬአለሁ።”
የእግዚአብሔር ሕዝብ የወደፊት ብልጽግና
23የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡን ወደ አገራቸው በመለስኩ ጊዜ በይሁዳና በከተሞቹ እንደገና ‘አንቺ የእውነት ማደሪያ የሆንሽ ቅድስት ተራራ እግዚአብሔር ይባርክሽ’ ይላሉ። 24‘ይሁዳና ከተሞቹ ሁሉ የሕዝብ መኖሪያ ይሆናሉ፤ ምድርን የሚያርሱ ገበሬዎችና መንጋን የሚጠብቁ እረኞች በዚያ ይገኛሉ፤ 25የደከሙትን ሁሉ ኀይላቸው እንዲታደስ አደርጋለሁ፤ በረሀብ ዝለው የነበሩትንም ምግብ በመስጠት አጠግባቸዋለሁ፤ 26ስለዚህም በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ‘ተኝተን ስንነቃ ታደስን’ ይላሉ።
27“እኔ እግዚአብሔር የእስራኤልንና የይሁዳን ምድር በሕዝብና በእንስሶች የምሞላበት ጊዜ ይመጣል። 28እነርሱን ለመንቀልና ለማፍረስ፥ ለመገለባበጥና ለማጥፋት፥ ለመደምሰስም እከታተል የነበርኩትን ያኽል፥ እነርሱን እንደገና ለመትከልና ለማነጽም እከታተላለሁ። 29በዚያ ዘመን፥ ‘አባቶች የበሉት ጎምዛዛ የሆነ የወይን ፍሬ፥
የልጆችን ጥርስ አጠረሰ’ እየተባለ
የሚነገረው ምሳሌ ይቀራል። #ሕዝ. 18፥2።
30ይህ መሆኑ ቀርቶ ጎምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሰው ሁሉ የገዛ ራሱን ጥርስ ብቻ ያጠርሳል፤ እያንዳንዱም በገዛ ራሱ ኃጢአት ይሞታል።”
31እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ከእስራኤል ሕዝብና ከይሁዳ ሕዝብ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል፤#ማቴ. 26፥28፤ ማር. 14፥24፤ ሉቃ. 22፥20፤ 1ቆሮ. 11፥25፤ 2ቆሮ. 3፥6። #ዕብ. 8፥8-12። 32ይህም ቃል ኪዳን እነርሱን ከግብጽ ለማውጣት እጃቸውን በያዝኩ ጊዜ እንደ ገባሁት ቃል ኪዳን ያለ አይደለም፤ እኔ አምላካቸው ብሆንም እንኳ እነርሱ ቃል ኪዳኔን አልጠበቁም፤ እኔም ችላ አልኳቸው፤ 33እነሆ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ #ዕብ. 10፥16። 34ከእንግዲህ ወዲህ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ ባልንጀራውንም ሆነ ወንድሙን የሚያስተምር ማንም አይኖርም፤ ከትልቁ ጀምሮ እስከ ትንሹ ሁሉም ያውቁኛል፤ በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም አላስታውስባቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” #ዕብ. 10፥17።
35ፀሐይን በቀን እንዲያበራ የሚያደርገው፥
ጨረቃና ከዋክብት በሌሊት እንዲያበሩ ሥርዓትን የወሰነላቸው፥ ባሕሩን በማዕበል እንዲናወጥ የሚቀሰቅሰው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል
ስሙም የሠራዊት አምላክ ነው።
36የተፈጥሮ ሥርዓት ጸንቶ እስከ ኖረ ድረስ
እስራኤል በፊቱ ሕዝብ ሆና የምትኖር መሆንዋን የሚገልጥ ተስፋ ይሰጣል፤
37እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን በሠሩት በደል ምክንያት ይጥላቸዋል ማለት የሚቻለው
የሰማይ ስፋቱ ተለክቶ፥
የምድርም መሠረቶች ሁሉ ተመርምረው ለመታወቅ ቢችሉ ብቻ ነው።
እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።
38እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከሐናንኤል መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ እስከ ማእዘኑ የቅጽር በር ድረስ ኢየሩሳሌም የእኔ ከተማ ሆና የምትታነጽበት ጊዜ ይመጣል። 39የወሰኑም መስመር ከማእዘኑ ቅጥር በር ወደ ጋሬብ ኰረብታ ይሄድና ወደ ጎዓ ይዞራል። 40በድንና ዐመድ የሚጣልበት መላው ሸለቆ በምሥራቅ በኩል እስከ ፈረስ በር ድረስ እንኳ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከተማይቱም እንደገና ከቶ አትፈርስም፤ አትደመሰስምም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ