የትንቢት ራእይ ሁሉ ትርጒም ከእናንተ ተሰውሮ እንደ ታሸገ መጽሐፍ ይሆናል፤ ወደሚያነብ ሰው ወስዳችሁ “አንብብልን” ብላችሁ ብትጠይቁት እንኳ “ስለ ታሸገ ላነበው አልችልም” ይላችኋል። ማንበብ ወደማይችል ሰው ወስዳችሁ “አንብብልን” ብትሉት፥ “እኔ ማንበብ አልችልም” ይላችኋል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕዝብ በአፉ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ እኔንም የሚያመልከኝ ሰው ሠራሽ ወግና ሥርዓትን እያስተማረ በከንቱ ነው። አስደናቂ ተአምርን አከታትዬ በማምጣት ይህ ሕዝብ እንዲገረም አደርገዋለሁ፤ የጥበበኞች ጥበብ ትሰወራለች፤ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትረሳለች።” ዕቅዳቸውን ከእግዚአብሔር ለመደበቅ ወደ ጥልቅ ቦታ ለሚሄዱ በጨለማ የሠሩትንም ሥራ “ማን ያይብናል? ማን ያውቅብናል?” ለሚሉ ሰዎች ወዮላቸው! እናንተ ሁሉን ነገር ትገለባብጣላችሁ። ሸክላ ሠሪው ከሸክላው አይበልጥምን? አንድ የተሠራ ሥራ ሠሪውን “አንተ አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ ደግሞ የሸክላ ዕቃ ሸክላ ሠሪውን “ሥራህን አታውቅም” ይለዋልን? በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሊባኖስ ጫካ የእርሻ ቦታ ይሆናል፤ የእርሻው ቦታ ወደ ጫካነት ይለወጣል። ደንቆሮዎች የሚነበብላቸውን መጽሐፍ መስማት የሚችሉበት ጊዜና በጨለማ የሚኖሩ ዕውሮችም ዐይኖቻቸው በርተው የሚያዩበት ጊዜ ይመጣል። ትሑታንና ችግረኞች በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ይደሰታሉ። ጨካኞችና ፌዘኞች ይጠፋሉ፤ ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ይደመሰሳሉ። ሰውን በነገር ወንጀለኛ የሚያደርጉ፥ ተከሳሽንም በፍርድ ሸንጎ የሚያጠምዱ፥ በሐሰተኛ ምስክር ንጹሕ ሰው ፍትሕ እንዳያገኝ በሐሰት የሚመሰክሩትን ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል። ስለዚህ አብርሃምን ከችግሩ ያዳነ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ውርደትና ኀፍረት አይደርስባችሁም። የእጄ ሥራ የሆኑትን ልጆቻቸውን በመካከላቸው ባዩ ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የእስራኤልን ቅዱስ ያከብራሉ፤ በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሃት ይቆማሉ። በመንፈስም የሚሳሳቱ ማስተዋልን ይገበያሉ፤ ዘወትር የሚያጒረመርሙ ትምህርትን ይቀበላሉ።”
ትንቢተ ኢሳይያስ 29 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 29:11-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos