ራእዩም ሁሉ እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፥ ማንበብንም ለሚያውቅ፦ ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ ታትሞአልና አልችልም ይላቸዋል፥ ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ፦ ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል። ጌታም፦ ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ ድንቅ ነገርን ተአምራትንም፥ እንደ ገና አደርጋለሁ፥ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች። ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው፦ ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል? ለሚሉ ወዮላቸው! ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፦ አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን፦ አታስተውልም ይለዋልን? ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቆጠር ጥቂት ዘመን የቀረ አይደለምን? በዚያም ቀን ደንቆሮች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፥ የዕውሮችም ዓይኖች ከጭጋግና ከጨለማ ተለይተው ያያሉ። የዋሃን ደስታቸውን በእግዚአብሔር ያበዛሉ፥ በሰዎች መካከል ያሉ ችግረኞችም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ። ጨካኙ ሰው አልቆአልና፥ ፌዘኛውም ጠፍቷልና፥ ለኃጢአትም የደፈጡ ሁሉ ይቈረጣሉና፥ እነዚህም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው። ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠ እግዚአብሔር ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፦ ያዕቆብ አሁን አያፍርም፥ ፊቱም አሁን አይለወጥም። ነገር ግን የእጄን ሥራ ልጆቹን በመካከሉ ባያቸው ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፥ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ። በመንፈስም የሳቱ ማስተዋልን ያውቃሉ፥ የሚያጕረመርሙ ትምህርትን ይቀበላሉ።
ትንቢተ ኢሳይያስ 29 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 29:11-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች