ኦሪት ዘሌዋውያን 15
15
1እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው፦ ማንም ሰው ከሥጋው ፈሳሽ ነገር ቢወጣ፥ ስለሚፈስሰው ነገር ርኩስ ነው። 3ስለሚፈስሰው ነገር ርኩስነቱ ይህ ነው፤ ፈሳሹ ነገር ከሥጋው ቢፈስስ ወይም ከመፍሰሱ ቢቆም፥ ርኩስ መሆኑ ነው። 4ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው፤ የሚቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 5መኝታውንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 6ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በተቀመጠበት ነገር ላይ የሚቀመጥበት ሰው ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 7ፈሳሽ ነገር ያለበትን የሰውን ሥጋ የሚነካ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 8ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በንጹሕ ሰው ላይ ቢተፋ፥ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 9ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ነው። 10ከበታቹም ያለውን ነገር የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 11ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው እጁን በውኃ ሳይታጠብ የሚነካው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 12ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚነካውን የሸክላ ዕቃ ይስበሩት፤ የእንጨቱም ዕቃ ሁሉ በውኃ ይታጠብ። 13ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለ መንጻቱ ሰባት ቀን ይቈጥራል፤ ልብሱንም ያጥባል፥ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። 14በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ይመጣል፥ ለካህኑም ይሰጣቸዋል። 15ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ፈሳሹ ነገር ያስተሰርይለታል። 16የማንም ሰው ዘር ከእርሱ ቢወጣ፥ ገላውን ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 17ዘር የነካው ልብስ ሁሉ ቍርበትም ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 18ወንዱ በሴቲቱ ቢደርስባት ሁለቱ በውኃ ይታጠባሉ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩሶች ናቸው። 19ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው። 20መርገምም ስትሆን የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 21መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 22የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 23በመኝታዋም ላይ ወይም በምትቀመጥበት ነገር ላይ ቢሆን ሲነካው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው። 24ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋ ቢነካው፥ ሰባት ቀን ርኩስ ነው፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው። 25ሴትም ከመርገም ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከመርገምዋ ወራት የሚበልጥ ቢፈስስ፥ በመርገምዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኵስነት ወራት ትሆናለች፤ ርኩስ ናት። 26ደምዋም በሚፈስስበት ወራት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በመርገምዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ እንደ መርገምዋ ርኩስነት ርኩስ ነው። 27እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ልብሱንም ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 28ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች ከዚያም በኋላ ንጹሕ ትሆናለች። 29በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታመጣቸዋለች። 30ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ ርኩስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል። 31እንዲሁም በእነርሱ መካከል ያለችውን ማደሪያዬን ባረከሱ ጊዜ፥ በርኩስነታቸው እንዳይሞቱ የእስራኤልን ልጆች ከርኩስነታቸው ለያቸው። 32ፈሳሽ ነገር ላለበት ሰው፥ ይረክስም ዘንድ ዘሩ ለሚወጣበት ሰው፥ 33በመርገምዋም ለታመመች፥ ፈሳሽም ነገር ላለባቸው ለወንድም ለሴትም፥ የረከሰችንም ሴት ለሚገናኝ ሰው ሕጉ ይኸው ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 15: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ