ትንቢተ ኤርምያስ 32
32
ኤርምያስ መሬት መግዛቱ
1የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥረኛው ዓመት፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት እግዚአብሔር እኔን ኤርምያስን ተናገረኝ፤ #2ነገ. 25፥1-7። 2ያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ከበባ ያደረገበት ጊዜ ነበር፤ እኔም በዚያን ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ግቢ በሚገኘው በዘብ ጠባቂዎች ክፍል ውስጥ ተዘግቶብኝ ነበር፤ 3ንጉሥ ሴዴቅያስ እኔን በዚያ እስረኛ አድርጎ ያስቀመጠኝና የከሰሰኝ እግዚአብሔር የተናገረኝን የትንቢት ቃል ለእርሱ በማሳወቄ ሲሆን፥ እርሱም እንዲህ የሚል ነበር፥ “የባቢሎን ንጉሥ ይህችን ከተማ በኀይል እንዲይዝ ልፈቅድለት ነው፤ 4ንጉሥ ሴዴቅያስም ማምለጫ የለውም፤ እርሱ ለባቢሎን ንጉሥ ተላልፎ ይሰጣል፤ ንጉሡን ፊት ለፊት ያየዋል፤ በግሉም ያነጋግረዋል። 5ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ይወሰዳል፤ እኔ በሞት እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፤ ከባቢሎናውያን ጋር ለመዋጋት ቢሞክር እንኳ አይሳካለትም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
6እንደገናም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 7“አጐትህ የሻሉም ልጅ ሐናምኤል በብንያም ክፍል በዐናቶት የሚገኘውን መሬቱን እንድትገዛው ለመጠየቅ ወደ አንተ ይመጣል፤ የቅርብ ዘመድ ስለ ሆንክ ያን መሬት መግዛት የሚገባህ አንተ ነህ።” 8እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት ሐናምኤል ታስሬ ወዳለሁበት ወደ ዘብ ጠባቂዎች ክፍል መጥቶ “የመግዛት መብት ያንተ ስለ ሆነ መሬቴን ግዛ” አለኝ፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር እንደ ተናገረኝ ዐወቅሁ። 9መሬቱንም ከሐናምኤል ለመግዛት ገንዘቡን መዘንኩለት፤ የዋጋውም ልክ ወደ ሁለት ኪሎ የሚመዝን ብር ሆነ። 10የግዢውንም ውል ምስክሮች ባሉበት ፈርሜ አሸግሁት፤ ገንዘቡንም በሚዛን መዝኜ ሰጠሁት። 11ከዚያም አጠቃሎ ይዞ የታተመውንና ያልታተመውን የሽያጩን ውል ሁለት ግልባጭ ወስጄ፥ 12የማሕሴያ የልጅ ልጅ ለሆነው ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት፤ እነዚያን ግልባጮች የሰጠሁት በሐናምኤል፥ የሽያጩን ውል በፈረሙት ምስክሮችና በአደባባዩ ተቀምጠው በነበሩት ሰዎች ፊት ነው፤ 13በእነርሱም ሁሉ ፊት ባሮክን እንዲህ አልኩት፥ 14“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘የታሸገውንና ግልጥ የሆነውን ሁለቱንም የሽያጭ ውል ወረቀት ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ እንድታኖረውና ለብዙ ዘመን ተጠብቆ እንዲኖር አድርግ፤’ 15እንደገና በዚህች ምድር ቤቶችን፥ የእርሻ መሬቶችን፥ የወይን ተክል ቦታዎችን መግዛት የሚቻልበት ጊዜ ይመጣል ብሎአል።”
የኤርምያስ ጸሎት
16የሽያጩን ውል ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ከሰጠሁት በኋላ እኔ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦ 17“ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በታላቁ ሥልጣንህና ኀይልህ ሰማይና ምድርን ፈጥረሃል፤ ከቶም የሚሳንህ ነገር የለም፤ 18ለብዙ ሺህ ሕዝብ ዘለዓለማዊ ፍቅርህን አሳይተሃል፤ ይሁን እንጂ አባቶቻቸው በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ልጆቻቸውን ትቀጣለህ፤ አንተ ታላቅና ኀያል አምላክ ነህ፤ አንተ ሁሉን ቻይና ስምህም የሠራዊት ጌታ ነው፤ 19ዓላማህ ታላቅ ነው፤ ሥራህም ኀያል ነው፤ ሕዝቦች የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ ታያለህ፤ ለእያንዳንዱም ሰው እንደአካሄዱና እንደየሥራው ዋጋውን ትከፍላለህ። 20በቀድሞ ጊዜ በግብጽ ምድር ተአምራትንና አስደናቂ ነገሮችን አደረግህ፤ እስከ አሁንም ድረስ እነዚያን ድንቅ ሥራዎች በእስራኤል ሕዝብና በሌሎች ሰዎች መካከል ከማድረግ አልተቈጠብክም፤ ከዚህም የተነሣ በሁሉ ስፍራ ስምህ ገኗል። 21በተአምራትና በአስደናቂ ሁኔታ፥ በኀይልህና በታላቅነትህ፥ እንዲሁም በአስፈሪ ግርማህ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አወጣህ፥ 22ለቀድሞ አባቶቻቸውም በሰጠሃቸው ተስፋ መሠረት ይህችን ብልጽግና የሞላባት ለምለም ምድር አወረስካቸው። 23ነገር ግን ወደዚህች ምድር መጥተው ከወረሱአት በኋላ ለቃልህ መታዘዝንና በአስተማርካቸው ሕግ ጸንተው መኖርን እምቢ አሉ፤ ያዘዝካቸውንም ነገር ሁሉ አልፈጸሙም፤ ከዚህም የተነሣ ይህን ሁሉ ጥፋት አመጣህባቸው።
24“እነሆ ባቢሎናውያን ከተማይቱን ለመያዝ ዐፈር ቈልለው ዙሪያዋን በመክበብ ላይ ናቸው፤ ጦርነት፥ ራብና ቸነፈር ከተማይቱ በእነርሱ እጅ እንድትወድቅ ያደርጓታል፤ እነሆ አንተ የተናገርከው ሁሉ መድረሱን ታያለህ፤ 25ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ከተማይቱ በባቢሎናውያን ልትያዝ ተቃርባ ሳለ መሬቱን በምስክሮች ፊት እንድገዛ ያዘዝከኝ አንተ ነህ።”
26እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 27“የሰው ዘር ሁሉ አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከቶ ለእኔ የሚሳነኝ ነገር አለን? 28ይህችን ከተማ ለባቢሎናውያንና ለንጉሣቸው ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ይይዛታል። #2ነገ. 25፥1-11፤ 2ዜ.መ. 36፥17-21። 29ይህችን ከተማ የከበቡ ባቢሎናውያን መጥተው ያቃጥሉአታል፤ እንደዚሁም እኔን ለማስቈጣት በጣራዎቻቸው ላይ ለባዓል ጣዖት ዕጣን ያጥኑባቸው የነበሩትንና ለሌሎችም ጣዖቶች የመጠጥ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን ቤቶች ያቃጥላሉ። 30የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከክፉ አድራጎት በስተቀር ምንም ያደረጉት መልካም ነገር የለም። በተለየም የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው በሠሩት ጣዖት እኔን ከማስቈጣት በቀር ምንም የሠሩት ነገር የለም። 31ይህች ከተማ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝብዋ እጅግ ስላስቈጡኝ ከተማይቱን ለማጥፋት ወስኜአለሁ። 32የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ፥ የእነርሱ ነገሥታት፥ ባለሥልጣኖቻቸው፥ የእነርሱ ካህናትና ነቢያት በሚያደርጉአቸው ክፉ ነገሮች ሁሉ ቊጣዬን አነሣሥተዋል። 33እነርሱ እኔን ትተው ሄደዋል፤ ዘወትር በመደጋገም ባስተምራቸውም አልሰሙኝም፤ ተግሣጼንም አልተቀበሉም፤ 34ይልቁንም የስሜ መጠሪያ እንዲሆን በተሠራው መቅደሴ አጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቻቸውን በማቆም አርክሰውታል። #2ነገ. 23፥10፤ ኤር. 7፥30-31፤ 19፥1-6። 35ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ሞሌክ ለተባለው ጣዖት መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ በሄኖም ሸለቆ ውስጥ ለበዓል ጣዖት መሠዊያ ሠርተዋል፤ እኔ ይህን እንዲያደርጉ አላዘዝኳቸውም የይሁዳንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት ለመምራት ይህን ያደርጋሉ ብዬ አልጠበቅሁም ነበር።” #ዘሌ. 18፥21፤ 2ነገ. 23፥10፤ ኤር. 7፥31።
አስተማማኝ ተስፋ
36የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ኤርምያስ ሆይ! እነሆ ሕዝቡ ‘ይህችን ከተማ ጦርነት፥ ራብና ቸነፈር በባቢሎን ንጉሥ እጅ እንድትወድቅ ሊያደርጉአት ነው’ ይላሉ፤ እነሆ እኔ የምለውን ሌላ ነገር ደግሞ ስማ፤ 37እንደ እሳት በሚነደው ታላቅ ቊጣዬ የበተንኳቸውን ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች ሁሉ እንደገና ወደዚህ ቦታ እሰበስባቸዋለሁ፤ በሰላም እንዲኖሩም አደርጋለሁ። 38እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ 39አንድ ዓላማ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፤ ይኸውም ለእነርሱና ለልጆቻቸው ሁሉ መልካም ነገር እንዲሆንላቸው ዘወትር ያከብሩኝ ዘንድ ነው። 40ከእነርሱ ጋር የዘለዓለም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ለእነርሱ መልካም ነገር ከማድረግም አላቋርጥም፤ በእውነት እንዲፈሩኝ አደርጋለሁ። ከዚያም በኋላ ፊታቸውን ከእኔ ወደ ሌላ አይመልሱም። 41እኔም ለእነርሱ መልካም ነገር በማድረግ ደስ ይለኛል፤ እኔ በፈቃዴ በዚህች ምድር በእውነት እመሠርታቸዋለሁ።
42“በሕዝቡ ላይ ይህን ሁሉ ጥፋት እንዳመጣሁባቸው ሁሉ እንዲሁም ቃል የገባሁላቸውን መልካም ነገር እሰጣቸዋለሁ፤ 43‘ምድሪቱ ለባቢሎናውያን ስለ ተሰጠች ሰዎችም ሆኑ እንስሶች የማይኖሩባት ባድማ ትሆናለች’ ባላችኋት በዚህች ምድር የእርሻ መሬት መግዛትና መሸጥ እንደገና ይጀመራል። 44ሕዝቡ መሬት ይገዛሉ፤ ውሎች ተፈርመው በምስክሮች ፊት ይታተማሉ፤ ይህም ሁሉ በብንያም ክፍል በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉ መንደሮች፥ በይሁዳ ገጠር ከተሞች፥ በተራራማው አገር ከተሞች፥ በኮረብቶች ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ሁሉ ይፈጸማል። ሕዝቡ ሁሉ ወደ ምድራቸው ተመልሰው ንብረታቸውን እንዲረከቡ አደርጋለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 32: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997