የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 31

31
1በዚያን ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤል ማረፊያ ሊሻ በሄደ ጊዜ ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ። 3እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፥ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ። 4የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፥ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ። 5እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ቦታዎችን ትተክሊአለሽ፥ አትክልተኞች ይተክላሉ በፍሬውም ደስ ይላቸዋል። 6በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቆች፦ ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣልና።
7እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ስለ ያዕቆብ ደስ ይበላችሁ ስለ አሕዛብም አለቆች እልል በሉ፥ አውሩ፥ አመስግኑ፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን የእስራኤልን ቅሬታ አድኖአል በሉ። 8እነሆ፥ ከሰሜን አገር አመጣቸዋለሁ፥ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፥ በመካከላቸውም ዕውሩና አንካሳው ያረገዘችና የወለደችም በአንድነት፥ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ወደዚህ ይመለሳሉ። 9በልቅሶ ወጡ እኔም በማጽናናት አመጣቸዋለሁ፥ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስኬዳቸዋለሁ፥ በእርሱም አይሰናከሉም፥ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና።
10አሕዛብ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩና፦ እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፥ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል በሉ። 11እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶታል፥ ከበረቱበትም እጅ አድኖታል። 12ይመጣሉ በጽዮንም ተራራ እልል ይላሉ፥ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ይሰበሰባሉ፥ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አያዝኑም። 13በዚያን ጊዜም ድንግሊቱ በዘፈን ደስ ይላታል፥ ጐበዛዝቱና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፥ ልቅሶአቸውንም ወደ ደስታ እመልሳለሁ፥ አጽናናቸውማለሁ፥ ከኅዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ። 14የካህናቱንም ነፍስ በብዛት አረካታለሁ ሕዝቤም በጎነቴን ይጠግባል።
15እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። 16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምፅሽን ከልቅሶ ዓይንሽንም ከእንባ ከልክዪ፥ ለሥራሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። 17ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ልጆችሽም ወደ ዳርቻቸው ይመለሳሉ። 18ኤፍሬም፦ ቀጣኸኝ እኔም እንዳልተገራ ወይፈን ተቀጣሁ፥ አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ። 19ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፥ ከተገሠጽሁም በኋላ ጭኔን ጸፋሁ፥ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ፥ ተዋረድሁም ብሎ ሲያለቅስ ሰማሁ። 20በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ ነውን? ወይስ የተወደደ ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አስበዋለሁ፥ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
21ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዓምዶችን ትከዪ፥ ልብሽንም ወደ ሄድሽበት መንገድ ወደ ጥርጊያው አቅኚ፥ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ ተመለሺ፥ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ ተመለሺ። 22አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፥ እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሴት ወንድን ትከብባለች።
23የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ፦ የጽድቅ ማደሪያ ሆይ፥ የቅድስና ተራራ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ የሚልን ነገር እንደ ገና ይናገራሉ። 24በይሁዳ ከተሞችና በአገሩ ሁሉ ከገበሬዎችና መንጋን ይዘው ከሚዞሩ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ይገኛሉ። 25የደከመችውን ነፍስ አርክቻለሁና፥ ያዘነችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና። 26ከዚህም በኋላ ነቃሁ ተመለከትሁም፥ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆነልኝ።
27የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት በሰው ዘርና በእንስሳ ዘር የምዘራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 28እንዲህም ይሆናል፥ አፈርሳቸውና ክፉ አድርግባቸው ዘንድ እንደ ተጋሁባቸው፥ እንዲሁ እሠራቸውና እተክላቸው ዘንድ እተጋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 29በዚያ ዘመን ሰው ዳግመኛ እንዲህ አይልም፦ አባቶች ጨርቋ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፥ 30ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፥ መራራውን የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ ጥርሶቹ ይጠርሳሉ።
31እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ 32ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፥ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። 33ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 34እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፥ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።
35ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 36ይህ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያን ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ዘር በፊቴ ሕዝብ እንዳይሆን ለዘላለም ይቀራል። 37እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ በላይ ቢከነዳ፥ የምድርም መሠረት በታች ቢመረመር፥ በዚያን ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ የእስራኤልን ዘር ሁሉ እጥላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
38ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ከተማ ለእግዚአብሔር የሚሠራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 39የተለካበትም ገመድ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፥ ወደ ጎዓም ይዞራል። 40የሬሳም ሸለቆ ሁሉ የአመድም እርሻ ሁሉ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል እስካለው እስከ ፈረሰ በር ማዕዘን ድረስ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፥ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘላለም አይነቀልም አይፈርስምም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ