ትንቢተ ኤርምያስ 32
32
1በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በአሥረኛው ዓመት፥ በናቡከደነፆር በአሥራ ስምንተኛው ዓመት፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፥ ነቢዩም ኤርምያስ በይሁዳ ንጉሥ ቤት በነበረው በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ነበር። 3የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲህ ብሎ አስጠብቆት ነበርና፦ ስለ ምን እንዲህ ብለህ ትንቢት ትናገራለህ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ እርሱም ይይዛታል፥ 4የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ በእውነት በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፥ አፍ ለአፍም ይናገረዋል፥ ዓይኑም ዓይኑን ያያል እንጂ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፥ 5እርሱም ሴዴቅያስን ወደ ባቢሎን ያፈልሰዋል፥ እኔም እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ከከላዳውያን ጋር ብትዋጉ ምንም አትረቡም።
6ኤርምያስም እንዲህ አለ፦ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 7እነሆ፥ የአጐትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፦ ትገዛው ዘንድ መቤዠቱ የአንተ ነውና በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ ይልሃል። 8እንደ እግዚአብሔርም ቃል የአጐቴ ልጅ አናምኤል እኔ ወዳለሁበት ወደ ግዞቱ ቤት አደባባይ መጥቶ፦ በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን፥ እባክህ፥ ግዛ፥ ርስቱ የአንተ ነውና፥ መቤዠቱም የአንተ ነውና፥ ለአንተ ግዛው አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ አወቅሁ። 9በዓናቶትም ያለውን እርሻ ከአጐቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፥ አሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት። 10በውሉም ወረቀት ላይ ፈረምሁ አተምሁትም፥ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት። 11የታተመውንና የተከፈተውን የውል ወረቀት ወሰድሁ፥ 12የአጐቴም ልጅ አናምኤል፥ የውሉንም ወረቀት የፈረሙ ምስክሮች፥ በግዞትም ቤት አደባባይ የተቀመጡ አይሁድ ሁሉ እያዩ የውሉን ወረቀት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት። 13በፊታቸውም እንዲህ ብዬ ባሮክን አዘዝሁት፦ 14የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብዙ ቀን ይጠበቁ ዘንድ የታተመውንና የተከፈተውን ይህን የውል ወረከት ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው። 15የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰዎች በዚህች ምድር ቤትንና እርሻን የወይን ቦታንም እንደ ገና ይገዛሉ።
16ለኔርያ ልጅ ለባሮክም የውሉን ወረቀት ከሰጠሁት በኋላ፥ እንዲህ ብዬ ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፦ 17አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፥ ከአንተም የሚያቅት ነገር የለም። 18ለብዙ ሺህ ምሕረት ታደርጋለህ፥ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ብብት ትመልሳለህ፥ ስምህ ታላቅና ኃያል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። 19በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ ነህ፥ ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ትሰጥ ዘንድ ዓይኖችህ በአዳም ልጆች መንገድ ሁሉ ተገልጠዋል። 20እስከ ዛሬም ድረስ ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብጽ ምድር ደግሞም በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች መካከል አድርገሃል፥ እንደ ዛሬም ለአንተ ስም አድርገሃል። 21በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አወጣህ። 22ትሰጣቸውም ዘንድ ለአባቶቻቸው የማልህላቸውን ምድር፥ ወተትና ማርንም የምታፈስሰውን ምድር፥ ሰጠሃቸው፥ 23እነርሱም ገብተው ወረሱአት፥ ነገር ግን ቃልህን አልሰሙም በሕግህም አልሄዱም፥ ያደርጉም ዘንድ ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፥ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው። 24እነሆ የአፈር ድልድል፥ ሊይዙአትም እስከ ከተማይቱ ድረስ ቀርበዋል፥ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም የተነሣ ከተማይቱ ለሚዋጉአት ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች፥ የተናገርኸውም ሆኖአል፥ እነሆም፥ አንተ ታየዋለህ። 25አንተም፥ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፦ እርሻውን በብር ግዛ ምስክሮችንም ጥራ አልኸኝ፥ ከተማይቱ ግን ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች።
26የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 27እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፥ 28በውኑ እኔን የሚያቅተኝ ነገር አለን? ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ይይዛታል። 29ይህችን ከተማ የሚወጉ ከለዳውያን መጥተው በእሳት ያነድዱአታል፥ ያስቈጡኝም ዘንድ በሰገነታቸው ላይ ለበኣል ካጠኑባቸው፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን ካፈሰሱባቸው ቤቶች ጋር ያቃጥሉአታል። 30የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች ከታናሽነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ ነገርን ብቻ አድርገዋልና፥ የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደረጉምና። 31ከፊቴ አስወግዳት ዘንድ ይህች ከተማ ከሠሩአት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቍጣዬንና መዓቴን ለማነሣሣት ሆናለችና፥ 32ይህም እኔን ያስቈጡኝ ዘንድ፥ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነቢያቶቻቸውም የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ፥ ስላደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው። 33ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ፥ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ሳስተምራቸው ተግሣጽን ይቀበሉ ዘንድ አልሰሙም። 34ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ውስጥ ርኵሰታቸውን አኖሩ። 35ይሁዳን ወደ ኃጢአት እንዲያገቡት፥ ይህንን ርኵሰት ያደርጉ ዘንድ፥ እኔ ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን ነገር፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ በእሳት ያሳልፉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን የበኣልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠሩ።
36አሁን እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አንተ ስለ እርስዋ፦ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ተሰጥታለች ስለምትላት ከተማ እንዲህ ይላል፦ 37እነሆ፥ በቍጣዬና በመዓቴ በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት አገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፥ ተዘልለውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፥ 38እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 39ለእነርሱም ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘላለም እንዲፈሩኝ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ። 40ለእነርሱም ከማደርገው በጎነት አልመለስም ስል፥ ከእነርሱ ጋር የዘላለምን ቃል ኪዳን እገባለሁ፥ ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ። 41ለእነርሱም መልካምን በማድረግ ደስ ይለኛል በእውነትም በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ። 42እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፥ እንዲሁ የተናገርሁላቸውን በጎነት ሁሉ አመጣላቸዋለሁ። 43እናንተም፦ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት፥ ለከለዳውያንም እጅ ተሰጥታለች በምትሉአት ምድር እርሻን ይገዛሉ። 44ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና በብንያም አገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በደጋውም ባሉ ከተሞች በቈላውም ባሉ ከተሞች በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ በውሉም ወረቀት ፈርመው ያትማሉ ምስክሮችንም ይጠራሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 32: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ