ኦሪት ዘሌዋውያን 16:1-10

ኦሪት ዘሌዋውያን 16:1-10 አማ54

በእግዚአብሔር ፊት የቀረቡና የሞቱ ሁለቱ የአሮን ልጆች ከሞቱ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ተናገረው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና እንዳይሞት በመጋረጃው ውስጥ በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሁልጊዜ እንዳይገባ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው። እንዲሁ አሮን ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አውራ በግ ይዞ ወደ ተቀደሰ ስፍራ ይግባ። የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፥ የበፍታውም ሱሪ በገላው ላይ ይሁን፥ የበፍታውንም መታጠቂያ ይታጠቅ፥ የበፍታውንም መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ እነዚህ የተቀደሱ ልብሶች ናቸው፤ ገላውንም በውኃ ታጥቦ ይልበሳቸው። ከእስራኤልም ልጆች ማኅበር ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለት አውራ ፍየሎች፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ። አሮንም ለእርሱ ያለውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያቀርባል፥ ለራሱም ለቤተሰቡም ያስተሰርያል። ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያቆማቸዋል። አሮንም በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጥልባቸዋል፥ አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር ሌላውንም ዕጣ ለሚለቀቅ። አሮንም የእግዚአብሔር ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያቀርባል፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት ያደርገዋል። የመለቀቅም ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያስተሰርይበት ዘንድ፥ ለመለቀቅም ወደ ምድረ በዳ ይሰድደው ዘንድ በሕይወቱ በእግዚአብሔር ፊት ያቆመዋል።