ኦሪት ዘሌዋውያን 17
17
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገር፦ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፥ እንዲህም አለ፦ 3ከእስራኤል ቤት ማናችውም ሰው በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፥ በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥ 4በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር ቍርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአል፤ ያም ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 5ስለዚህ የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ወደ ካህኑም አምጥተው ለእግዚአብሔር ለደኅንነት መሥዋዕት ይሠዉታል። 6ካህኑም በመገኛኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ደሙን ይረጨዋል፥ ስቡንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ያቃጥለዋል። 7መሥዋዕታቸውንም ደግሞ ተከትለው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት አይሠዉ። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ሥርዓት ይሁን። 8ለእነርሱም እንዲህ በላቸው፦ ከእስራኤል ቤት በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ 9ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 10ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፥ ያንንም ሰው ከሕዝቡ ለይቼ አጠፋዋለሁ። 11የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። 12ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች፦ ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፥ በመካከላችሁም ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም አልሁ። 13ከእስራኤልም ልጆች በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ እያደነ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል በአፈርም ይከድነዋል። 14የሥጋ ሁሉ ሕይወትና ደሙ አንድ ነውና ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች፦ የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ አልኋቸው። 15የሞተውን ወይም አውሬ የሰበረውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የአገር ልጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 16ልብሱንና ገላውን ባያጥብ ግን ኃጢአቱን ይሸከማል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 17: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ