ኦሪት ዘሌዋውያን 14
14
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2በመንጻቱ ቀን የለምጻሙ ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል። 3ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ፥ 4ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሐን ወፎች በሕይወታቸው፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። 5ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ይዝዛል። 6ሕያውንም ወፍ ዝግባውንም እንጨት ቀዩንም ግምጃ ሂሶጱንም ወስዶ ከሕያው ወፍ ጋር በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። 7ከለምጹ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ነው ይለዋል፥ ሕያውንም ወፍ ወደ ሜዳ ይለቅቀዋል። 8የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጕሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። 9በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጫል፤ ልብሱንም፥ ገላውንም በውኃ ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል። 10በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ስለ እህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። 11የሚያነጻውም ካህን እነዚህን ነገሮች የሚነጻውንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያኖራቸዋል። 12ካህኑም አንዱን ጠቦት ወስዶ ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ያንንም የሎግ መስፈሪያ ዘይት፤ ስለ መወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል። 13የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ የኃጢአቱ መሥዋዕት ለካህኑ እንደሚሆን፥ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 14ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። 15ካህኑም ከዘይቱ ከሎግ መስፈሪያው ወስዶ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። 16ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ባለው ዘይት ቀኝ ጣቱን ነክሮ ከዘይቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። 17ካህኑም በእጁ ውስጥ ከቀረው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል። 18በካህኑም እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 19ካህኑም የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፥ ከርኩሰቱም ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ በኋላም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል። 20ካህኑም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፥ ካህኑም ያስተሰርይለታል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል። 21ድሀም ቢሆን ይህንም ለማምጣት ገንዘቡ ባይበቃው፥ ማስተስረያ ይሆንለት ዘንድ እንዲወዘወዝ አንድ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፥ ከመስፈሪያውም ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። 22ሁለት ዋኖሶች ወይም የርግብ ግልገሎች እንደሚቻለው፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ይወስዳል። 23በስምንተኛውም ቀን ስለ መንጻት ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣቸዋል። 24ካህኑም የበደሉን መሥዋዕት ጠቦት የሎግ መስፈሪያውንም ዘይት ይወስዳል፤ ካህኑም ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል። 25የበደሉንም መሥዋዕት ጠቦት ያርዳል፤ ካህኑም ከበደሉ መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። 26ካህኑም ከዘይቱ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። 27ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ካለው ዘይት በቀኝ ጣቱ ሰባት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ይረጨዋል። 28ካህኑም በእጁ ውስጥ ካለው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል። 29በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በካህኑ እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርገዋል። 30እንደሚቻለው ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ግልገሎች አንዱን ያቀርባል። 31እንደሚቻለው አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ከእህል ቍርባን ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል ካህኑም ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 32ለመንጻቱ የሚያስፈልገውን ነገር ለማያገኝ የለምጽ ደዌ ላለበት ሰው ሕግ ይህ ነው። 33እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 34ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ እኔም የለምጽ ደዌ በርስታችሁ ምድር በአንድ ቤት ባደረግሁ ጊዜ፥ 35ባለቤቱ መጥቶ ካህኑን፦ ደዌ በቤቴ ውስጥ እንዳለ ይመስለኛል ብሎ ይንገረው። 36ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤት ሳይገባ፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ በኋላም ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። 37ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በግንቡ ላይ በአረንጓዴና በቀይ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ወደ ግንቡ ውስጥ ቢጠልቅ፥ 38ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። 39ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግንብ ላይ ቢሰፋ፥ 40ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ወደ ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። 41ቤቱንም በውስጡ በዙሪያው ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። 42በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሌች ድንጋዮች ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል። 43ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ 44ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስት ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። 45ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። 46በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 47በቤቱም የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም የሚበላ ልብሱን ያጥባል። 48ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ሻረ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። 49ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል። 50አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከምንጩ ውኃ በላይ ያርዳል። 51የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሕያውንም ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 52ቤቱንም በወፉ ደም በምንጩም ውኃ በሕያውም ወፍ በዝግባውም እንጨት በሂሶጱም በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። 53ሕያውንም ወፍ ከከተማ ወደ ሜዳ ይሰድደዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ ንጹሕም ይሆናል። 54ይህም ሕግ ነው ለሁሉ ዓይነት ለምጽ ደዌ፥ 55ለቈረቈርም፥ በልብስና በቤትም ላለ ለምጽ፥ 56ለእባጭም፥ ለብጕርም፥ ለቍቁቻም፤ 57በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ እንዲያስታውቅ ይህ የለምጽ ሕግ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 14: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ