የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 19

19
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ባላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። 3ከእናንተ ሰው ሁሉ እናቱንና አባቱን ይፍራ፥ ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 4ወደ ጣዖታትም ዘወር አትበሉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የአማልክት ምስሎች ለእናንተ አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5የደኅንነትንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሰዉ እርሱን ደስ እንድታሰኙበት ሠውት። 6በምትሠውት ቀንና በነጋው ይበላል፤ እስከ ሦስተኛውም ቀን ድረስ ቢተርፍ በእሳት ይቃጠላል። 7በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ጸያፍ ነው፥ ደስም አያሰኝም፤ 8የበላውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና ኃጢአቱን ይሸከማል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 9የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ። 10የወይንህንም ቃርሚያ አትቃርም፥ የወደቀውንም የወይንህን ፍሬ አትሰብስብ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተወው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 11አትስረቁ፥ አትካዱም፥ ከእናንተም እርስ በርሳችሁ ሐሰት አትነጋገሩ። 12በስሜም በሐሰት አትማሉ፥ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13በባልንጀራህ ግፍ አታድርግ፥ አትቀማውም። የሞያተኛው ዋጋ እስከ ነገ ድረስ በአንተ ዘንድ አይደርብህ። 14ደንቆሮውን አትስደብ፥ በዕውርም ፊት ዕንቅፋት አታድርግ፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 15በፍርድ ዓመፃ አታድርጉ፤ ለድሀ አታድላ፥ ባለ ጠጋውንም አታክብር፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በእውነት ፍረድ። 16በሕዝብህ መካከል በሸንጋይነት አትዙር፤ በባልንጀራህም ደም ላይ አትቁም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 17ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልነጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። 18አትበቀልም፥ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 19ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ። 20ማናቸውም ሰው ከሴት ባሪያ ጋር ቢተኛ፥ እርስዋም ለባል የተሰጠች ዋጋዋም ያልተከፈለ አርነት ያልወጣች ብትሆን፥ ቅጣት አለባቸው፤ አርነት አልወጣችምና አይገደሉም። 21እርሱም የበደሉን መሥዋዕት ይዞ ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይመጣል፥ ለበደልም መሥዋዕት አውራ በግ ያመጣል። 22ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት በበደል መሥዋዕት በግ ያስተሰርይለታል የሠራውም ኃጢአት ይቀርለታል። 23ወደ አገሩም በገባችሁ ጊዜ፥ የሚበላ የፍሬ ዛፍ ሁሉ በተከላችሁም ጊዜ፥ ፍሬውን እንዳልተገረዘ ትቈጥሩታላችሁ፤ ሦስት ዓመት እንዳልተገረዘ ይሆንላችኋል፤ አይበላም። 24የአራተኛውም ዓመት ፍሬ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ቅዱስ ይሁን። 25ፍሬውም ይበዛላችሁ ዘንድ የአምስተኛውን ዓመት ፍሬ ብሉ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 26ከደሙ ጋር ምንም አትብሉ፤ አስማትም አታድርጉ፥ ሞራ ገላጭም አትሁኑ። 27የራስ ጠጕራችሁንም ዙሪያውን አትከርክሙት፥ ጢማችሁንም ዙሪያውን አትቍረጡት። 28ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ፥ ገላችሁንም አትንቀሱት፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 29ምድሪቱ ከግልሙትና ከርኩሰትም እንዳትሞላ ሴት ልጅህን ታመነዝር ዘንድ አታርክሳት። 30ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 31ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቍዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 32በሽበታሙ ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 33በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። 34እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፥ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 35በፍርድ፥ በመለካትም፥ በመመዘንም፥ በመስፈርም ዓመፃ አታድርጉ። 36የእውነትም ሚዛን፥ የእውነትም መመዘኛ፥ የእውነትም የኢፍ መስፈሪያ፥ የእውነትም የኢን መስፈሪያ ይሁንላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እኔ ነኝ። 37ሥርዓቴን ሁሉ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ አድርጉም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ