ትንቢተ ኢሳይያስ 29:11-24

ትንቢተ ኢሳይያስ 29:11-24 መቅካእኤ

ይህ ሁሉ ራእይ እንደ ታተመ የመጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ፦ “ይህን አንብብ” ብለው ባዘዙት ጊዜ እርሱ፦ “ታሽጓልና አልችልም” ይላቸዋል፤ ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ፦ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ “ማንበብ አላውቅም” ይላቸዋል። ጌታም፦ ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛል። ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ አስደማሚ ነገርን ተአምራትንም እንደገና አደርጋለሁ፤ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች። ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከጌታ ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው፦ “ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል?” ለሚሉ ወዮላቸው! ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፦ “አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን፦ “አታስተውልም” ይለዋልን? ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቆጠር ጥቂት ዘመን ቀርቶት የለምን? በዚያም ቀን ደንቆሮዎች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፥ የዕውሮችም ዐይኖች ጭጋግና ጨለማው ተገፎላቸው ያያሉ። የዋሃን ደስታቸውን በጌታ ያበዛሉ፥ በሰዎች መካከል ያሉ ችግረኞችም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ። ጨካኙ ሰው አልቆአልና፥ ፌዘኛውም ጠፍቷልና፥ ለኃጢአትም ያደፈጡ ሁሉ ይቈረጣሉ፤ እነርሱም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው። ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠ ጌታ ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፦ ያዕቆብ አሁን አያፍርም፥ ፊቱም አሁን አይለወጥም። ነገር ግን የእጄን ሥራ ልጆቹን በመካከሉ ባያቸው ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ። በመንፈስም የሳቱ ወደ ማስተዋል ይደርሳሉ፤ የሚያጉረመርሙም ምክርን ይቀበላሉ።