የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኤርምያስ 31

31
1“በዚያ ዘመን” ይላል እግዚአብሔር፤ “ለእስራኤል ነገድ ሁሉ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።”
2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ፣
በምድረ በዳ ሞገስን ያገኛል፤
እኔም ለእስራኤል ዕረፍት ለመስጠት እመጣለሁ።”
3 እግዚአብሔር ከሩቅ#31፥3 ወይም እግዚአብሔር ከጥንት ወይም ከቀድሞ ተገለጠልን ተገለጠልን፤ እንዲህም አለን፤
“በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ፤
ስለዚህም በርኅራኄ ሳብሁሽ።
4የእስራኤል ድንግል ሆይ፤ እንደ ገና ዐንጽሻለሁ፤
አንቺም ትታነጺአለሽ፤
ከበሮችሽንም እንደ ገና አንሥተሽ፣
ከሚፈነጥዙት ጋር ትፈነድቂአለሽ።
5እንደ ገናም በሰማርያ ኰረብቶች ላይ፣
ወይን ትተክያለሽ፤
አትክልተኞች ይተክሏቸዋል፤
በፍሬውም ደስ ይላቸዋል።
6ጠባቂዎች፣ በኤፍሬም ኰረብቶች ላይ፣
‘ኑ፤ ወደ ጽዮን፣
ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ!’
ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣል።”
7 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ስለ ያዕቆብ በደስታ ዘምሩ፤
ስለ ሕዝቦች አለቃ እልል በሉ፤
ምስጋናችሁን አሰሙ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ የእስራኤልን ቅሬታ፣
ሕዝብህን አድን’ በሉ።
8እነሆ፤ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ፤
ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤
በመካከላቸውም ዕውሮችና ዐንካሶች፣
ነፍሰ ጡርና በምጥ ላይ ያሉ ሴቶች ይገኛሉ፤
ታላቅም ሕዝብ ሆነው ይመለሳሉ።
9እያለቀሱ ይመጣሉ፤
እያጽናናሁ አመጣቸዋለሁ፤
እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፣
ኤፍሬም በኵር ልጄ ነውና፣
በውሃ ምንጭ ዳር፣
በማይሰናከሉበት ቀና መንገድ እመራቸዋለሁ።
10“ሕዝቦች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤
ሩቅ ባሉ የባሕር ጠረፎችም፣
‘እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤
መንጋውንም እንደ እረኛ ይጠብቃል’ ብላችሁ ዐውጁ።
11 እግዚአብሔር ያዕቆብን ይዋጀዋልና፤
ከእርሱም ከሚበረቱት እጅ ይታደገዋልና።
12መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤
በእግዚአብሔርም ልግስና፣
በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣
በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤
ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤
ከእንግዲህም አያዝኑም።
13ኰረዶች ይዘፍናሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤
ጐረምሶችና ሽማግሌዎችም ይፈነጥዛሉ፤
ልቅሷቸውን ወደ ደስታ እለውጣለሁ፤
ከሐዘናቸውም አጽናናቸዋለሁ፤ ደስታንም እሰጣቸዋለሁ።
14ካህናቱን አትረፍርፌ እባርካለሁ፤
ሕዝቤም በልግስናዬ ይጠግባል፤”
ይላል እግዚአብሔር
15 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ዋይታና መራራ ልቅሶ
ከራማ ተሰማ፤
ልጆቿ የሉምና፣
ራሔል አለቀሰች፤
መጽናናትም እንቢ አለች።”
16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ድምፅሽን ከልቅሶ፣
ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤
ድካምሽ ያለ ዋጋ አይቀርምና፤”
ይላል እግዚአብሔር
“ከጠላት ምድር ይመለሳሉ፤
17ስለዚህ ወደ ፊት ተስፋ አለሽ”
ይላል እግዚአብሔር
“ልጆችሽ ወደ ገዛ ምድራቸው ይመለሳሉ።
18“የኤፍሬምን የሲቃ እንጕርጕሮ በርግጥ ሰምቻለሁ፤
‘እንዳልተገራ ወይፈን ቀጣኸኝ፤
እኔም ተቀጣሁ።
አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና፣
መልሰኝ፤ እኔም እመለሳለሁ።
19ከአንተ ከራቅሁ በኋላ፣
ተመልሼ ተጸጸትሁ፤
ባስተዋልሁም ጊዜ፣
ጭኔን መታሁ፤
የወጣትነት ውርደቴን ተሸክሜአለሁና
ዐፈርሁ፤ ቀለልሁም።’
20ኤፍሬም የምወድደው፣
ደስም የምሰኝበት ልጄ አይደለምን?
ብዙ ጊዜ ተቃውሜው ብናገርም፣
መልሼ ስለ እርሱ ዐስባለሁ፤
አንጀቴ ይላወሳል፤
በታላቅ ርኅራኄም እራራለታለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር
21“የጐዳና ምልክት አቁሚ፤
መንገድ አመልካች ትከዪ፤
የምትሄጂበትን መንገድ፣
አውራ ጐዳናውን አስተውዪ፤
ድንግሊቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሺ፤
ወደ ከተሞችሽም ግቢ።
22አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፤
እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ?
እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ይፈጥራል፤
ሴት በወንድ ላይ ከበባ ታደርጋለች።#31፥22 ወይም መፈለግ ትጀምራለች ወይም መጠበቅ ትጀምራለች
23የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምርኳቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣#31፥23 ወይም ዕድል ፈንታቸውን በመለስሁላቸው እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ። 24ገበሬዎችና ዘላን ከብት አርቢዎች በይሁዳና በከተሞቿ በአንድነት ይኖራሉ። 25የዛለችውን ነፍስ ዐድሳለሁ፤ የደከመችውንም አበረታለሁ።”
26በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ነቅቼ ዙሪያዬን ተመለከትሁ፤ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆኖልኝ ነበር።
27“እነሆ፤ የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት” ይላል እግዚአብሔር፤ “በሰውና በእንስሳት ዘር የምሞላበት ጊዜ ይመጣል፤ 28ልነቅላቸውና ላፈርሳቸው፣ ልገለብጣቸውና ላጠፋቸው፣ መከራም ላመጣባቸው እንደ ተጋሁ ሁሉ፣ ላንጻቸውና ልተክላቸው ደግሞ እተጋለሁ” ይላል እግዚአብሔር29“በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ፣
“ ‘አባቶች በበሉት ጐምዛዛ የወይን ፍሬ፣
የልጆች ጥርስ ጠረሰ’
የሚለውን ምሳሌ አይናገሩም። 30ነገር ግን፣ እያንዳንዱ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል፤ ጐምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ የራሱን ጥርስ ይጠርሳል።
31“ከእስራኤል ቤትና፣
ከይሁዳ ቤት ጋር” ይላል እግዚአብሔር
“አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት፣
ጊዜ ይመጣል።
32ከግብፅ አወጣቸው ዘንድ፣
እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣
ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን
አይደለም፤#31፥32 የዕብራይስጡ፣ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርሰት ትርጕሞች እኔም ዘወር አልሁባቸው ይላሉ።
የእነርሱ ባል#31፥32 31፥32 ወይም የእነርሱ ጌታ ሆኜ ሳለሁ፣
ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና።”
ይላል እግዚአብሔር
33“ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣
ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር
“ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤
በልባቸውም እጽፈዋለሁ።
እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤
እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።
34ከእንግዲህ ማንም ሰው ባልንጀራውን፣
ወይም ወንድሙን፣ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤
ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፣
ሁሉም እኔን ያውቁኛልና፤”
ይላል እግዚአብሔር
“በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤
ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም።”
35በቀን እንድታበራ፣
ፀሓይን የመደበ፣
በሌሊት እንዲያበሩ፣
ጨረቃንና ከዋክብትን ያዘዛቸው፣
የሞገዱ ድምፅ እንዲተምም፣
ባሕሩን የሚያናውጥ፣
ስሙ የሰራዊት ጌታ የሆነ፣
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
36“ይህ ሥርዐት በፊቴ ከተሻረ፣”
ይላል እግዚአብሔር
“በዚያ ጊዜ የእስራኤልም ዘር በፊቴ፣
መንግሥት መሆኑ ለዘላለም ይቀራል።”
37 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በላይ ያሉትን ሰማያትን መለካት፣
በታችም ያሉትን የምድር መሠረቶች መመርመር ከተቻለ፣
በዚያ ጊዜ የእስራኤልን ዘር ሁሉ፣
ስላደረጉት ነገር ሁሉ እጥላቸዋለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር
38“እነሆ ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማእዘኑ በር ድረስ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ይህች ከተማ ለእግዚአብሔር የምትሠራበት ጊዜ ይመጣል፤ 39መለኪያ ገመዱም ከዚያ ጀምሮ በቀጥታ ወደ ጋሬብ ኰረብታ፣ ዐልፎም ወደ ጎዓ ይዘረጋል። 40ሬሳና ዐመድ የሚጣልበት ሸለቆ በሙሉ፣ በምሥራቅ በኩል የቄድሮንን ሸለቆ ይዞ እስከ ፈረስ በር የሚደርሰው ደልዳላ ቦታ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ከተማዪቱ አትነቀልም፤ አትፈርስምም።”

Currently Selected:

ኤርምያስ 31: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ