የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12

12
የናታን ትንቢታዊ ምሳሌና የዳዊት ንስሓ
1እግዚአብሔር ነቢዩን ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ ናታንም ወደ ዳዊት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱ አንዱ ሀብታም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ድኻ ነበር፤ #መዝ. 51። 2ሀብታሙ ሰው ብዙ የቀንድ ከብቶችና የበግ መንጋ ነበሩት፤ 3ድኻው ግን በገንዘቡ የገዛት አንዲት የበግ ግልገል ብቻ ነበረችው፤ እርስዋን እየተንከባከበ ከልጆቹ ጋር በቤቱ ውስጥ ያሳድጋት ነበር፤ ከሚመገበው ይመግባት፥ ከሚጠጣውም ያጠጣት ነበር፤ ስትተኛም ያቅፋት ነበር፤ ያቺም ግልገል ልክ እንደ ልጁ ነበረች፤ 4አንድ ቀን ወደ ሀብታሙ ሰው ቤት አንድ መንገደኛ መጣ፤ ሀብታሙ ሰው ለእንግዳው የሚሆን ምግብ ለማዘጋጀት ከእንሰሶቹ አንዱን ማረድ አልፈለገም፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ የድኻውን ሰው ግልገል ወስዶ በማረድ ለእንግዳው ምግብ አዘጋጀ።”
5ዳዊት በሀብታሙ ሰው ታሪክ እጅግ ተቈጥቶ “ይህን ያደረገው ሰው ሞት እንደሚገባው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! 6ይህን የመሰለ የጭካኔ ሥራ በመፈጸሙ ከዚያ ሰው የወሰደበትን አራት እጥፍ አድርጎ መመለስ አለበት” አለ።
7ናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ራስህ ነህ! የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ ንጉሥ አደረግኹህ፤ ከሳኦልም እጅ በመታደግ አዳንኩህ፤ 8መንግሥቱንና ሚስቶቹን ሰጠሁህ፤ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ አነገሥኩህ፤ ይህም ሁሉ እንኳ የማይበቃህ ቢሆን ኖሮ በተጨማሪ እጥፍ አድርጌ በሰጠሁህ ነበር፤ 9ታዲያ ትእዛዜን የናቅኸው ስለምንድን ነው? ይህንንስ ክፉ ነገር ለምን አደረግህ? ኦርዮን በጦር ሜዳ አስገደልከው፤ ንጹሑን ሰው ዐሞናውያን እንዲገድሉት አደረግህ፤ ሚስቱንም ወሰድክ! 10አንተ ለእኔ ስላልታዘዝክ የኦርዮን ሚስት ስለ ወሰድክ፥ እነሆ ከቤትህ በሰይፍ የሚገደል አይጠፋም፤ 11ከቤተሰብህ አንዱ ተነሥቶ ችግር እንዲያደርስብህ የማደርግ መሆኔን በመሐላ አረጋግጥልሃለሁ፤ ሚስቶችህን ወስጄ ለሌላ ሰው በምሰጥበት ጊዜ ይህ ነገር እንደሚፈጸም ትገነዘባለህ፤ እርሱም ከሚስቶችህ ጋር በቀን ብርሃን ይገናኛል። 12አንተ ይህን ኃጢአት በስውር ሠርተሃል፤ እኔ ግን እስራኤል ሁሉ ይመለከቱ ዘንድ ይህን ነገር የቀን ብርሃን ባለበት በግልጥ አደርጋለሁ።’ ” #2ሳሙ. 16፥22።
13ዳዊትም “ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዝኛለሁ” አለ። #12፥13 “እግዚአብሔርን ስለ ናቅሁ” አንዳንድ ትርጒሞች “የእግዚአብሔርን ጠላቶች እንዲሳለቁ ስላደረግህ” ይላሉ።
ናታንም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እግዚአብሔር ይቅር ስላለህ አትሞትም፤ 14ነገር ግን ይህን በደል በመፈጸም እግዚአብሔርን ስለ ናቅህ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።”
የዳዊት ልጅ መሞት
15ከዚህ በኋላ ናታን ወደ ቤቱ ሄደ። የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ልጅ እግዚአብሔር በከባድ ሕመም ቀሠፈው፤ 16ዳዊትም ሕፃኑን እንዲፈውስለት በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ለመነ፤ በየሌሊቱም ወደ መኝታ ክፍሉ እየገባ በመሬት ላይ ይተኛ ነበር፤ 17የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች ወደ እርሱ ቀርበው ከመሬት ላይ ሊያስነሡት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከመሬት ላለመነሣትና ከእነርሱም ጋር ምንም ነገር ላለመቅመስ ወሰነ፤ 18ከአንድ ሳምንትም በኋላ ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት ባለሟሎችም መርዶውን ለመንገር ፈርተው “ሕፃኑ በሕይወት በነበረበት ጊዜ እንኳ ዳዊት ስንመክረው አልሰማንም፤ ታዲያ፥ አሁን የልጁን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? ምናልባት በራሱ ላይ አንዳች ጒዳት ማድረስ ይችል ይሆናል!” አሉ።
19ዳዊት እርስ በርሳቸው ሲያንሾካሹኩ በሰማ ጊዜ ሕፃኑ መሞቱን ተረዳ፤ ስለዚህም “ሕፃኑ ሞተ እንዴ?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም “አዎ ሞቶአል” ሲሉ መለሱለት።
20ዳዊትም ከተኛበት መሬት ተነሥቶ ሰውነቱን ታጠበ፤ ቅባት ተቀባ፤ ልብሱንም ለወጠ፤ ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄዶ ሰገደ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም ሲመለስ ምግብ እንዲያቀርቡለት ጠየቀ፤ እንደ ቀረበለትም ወዲያውኑ ተመገበ፤ 21ባለሟሎቹም “ይህ ነገር ምን እንደ ሆነ ለማወቅ አልቻልንም፤ ሕፃኑ በሕይወት በነበረበት ጊዜ በመጾም አለቀስክለት፤ እርሱ ከሞተ በኋላ ግን ወዲያውኑ ተነሥተህ ተመገብክ!” አሉት።
22ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕፃኑ በሕይወት ሳለ መጾሜና ማልቀሴ እርግጥ ነው፤ እግዚአብሔር ምሕረት አድርጎልኝ ሕፃኑ እንዳይሞት ያደርግ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፤ 23አሁን ግን ከሞተ በኋላ ስለምን እጾማለሁ? ሕፃኑን እንደገና በሕይወት እንዲኖር ማድረግ ይቻለኛልን? እኔ አንድ ቀን ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ ተመልሶ አይመጣም።”
የሰሎሞን መወለድ
24ከዚህ በኋላ ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ከእርስዋም ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ዳዊትም የልጁን ስም “ሰሎሞን” ብሎ ጠራው፤ እግዚአብሔር ሕፃኑን ስለ ወደደው፥ 25“ይዲድያ” የሚል ስም እንዲያወጣለት ነቢዩ ናታንን አዘዘው፤ ይህም “በእግዚአብሔር የተወደደ” ማለት ነው።
ዳዊት በድል አድራጊነት ራባ ተብላ የምትጠራውን ከተማ መያዙ
(1ዜ.መ. 20፥1-3)
26በዚያን ጊዜ ኢዮአብ ራባ ተብላ የምትጠራውን የዐሞናውያንን ከተማ ለመያዝ የሚያደርገውን ዘመቻ በመቀጠል የከተማ ውሃ የሚገኝበትን ምሽግ ያዘ። 27መልእክተኞችንም ልኮ ለዳዊት እንዲህ ብለው እንዲነግሩት አደረገ፤ “በራባ ላይ አደጋ ጥዬ የውሃ ማመንጫውን ምሽግ ይዤአለሁ፤ 28እነሆ አሁን ከሠራዊትህ ቀሪውን ክፍል አሰባስብና በከተማይቱ ላይ አደጋ በመጣል አንተው ራስህ ያዛት፤ አለበለዚያ እኔ ከተማይቱን ይዤ በስሜ እንድትጠራ አደርጋለሁ።” 29ስለዚህም ዳዊት ሠራዊቱን ሁሉ አሰባስቦ ወደ ራባ በመዝመት አደጋ ጥሎ ያዛት፤ 30ዳዊት የዐሞናውያን አምላክ ከሆነው ሚልኮም ተብሎ ከሚጠራው ጣዖት ራስ ላይ ሠላሳ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝነውንና በውስጡም የከበረ ዕንቊ ያለበትን ዘውድ ወስዶ በራሱ ላይ ደፋው፤ እንዲሁም ከከተማይቱ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ #12፥30 ሜልኮም ተብሎ ከሚጠራው ጣዖት፦ ወይም “ከአሞናውያን ንጉሥ” 31ሰዎቹም በመጋዝ፥ በብረት ዶማና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ ጡብ እንዲሠሩለትም አስገደዳቸው፤ በሌሎቹ የዐሞን ከተሞች ሁሉ ያሉትን ሰዎችም እንዲሁ በዚሁ ዐይነት እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ ከዚህ በኋላ እርሱና ሠራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ