ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:11-31

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:11-31 አማ05

ከቤተሰብህ አንዱ ተነሥቶ ችግር እንዲያደርስብህ የማደርግ መሆኔን በመሐላ አረጋግጥልሃለሁ፤ ሚስቶችህን ወስጄ ለሌላ ሰው በምሰጥበት ጊዜ ይህ ነገር እንደሚፈጸም ትገነዘባለህ፤ እርሱም ከሚስቶችህ ጋር በቀን ብርሃን ይገናኛል። አንተ ይህን ኃጢአት በስውር ሠርተሃል፤ እኔ ግን እስራኤል ሁሉ ይመለከቱ ዘንድ ይህን ነገር የቀን ብርሃን ባለበት በግልጥ አደርጋለሁ።’ ” ዳዊትም “ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዝኛለሁ” አለ። ናታንም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እግዚአብሔር ይቅር ስላለህ አትሞትም፤ ነገር ግን ይህን በደል በመፈጸም እግዚአብሔርን ስለ ናቅህ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ከዚህ በኋላ ናታን ወደ ቤቱ ሄደ። የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ልጅ እግዚአብሔር በከባድ ሕመም ቀሠፈው፤ ዳዊትም ሕፃኑን እንዲፈውስለት በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ለመነ፤ በየሌሊቱም ወደ መኝታ ክፍሉ እየገባ በመሬት ላይ ይተኛ ነበር፤ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች ወደ እርሱ ቀርበው ከመሬት ላይ ሊያስነሡት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከመሬት ላለመነሣትና ከእነርሱም ጋር ምንም ነገር ላለመቅመስ ወሰነ፤ ከአንድ ሳምንትም በኋላ ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት ባለሟሎችም መርዶውን ለመንገር ፈርተው “ሕፃኑ በሕይወት በነበረበት ጊዜ እንኳ ዳዊት ስንመክረው አልሰማንም፤ ታዲያ፥ አሁን የልጁን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? ምናልባት በራሱ ላይ አንዳች ጒዳት ማድረስ ይችል ይሆናል!” አሉ። ዳዊት እርስ በርሳቸው ሲያንሾካሹኩ በሰማ ጊዜ ሕፃኑ መሞቱን ተረዳ፤ ስለዚህም “ሕፃኑ ሞተ እንዴ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አዎ ሞቶአል” ሲሉ መለሱለት። ዳዊትም ከተኛበት መሬት ተነሥቶ ሰውነቱን ታጠበ፤ ቅባት ተቀባ፤ ልብሱንም ለወጠ፤ ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄዶ ሰገደ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም ሲመለስ ምግብ እንዲያቀርቡለት ጠየቀ፤ እንደ ቀረበለትም ወዲያውኑ ተመገበ፤ ባለሟሎቹም “ይህ ነገር ምን እንደ ሆነ ለማወቅ አልቻልንም፤ ሕፃኑ በሕይወት በነበረበት ጊዜ በመጾም አለቀስክለት፤ እርሱ ከሞተ በኋላ ግን ወዲያውኑ ተነሥተህ ተመገብክ!” አሉት። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕፃኑ በሕይወት ሳለ መጾሜና ማልቀሴ እርግጥ ነው፤ እግዚአብሔር ምሕረት አድርጎልኝ ሕፃኑ እንዳይሞት ያደርግ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፤ አሁን ግን ከሞተ በኋላ ስለምን እጾማለሁ? ሕፃኑን እንደገና በሕይወት እንዲኖር ማድረግ ይቻለኛልን? እኔ አንድ ቀን ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ ተመልሶ አይመጣም።” ከዚህ በኋላ ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ከእርስዋም ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ዳዊትም የልጁን ስም “ሰሎሞን” ብሎ ጠራው፤ እግዚአብሔር ሕፃኑን ስለ ወደደው፥ “ይዲድያ” የሚል ስም እንዲያወጣለት ነቢዩ ናታንን አዘዘው፤ ይህም “በእግዚአብሔር የተወደደ” ማለት ነው። በዚያን ጊዜ ኢዮአብ ራባ ተብላ የምትጠራውን የዐሞናውያንን ከተማ ለመያዝ የሚያደርገውን ዘመቻ በመቀጠል የከተማ ውሃ የሚገኝበትን ምሽግ ያዘ። መልእክተኞችንም ልኮ ለዳዊት እንዲህ ብለው እንዲነግሩት አደረገ፤ “በራባ ላይ አደጋ ጥዬ የውሃ ማመንጫውን ምሽግ ይዤአለሁ፤ እነሆ አሁን ከሠራዊትህ ቀሪውን ክፍል አሰባስብና በከተማይቱ ላይ አደጋ በመጣል አንተው ራስህ ያዛት፤ አለበለዚያ እኔ ከተማይቱን ይዤ በስሜ እንድትጠራ አደርጋለሁ።” ስለዚህም ዳዊት ሠራዊቱን ሁሉ አሰባስቦ ወደ ራባ በመዝመት አደጋ ጥሎ ያዛት፤ ዳዊት የዐሞናውያን አምላክ ከሆነው ሚልኮም ተብሎ ከሚጠራው ጣዖት ራስ ላይ ሠላሳ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝነውንና በውስጡም የከበረ ዕንቊ ያለበትን ዘውድ ወስዶ በራሱ ላይ ደፋው፤ እንዲሁም ከከተማይቱ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ ሰዎቹም በመጋዝ፥ በብረት ዶማና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ ጡብ እንዲሠሩለትም አስገደዳቸው፤ በሌሎቹ የዐሞን ከተሞች ሁሉ ያሉትን ሰዎችም እንዲሁ በዚሁ ዐይነት እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ ከዚህ በኋላ እርሱና ሠራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።