ዘሌዋውያን 16:1-10

ዘሌዋውያን 16:1-10 NASV

በእግዚአብሔር ፊት በቀረቡ ጊዜ ከሞቱት፣ ከሁለቱ የአሮን ልጆች ሞት በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ተናገረው። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመና ውስጥ እገለጣለሁና ወንድምህ አሮን በመጋረጃው ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ማለት በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ፊት፣ በፈለገ ጊዜ ሁሉ እንዳይገባና እንዳይሞት ንገረው። “ወደ ተቀደሰው ስፍራ በሚገባበት ጊዜ፣ አሮን እንዲህ ያድርግ፤ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይዞ ይምጣ፤ የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፤ በሰውነቱ ላይ የሚያርፈውን ከበፍታ የተሠራውን የውስጥ ሱሪ ያጥልቅ፤ የበፍታውን መታጠቂያ ይታጠቅ፤ የበፍታውን መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ ልብሶቹ የተቀደሱ በመሆናቸው እነዚህን ከመልበሱ በፊት ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ። ከእስራኤል ማኅበረ ሰብ ለኀጢአት መሥዋዕት ሁለት ተባዕት ፍየሎች፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ። “አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ፣ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤ ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቁማቸው። አሮንም አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር፣ ሌላውን ለሚለቀቀው ፍየል ለማድረግ በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጣል። በዕጣ ለእግዚአብሔር የደረሰውንም ፍየል አምጥቶ ለኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ይሠዋ። ወደ ምድረ በዳ ተለቅቆ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ፣ እንዲለቀቅ ዕጣ የወጣበትን ፍየል ከነሕይወቱ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ።