2 ሳሙኤል 12:11-31

2 ሳሙኤል 12:11-31 NASV

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋራ ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።’ ” ከዚያም ዳዊት ለናታን፣ “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፣ “እግዚአብሔር ኀጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤ ይህን በመፈጸምህ ግን፣ የእግዚአብሔር ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፣ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፣ የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃን እግዚአብሔር ከባድ ሕመም ላይ ጣለው። ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ከዚያም ወደ ክፍሉ ገብቶ በተከታታይ ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ። የቤተ ሰቡ ሰው፣ ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያስነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፤ ዐብሯቸውም አንዳች ነገር አልበላም። በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፣ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም፤ ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጕዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ። ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፣ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፣ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አዎን ሞቷል” ብለው መለሱለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፣ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ፣ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ። አገልጋዮቹም፣ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “በርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፣ ‘እግዚአብሔር ይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ። አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፣ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፣ እርሱ ወደ እኔ አይመለስ!” ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ ዐብሯት ተኛ፤ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን አለው። እግዚአብሔርም ወደደው፤ እግዚአብሔር ሕፃኑን ስለ ወደደውም ስሙ ይዲድያ ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ። በዚያ ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያንን ከተማ ረባትን ወግቶ የቤተ መንግሥቱን ምሽግ ያዘ። ከዚያም ኢዮአብ እንዲህ በማለት ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ “ረባትን ወግቼ የውሃውን ከተማ ይዤአለሁ፤ እንግዲህ የቀረውን ሰራዊት አሰባስበህ ከተማዪቱን ክበብና ያዛት፤ አለዚያ እኔ ከተማዪቱን እይዛትና በስሜ መጠራቷ ነው።” ስለዚህ ዳዊት መላውን ሰራዊት አሰባስቦ ወደ ረባት በመሄድ ወግቶ ያዛት። የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ የዘውዱ ክብደት አንድ መክሊት ወርቅ የሚመዝን ሲሆን፣ በከበረ ዕንቍም ያጌጠ ነበር፤ ይህም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ። ዳዊትም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ እዚያ የነበሩትንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ የብረት መቈፈሪያና መጥረቢያ ተጠቅመው ሥራ እንዲሠሩ አደረጋቸው፣ እንዲሁም የሸክላ ጡብ አሠራቸው። እንዲህ ያለውም ሥራ በሌሎቹ የአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲፈጸም አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሰራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።