የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 29:11-24

ኢሳይያስ 29:11-24 NASV

ይህ ሁሉ ራእይ በጥቅልል መጽሐፍ ውስጥ እንደ ታሸገ ቃል ሆኖባችኋል። ጥቅልሉንም መጽሐፍ ማንበብ ለሚችል ሰው፣ “እባክህ አንብብልን” ብላችሁ ብትሰጡት፣ “ታሽጓልና አልችልም” ይላችኋል። ደግሞም ጥቅልሉን መጽሐፍ ማንበብ ለማይችል ሰው፣ “እባክህን አንብብልን” ብላችሁ ብትሰጡ፣ “ማንበብ አልችልም” ይላችኋል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ የሚያመልከኝም፣ ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ነው። ስለዚህ ይህን ሕዝብ በድንቅ ላይ ድንቅ ነገር እያደረግሁ፣ ዳግመኛ አስገርመዋለሁ፤ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች።” ሐሳባቸውን ከእግዚአብሔር ለመደበቅ፣ ወደ ጥልቅ ጕድጓድ ለሚወርዱ ሥራቸውንም በጨለማ ለሚያከናውኑ፣ “ማን ያየናል? ማንስ ያውቅብናል” ለሚሉ ወዮላቸው! እናንተ ነገሮችን ትገለብጣላችሁ ሸክላ ሠሪውን እንደ ሸክላ ትመለከታላችሁ! ለመሆኑ፣ ተሠሪ ሠሪውን፣ “እርሱ አልሠራኝም” ይለዋልን? ሸክላ የሠራውን፣ “እርሱ ምንም አያውቅም” ይለዋልን? ሊባኖስ ወደ ለም ዕርሻነት ለመለወጥ፣ ለም የሆነውም መሬት ወደ ዱርነት ለመለወጥ ጥቂት ጊዜ አልቀረውምን? በዚያ ጊዜ ደንቈሮ የጥቅልሉን መጽሐፍ ቃል ይሰማል፤ የዐይነ ስውሩም ዐይኖች ከጭጋግና ከጨለማ ተላቀው ያያሉ። ትሑታን በእግዚአብሔር፣ ምስኪኖችም በእስራኤል ቅዱስ እንደ ገና ሐሤት ያደርጋሉ። ጨካኞች እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ፌዘኞችም በንነው ይጠፋሉ፤ ለክፋት ያደፈጡ ሁሉ ይወገዳሉ። ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፣ በተከሳሽ ላይ ወጥመድ የሚዘረጉ፣ በሐሰት ምስክር ፍትሕን ከንጹሓን የሚቀሙ ይቈረጣሉ። ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠው እግዚአብሔር ለያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፤ “ያዕቆብ ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም፤ ፊቱም ከእንግዲህ አይለዋወጥም። በመካከላቸው የእጄ ሥራ የሆኑ፣ ልጆቻቸውን ሲያዩ፣ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብን ቅዱስ ቅድስና ያውቃሉ፤ በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሀት ይቆማሉ። በመንፈስ የሳቱ ያስተውላሉ፤ የሚያጕረመርሙም ምክር ይቀበላሉ።”