እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፥ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፥ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ። ዳዊትም ናታንን፦ እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፥ አትሞትም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል አለው። ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈ፥ እጅግም ታምሞ ነበር። ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፥ ዳዊትም ጾመ፥ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ። የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፥ እርሱ ግን እንቢ አለ፥ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም። በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ባሪያዎች፦ ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፥ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ። ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ አወቀ፥ ዳዊትም ባሪያዎቹን፦ ሕፃኑ ሞቶአል? አላቸው። እነርሱም፦ ሞቶአል አሉት። ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፥ ተቀባም፥ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ፦ እንጀራ አምጡልኝ አለ፥ በፊቱም አቀረቡለት፥ በላም። ባሪያዎቹም፦ ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፥ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት። እርሱም፦ ሕፃኑ ሕያው ሳለ፦ እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቀስሁም። አሁን ግን ሞቶአል፥ የምጾመው ስለ ምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ። ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፥ ወደ እርስዋም ገባ፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ ወንድ ልጅም ወለደች፥ ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው፥ ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ይዲድያ ብሎ ጠራው። ኢዮአብም የአሞንን ልጆች ከተማ ረባትን ወጋ፥ የውኃውንም ከተማ ያዘ። ኢዪአብም ወደ ዳዊት፦ ረባትን ወግቻለሁ፥ የውኃውንም ከተማ ይዤአለሁ። አሁንም ከተማይቱን እንዳልይዝ፥ በስሜም እንዳትጠራ፥ የቀረውን ሕዝብ ሰብስብ፥ ከተማይቱንም ከብበህ ያዝ ብሎ መልእክተኞችን ላከ። ዳዊትም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ረባት ሄደ፥ ወግቶም ያዛት። የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበር፥ ክቡር ዕንቁም ነበረበት፥ ዳዊትም በራሱ ላይ አደረገው። ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቆፈሪያና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፥ የሸክላ ጡብም እንዲያቃጥሉ አደረጋቸው፥ በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲህ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:11-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች