የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 31

31
ምርኮኞቹ በደስታ ስለ መመለሳቸው
1በዚያን ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 2ጌታ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል ማረፊያ ሊሻ በሄደ ጊዜ ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ። 3ጌታም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ “በዘለዓለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በጽኑ ፍቅር ሳብሁሽ። 4የእስራኤል ድንግል ሆይ! እንደገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ሐሤት በሚያደርጉ ዘፋኞች ሽብሸባ እያሸበሸብሽ ትወጫለሽ። 5እንደገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ ወይንን በወይን እርሻዎች ትተክዪአለሽ፤ አትክልተኞች ይተክላሉ እነርሱም በፍሬው ይደሰታሉ። 6በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቂዎች፦ ‘ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ ጌታ እንውጣ’ ብለው የሚጣሩበት ቀን ይመጣልና።”
7ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ስለ ያዕቆብ በደስታ ዘምሩ ስለ አሕዛብም አለቆች እልል በሉ፤ አውጁ፥ አመስግኑ፦ ጌታ ሆይ! ሕዝብህን የእስራኤልን ትሩፍ አድን በሉ። 8እነሆ፥ ከሰሜን አገር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤ በመካከላቸውም ዓይነ ስውርና አንካሳው ያረገዘችና ምጥ የያዛትም በአንድነት ይሆናሉ፤ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ወደዚህ ይመለሳሉ። 9በልቅሶ ይወጣሉ፤ እኔንም በመማፀናቸው እየመራሁ እመልሳቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስኬዳቸዋለሁ፤ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኩሬ ነውና።
10አሕዛብ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፥ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውጁ፦ “እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፥ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል” በሉ። 11ጌታ ያዕቆብን ተቤዥቶታል፥ ከበረታበትም እጅ አድኖታል። 12ይመጣሉ በጽዮንም ተራራ ላይ ሆነው እልል ይላሉ፤ ስለ ጌታም በጎነቱ፥ ስለ እህሉና ስለ ወይን ጠጁ፥ ስለ ዘይቱም፥ ስለ በጎቹና ስለ ከብቶቹ በሐሤት ይሞላሉ፤ ነፍሳቸውም ውኃ ጠጥታ እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አያዝኑም። 13በዚያን ጊዜም ድንግሊቱ በሽብሸባ ትደሰታለች፥ ጉልማሶቹና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ ልቅሶአቸውንም ወደ ደስታ እለውጣለሁ፥ አጽናናቸዋለሁም፥ ከኀዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ። 14የካህናቱንም ነፍስ በብዛት አረካታለሁ ሕዝቤም በጎነቴን ይጠግባል፥ ይላል ጌታ።
15 # ዘፍ. 35፥16-19፤ ማቴ. 2፥18። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች።” 16ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ድምፅሽን ከልቅሶ ዓይንሽንም ከእንባ ከልክዪ፤ ለሥራሽ የሚከፈልሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ፥ ይላል ጌታ። 17ለወደፊት ላለሽ ጊዜ ተስፋ አለሽ፥ ይላል ጌታ፥ ልጆችሽም ወደ ግዛታቸው ይመለሳሉ። 18በእውነት ኤፍሬም ሲያለቅስ ሰማሁ፦ ‘ቀጣኸኝ እኔም እንዳልተገራ ወይፈን ተቀጣሁ፤ አንተ ጌታ አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ። 19ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፥ ከተገሠጽሁም በኋላ በኀዘን ጭኔን ጸፋሁ፤#31፥19 ጥልቅ ኀዘንን የሚገልጥ አባባል ነው። የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ ተዋረድሁም።’ 20በእውነት ኤፍሬም የተወደደ ልጄ ነውን? ወይስ ደስ የምሰኝበት ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አሁንም ድረስ በትክክል አስታውሰዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል ጌታ።
21“ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዓምዶችን ትከዪ፥ የሄድሽበትን መንገድ ዐውራ ጐዳናውን ልብ አድርገሽ ተመልከቺ፤ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ! ተመለሺ፥ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ ተመለሺ። 22አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! እስከ መቼ ታመነቻለሽ? ጌታ በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሴት ወንድን ትከብባለች።”
23የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ፦ ‘የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! ጌታ ይባርክህ’ የሚልን ቃል እንደገና ይናገራሉ። 24የይሁዳና የከተሞችዋ ሕዝብ ሁሉ፥ ገበሬዎችና ከመንጋቸም ጋር የሚዞሩ በአንድነት በዚያ ይቀመጣሉ። 25የደከመችውን ነፍስ አርክቻለሁና፥ የዛለችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና።” 26ከዚህም በኋላ ነቃሁ ተመለከትሁም፥ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆነልኝ።
እያንዳንዱ ሰው ስለ ኃጢአቱ ፍዳውን መቀበሉ
27“የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት በሰው ዘርና በእንስሳ ዘር የማራባበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል ጌታ። 28እንዲህም ይሆናል፤ እነርሱን ልነቅላቸውና ልሰባብራቸው፥ ላፈርሳቸውና ላጠፋቸው፥ ክፉም ላደርግባቸው እንደ ተጋሁ፥ እንዲሁ ልሠራቸውና ልተክላቸው እተጋለሁ፥ ይላል ጌታ። 29#ሕዝ. 18፥2።በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ እንዲህ አይሉም፦ ‘አባቶች የሚጎመዝዝ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፤’ 30ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ መራራውን የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ ጥርሶቹ የተጠረሱ ይሆናሉ።”
አዲስ ቃል ኪዳን
31 # ማቴ. 26፥28፤ ማር. 14፥24፤ ሉቃ. 22፥20፤ 1ቆሮ. 11፥25፤ 2ቆሮ. 3፥6፤ ዕብ. 8፥8-12። “እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የማደርግበት ወራት ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ 32እጃቸውን ይዤ ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ አደረግሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እኔ ገዢአቸው ብሆንም እንኳ ያን ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፥ ይላል ጌታ። 33#ዕብ. 10፥16።ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የማደርገው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 34#ዕብ. 10፥17።እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ ‘ጌታን እወቅ’ ብሎ ከእንግዲህ ወዲህ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል ጌታ። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስምና።”
35ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን የማይዛነፍ ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ 36“ይህ ጽኑ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል ጌታ፥ በዚያን ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ትውልድ በፊቴ ሕዝብ የመሆኑ ነገር ለዘለዓለም ያበቃለታል። 37ጌታ እንዲህ ይላል፦ በላይ ያለው ሰማይ ቢለካ፥ በታችም ያለው የምድር መሠረት ቢመረመር፥ በዚያን ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ የእስራኤልን ትውልድ በሙሉ እጥላለሁ፥ ይላል ጌታ።”
የኢየሩሳሌም ድንበር መስፋቱ
38“ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ለጌታ ከተማ የሚሠራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል ጌታ። 39የመለኪያውም ገመድ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፥ ከዚያም ወደ ጎዓም ይዞራል። 40የሬሳና የአመድ ሸለቆ ሁሉ፥ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ ያለው የትልም እርሻ ሁሉ፥ በምሥራቅም በኩል እስካለው እስከ ፈረሰ በር ማዕዘን ድርስ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘለዓለም አይነቀልም አይፈርስምም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ