ትንቢተ ኢሳይያስ 29
29
1ዳዊት የሰፈረብሽ ከተማ አርኤል፥ አንቺ አርኤል ወዮልሽ! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ፥ በዓላትም ይመላለሱ። 2ግን አርኤልንም አስጨንቃለሁ፥ ልቅሶና ዋይታም ይሆንባታል፤ እሷም እንደ አርኤል ትሆንልኛለች። 3በዙሪያሽም እሰፍራለሁ፥ በቅጥርም ከብቤ አስጨንቅሻለሁ፥ የጥበቃ አምባም በላይሽ አቆማለሁ። 4ትዋረጃለሽ፥ መሬት ላይ ተደፍተሽ ትናገሪያለሽ፥ ቃልሽም በዝግታ ከአፈር ይወጣል፤ ድምጽሽም ከመሬት እንደሚወጣ እንደ መናፍስት ድምፅ ይሆናል፥ ንግግርሽም ከአፈር በሹክሹክታ ይወጣል። 5ነገር ግን የጠላቶችሽ ብዛት እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጨካኞችም ብዛት እንደሚያልፍ ገለባ ይሆናል። 6ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅም ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። 7በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ እርሷንና ምሽግዋንም የሚወጉ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደ ሕልምና፥ እንደ ሌሊት ራእይ ይሆናል። 8ተርቦም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይበላል፥ ነገር ግን ይነቃል ሰውነቱም ባዶ ነው፤ ተጠምቶም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይጠጣል፥ ነገር ግን ይነቃል፥ እነሆም፥ ይዝላል ሰውነቱም እንደተጠማ አለ፤ የጽዮንን ተራራም የሚወጉ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደዚሁ ይሆናል። 9ተደነቁ ደንግጡም፤ ጨፍኑ ታወሩም! ስክሩም፥ በወይን ጠጅ አይደለም፤ ተንገዳገዱ፥ በመጠጥ አይደለም። 10#ሮሜ 11፥8።ጌታ የሚደብት የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል፤ ዐይኖቻችሁን፥ ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል፤ ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል። 11ይህ ሁሉ ራእይ እንደ ታተመ የመጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ፦ “ይህን አንብብ” ብለው ባዘዙት ጊዜ እርሱ፦ “ታሽጓልና አልችልም” ይላቸዋል፤ 12ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ፦ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ “ማንበብ አላውቅም” ይላቸዋል። 13#ማቴ. 15፥8፤9፤ ማር. 7፥6፤7።ጌታም፦ ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛል። 14#1ቆሮ. 1፥19።ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ አስደማሚ ነገርን ተአምራትንም እንደገና አደርጋለሁ፤ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች። 15ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከጌታ ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው፦ “ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል?” ለሚሉ ወዮላቸው! 16#ኢሳ. 45፥9፤ ሲራ. 33፥13፤ ሮሜ 9፥20።ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፦ “አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን፦ “አታስተውልም” ይለዋልን? 17ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቆጠር ጥቂት ዘመን ቀርቶት የለምን? 18በዚያም ቀን ደንቆሮዎች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፥ የዕውሮችም ዐይኖች ጭጋግና ጨለማው ተገፎላቸው ያያሉ። 19የዋሃን ደስታቸውን በጌታ ያበዛሉ፥ በሰዎች መካከል ያሉ ችግረኞችም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ። 20ጨካኙ ሰው አልቆአልና፥ ፌዘኛውም ጠፍቷልና፥ ለኃጢአትም ያደፈጡ ሁሉ ይቈረጣሉ፤ 21እነርሱም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው። 22ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠ ጌታ ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፦ ያዕቆብ አሁን አያፍርም፥ ፊቱም አሁን አይለወጥም። 23ነገር ግን የእጄን ሥራ ልጆቹን በመካከሉ ባያቸው ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ። 24በመንፈስም የሳቱ ወደ ማስተዋል ይደርሳሉ፤ የሚያጉረመርሙም ምክርን ይቀበላሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 29: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ