የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 16

16
1በእግዚአብሔር ፊት የቀረቡና የሞቱ ሁለቱ የአሮን ልጆች ከሞቱ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ተናገረው፤ 2እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና እንዳይሞት በመጋረጃው ውስጥ በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሁልጊዜ እንዳይገባ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው። 3እንዲሁ አሮን ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አውራ በግ ይዞ ወደ ተቀደሰ ስፍራ ይግባ። 4የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፥ የበፍታውም ሱሪ በገላው ላይ ይሁን፥ የበፍታውንም መታጠቂያ ይታጠቅ፥ የበፍታውንም መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ እነዚህ የተቀደሱ ልብሶች ናቸው፤ ገላውንም በውኃ ታጥቦ ይልበሳቸው። 5ከእስራኤልም ልጆች ማኅበር ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለት አውራ ፍየሎች፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ። 6አሮንም ለእርሱ ያለውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያቀርባል፥ ለራሱም ለቤተሰቡም ያስተሰርያል። 7ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያቆማቸዋል። 8አሮንም በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጥልባቸዋል፥ አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር ሌላውንም ዕጣ ለሚለቀቅ። 9አሮንም የእግዚአብሔር ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያቀርባል፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት ያደርገዋል። 10የመለቀቅም ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያስተሰርይበት ዘንድ፥ ለመለቀቅም ወደ ምድረ በዳ ይሰድደው ዘንድ በሕይወቱ በእግዚአብሔር ፊት ያቆመዋል። 11አሮንም ስለ ራሱ ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ወይፈኑን ያቀርባል፤ ለራሱም ለቤተ ሰቡም ያስተሰርያል፤ ስለ ኃጢአቱ የእርሱን መሥዋዕት ወይፈኑን ያርዳል። 12በእግዚአብሔርም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፥ ከተወቀጠውም ከጣፋጭ ዕጣን እጁን ሙሉን ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል። 13እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለውን መክደኛ ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል። 14ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ላይ ወደ ምሥራቅ በጣቱ ይረጨዋል፤ ከደሙም በመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጫል። 15ስለ ሕዝቡም ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል። 16ከእስራኤል ልጆች ርኩስነት ከመተላለፋቸውም ከኃጢአታቸውም የተነሣ ለመቅደሱ ያስተሰርይለታል፤ እንዲሁም በርኩስነታቸው መካከል ከእነርሱ ጋር ለኖረች ለመገናኛው ድንኳን ያደርጋል። 17እርሱም ለማስተስረይ ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተ ሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባዔ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማንም አይኖርም። 18በእግዚአብሔርም ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያ ወጥቶ ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል። 19ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፥ ከእስራኤልም ልጆች ርኩስነት ያነጻዋል፥ ይቀድሰውማል። 20መቅደሱንም፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መሠዊያውንም ማስተስረይ ከፈጸመ በኋላ ሕያውን ፍየል ያቀርባል፤ 21አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፥ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ መተላለፋቸውንም ሁሉ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፥ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል። 22ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ በረሀ ይሸከማል፤ ፍየሉንም በምድረ በዳ ውስጥ ይለቅቀዋል። 23አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባል፥ ወደ መቅደሱም በገባ ጊዜ የለበሰውን የበፍታ ልብስ ያወልቃል፥ በዚያም ይተወዋል፤ 24በተቀደሰውም ስፍራ ገላውን በውኃ ይታጠባል፥ ሌላውንም ልብስ ለብሶ ይወጣል፤ የእርሱንም የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የሕዝቡንም የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፥ ለራሱም ለሕዝቡም ያስተሰርያል። 25የኃጢአቱንም መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 26ለመለቀቅ የሚሆነውን ፍየል የወሰደ ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል። 27ለማስተስረያም እንዲሆን ደማቸው ወደ መቅደስ የገባውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈንና የኃጢአቱን መሥዋዕት ፍየል ከሰፈሩ ወደ ውጭ ያወጡአቸዋል፤ ቁርበታቸውንም፥ ሥጋቸውንም፥ ፈርሳቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። 28ያቃጠላቸውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል። 29-30ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ፤ በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተስረያ ይሆንላችኋልና በሰባተኛው ወር ከወሩም በአስረኛው ቀን ራሳችሁን አስጨንቍት፥ የአገር ልጅም በእናንተ መካከል የተቀመጠም እንግዳ ሥራን ሁሉ አትሥሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ። 31ታላቅ ሰንበት ይሆንላችኋል፥ ራሳችሁንም ታዋርዳላችሁ፤ የዘላለም ሥርዓት ነው። 32የሚቀባውም፥ በአባቱም ፈንታ ካህን ሊሆን የሚካነው ካህን ያስተስርይ፥ የተቀደሰውንም የበፍታ ልብስ ይልበስ፤ 33ለቅድስተ ቅዱሳንም ያስተስርይ፤ ለመገናኛውም ድንኳን ለመሠዊያውም ያስተስርይ፤ ለካህናቱም ለጉባኤውም ሕዝብ ሁሉ ያስተስርይ። 34ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኃጢአታቸው ሁሉ ያስተሰርይ ዘንድ የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ