የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 18

18
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 3እንደ ተቀመጣችሁባት እንደ ግብፅ ምድር ሥራ አትሥሩ፤ እኔም ወደ እርስዋ እንደማገባችሁ እንደ ከነዓን ምድር ሥራ አትሥሩ፤ በሥርዓታቸውም አትሂዱ። 4ፍርዴን አድርጉ፥ በእርስዋም ትሄዱ ዘንድ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 6ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 7የአባትህን ኃፍረተ ሥጋና የእናትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እናትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 8የአባትህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ኃፍረተ ሥጋ ነው። 9የእኅትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የእናትህ ልጅ፥ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 10የወንድ ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ወይም የሴት ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአንተ ኃፍረተ ሥጋ ነውና። 11ከአባትህ የተወለደችውን የአባትህን ሚስት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ። 12የአባትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ዘመድ ናት። 13የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የእናትህ ዘመድ ናት። 14የአባትህን ወንድም ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፥ ወደ ሚስቱም አትቅረብ፤ የአጎትህ ሚስት ናት፤ 15የምራትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 16የወንድምህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድምህ ኃፍረተ ሥጋ ነው። 17የሴትንና የሴት ልጅዋን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድ ልጅዋን ሴት ልጅ ወይም የሴት ልጅዋን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ አታግባ፤ ዘመዶች ናቸው፤ ዝሙት ነው። 18ሚስትህ በሕይወት ሳለች እኅትዋ ጣውንትዋ እንዳትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ከእርስዋ ጋር እኅትዋን አታግባ። 19እርስዋም በመርገምዋ ርኵሰት ሳለች ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ወደ ሴት አትቅረብ። 20እንዳትረክስባትም ከባልንጀራህ ሚስት ጋር አትተኛ። 21ከዘርህም ለሞሎክ በእሳት አሳልፈህ አትስጥ፥ የአምላክህንም ስም አታርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 22ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነውና። 23እንዳትረክስባትም ከእንሰሳ ጋር አትተኛ፤ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት አትቁም፤ የተጠላ ነገር ነውና። 24በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። 25ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች። 26ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩ ልጆች በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤ 27ከእናንተ በፊት የነበሩ የአገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ 28ምድሪቱም ረክሳለችና፤ ባረከሳችኋት ጊዜ ምድሪቱ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እናንተን እንዳትተፋችሁ። 29ከዚህ ርኵሰት ሁሉ ማናቸውን የሚያደርግ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። 30ስለዚህ ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የሠሩትን ጸያፍ የሆነውን ወግ ሁሉ እንዳትሠሩ፥ በእርሱም እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ