የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 13

13
አምኖንና ትዕማር
1የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ውብ የሆነች ትዕማር ተብላ የምትጠራ፥ ገና ባል ያላገባች እኅት ነበረችው፤ አምኖን ተብሎ የሚጠራው ከዳዊት ልጆች አንዱ ትዕማርን ወደዳት፤ 2እርስዋንም እጅግ ከማፍቀሩ የተነሣ ታመመ፤ ድንግል ስለ ነበረች እርስዋን መገናኘት ከቶ አልተቻለውም። 3ነገር ግን በጣም ዘዴኛ የሆነ፥ ዮናዳብ ተብሎ የሚጠራ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ነበር፤ 4ዮናዳብ አምኖንን “አንተ የንጉሥ ልጅ ሆነህ ሳለ በየቀኑ ሰውነትህ ጠውልጎ የማይህ ስለምንድን ነው? እስቲ ንገረኝ” ሲል ጠየቀው።
አምኖንም “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን ስለ ወደድኩ ነው” ሲል መለሰለት።
5ዮናዳብም እንዲህ አለው፤ “ይህ ከሆነ እንግዲህ የታመምህ መስለህ አልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣ፥ ‘እኅቴ ትዕማርን መጥታ እንድታስታምመኝ እባክህ ንገራት፤ እዚህ በአጠገቤ እያየኋት ምግብ አዘጋጅታ እርስዋ ራስዋ እንድታጐርሰኝ እፈልጋለሁ’ በለው።” 6ስለዚህም አምኖን የታመመ በመምሰል በአልጋው ላይ ተኛ።
ንጉሥ ዳዊትም ሊጠይቀው ወደ እርሱ በሄደ ጊዜ አምኖን “እኅቴ ትዕማር እዚህ በአጠገቤ እያየኋት ሁለት እንጀራ ጋግራ እርስዋ ራስዋ እንድታቀርብልኝ ፍቀድላት” አለው።
7ስለዚህም ዳዊት በቤተ መንግሥት ለምትገኘው ለትዕማር “ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ አዘጋጂለት” የሚል ትእዛዝ ላከ። 8እርስዋም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት በሄደች ጊዜ አልጋ ላይ ተኝቶ አገኘችው፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ በማቅጠንም አምኖን እያያት እንጀራ ጋገረች፤ 9የጋገረችውንም እንጀራ ከምጣዱ አውጥታ እንዲበላ አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መመገቡን እምቢ ብሎ “ሰዎቹን ሁሉ አስወጡልኝ” አለ፤ ሁሉም ወጡ፤ 10ከዚያም በኋላ አምኖን ትዕማርን “ታጐርሺኝ ዘንድ ምግቡን ይዘሽ ወደ አልጋዬ አምጪው” አላት፤ ስለዚህም ትዕማር ምግቡን ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን አመጣችው። 11በምታቀርብለትም ጊዜ አፈፍ በማድረግ ይዞ “እኅቴ ሆይ! አብረን እንተኛ!” አላት።
12እርስዋም “አይሆንም ወንድሜ ሆይ! እባክህ አታዋርደኝ! የዚህ ዐይነቱ አሳፋሪ ተግባር በእስራኤል ተፈጽሞ አያውቅም! ስለዚህ ይህን ትልቅ ብልግና አትፈጽም፤ 13እንደዚህ ካዋረድከኝ በኋላ በሕዝብ ፊት ራሴን ቀና አድርጌ ለመሄድ እንዴት እችላለሁ? አንተም ብትሆን በእስራኤል እጅግ የተዋረድክ ትሆናለህ፤ ይልቅስ ለንጉሡ ብትነግረው እኔን ለአንተ በሚስትነት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ነኝ” አለችው። 14እርሱ ግን ሊያዳምጣት አልፈቀደም፤ እርሱም ከእርስዋ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበረ በኀይል አስገድዶ ክብረ ንጽሕናዋን ደፈረ።
15ከዚያም በኋላ አምኖን እጅግ አድርጎ ጠላት፤ እንዲያውም ቀድሞ ካፈቀራት ይበልጥ አሁን በእርስዋ ላይ ያለው ጥላቻ ስለ ባሰ “ከዚህ ውጪልኝ!” አላት።
16እርስዋም “አይሆንም! እኔን እንደዚህ አድርገህ ብታባርረኝ አሁን ከፈጸምከው በደል ይልቅ የከፋ ኃጢአት ትፈጽማለህ!” አለችው።
አምኖን ግን ሊያዳምጣት አልፈቀደም፤ 17የግል አገልጋዩንም ጠርቶ “ይህችን ሴት ከፊቴ ወዲያ አስወግድልኝ! እርስዋንም ወደ ውጪ አስወጥተህ በሩን ዝጋ!” አለው። 18-19ትዕማርም የአምኖን አሽከር ከቤት አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ በዚያን ዘመን ያላገቡ የነገሥታት ልጆች ይለብሱት የነበረውን እጅጌ ረዥም የነበረ መጐናጸፊያ ለብሳ ነበር፤ እርስዋም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ ለብሳው የነበረውን መጐናጸፊያ ቀዳ እጅዋን በራስዋ ላይ በመጫን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች።
20ወንድምዋ አቤሴሎም ባያት ጊዜ “እኅቴ ሆይ! ወንድምሽ አምኖን አስነወረሽን? እባክሽ እንደዚህ አትበሳጪ፤ እርሱ ወንድምሽ ስለ ሆነ ለማንም አትናገሪ” አላት። ስለዚህ ትዕማር በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ከሰው የተለየች ብቸኛ ሆና ተቀመጠች።
21ንጉሥ ዳዊት የሆነውን ነገር በሰማ ጊዜ በብርቱ ተቈጣ፤ [ነገር ግን ይወደው ስለ ነበርና የበኲር ልጁም ስለ ነበረ ልጁን አምኖንን ሊያሳዝነው አልፈለገም።] 22የእኅቱን የትዕማርን ክብረ ንጽሕና በመድፈሩም ምክንያት አቤሴሎም አምኖንን እጅግ ጠላው፤ ዳግመኛም ክፉም ሆነ ደግ ሊያነጋግረው አልፈለገም።
አቤሴሎም የወሰደው የበቀል እርምጃ
23ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም ከተማ አጠገብ በዓለ ሐጾር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ ስለዚህም የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ ለግብዣ ወደዚያ ጠራ። 24ወደ ንጉሥ ዳዊትም ሄዶ “ንጉሥ ሆይ! በጎቼን እየሸለትሁ ነው፤ ስለዚህ አንተና መኳንንትህ መጥታችሁ የግብዣው ተካፋዮች እንድትሆኑልኝ ትፈቅዳለህን?” አለው።
25ንጉሡም “ልጄ ሆይ! መምጣት አያስፈልገንም፤ እኛ ሁላችን ከመጣን መስተንግዶው ይከብድብሃል” ሲል መለሰለት፤ አቤሴሎምም አጥብቆ ጠየቀ፤ ንጉሡ ግን አሳቡን መለወጥ ስላልፈቀደ አቤሴሎምን መርቆ አሰናበተው።
26አቤሴሎም ግን “መልካም ነው! አንተ መምጣት ካልፈቀድህ ወንድሜ አምኖን እንዲመጣ አትፈቅድለትምን?” ሲል ጠየቀ።
ንጉሡም “እርሱስ ቢሆን ለምን ይመጣል?” ሲል ጠየቀው። 27አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ጠየቀ ዳዊት፥ አምኖንና የቀሩትም ወንዶች ልጆቹ ሁሉ እንዲሄዱ ፈቀደ።
አቤሴሎም ለንጉሥ የሚገባ ግብዣ አዘጋጅቶ ነበር፤ 28አገልጋዮቹንም “አምኖን ብዙ ጠጥቶ መስከሩን ተመልከቱ፤ እኔም ትእዛዝ በምሰጣችሁ ጊዜ ግደሉት፤ ይህን ትእዛዝ የሰጠኋችሁ እኔ ስለ ሆንኩ ከቶ አትፍሩ! ደፋሮች ሁኑ፤ ምንም አታመንቱ!” አላቸው። 29ስለዚህ አገልጋዮቹ አቤሴሎም በነገራቸው መመሪያ መሠረት አምኖንን ገደሉ፤ የቀሩትም የዳዊት ወንዶች ልጆች በበቅሎዎቻቸው ተቀምጠው እየጋለቡ ሸሹ።
30ወደ ቤታቸው ለመድረስ ገና በመንገድ ላይ ሳሉ “አቤሴሎም ልጆችህን ሁሉ ገደላቸው! አንድ እንኳ የቀረ የለም!” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው። 31ንጉሡ ከተቀመጠበት በመነሣት በሐዘን ልብሱን ቀዶ በመሬት ላይ ተዘረረ፤ በዚያ ከእርሱ ጋር የነበሩ አገልጋዮቹም በሐዘን ልብሳቸውን ቀደው በአጠገቡ በአክብሮት ቆሙ። 32የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሆይ! የተገደሉት ልዑላኑ በሙሉ አይደሉም፤ የተገደለው አምኖን ብቻ ነው፤ አቤሴሎም ይህን ለማድረግ ያቀደው አምኖን የእኅቱን የትዕማርን ክብረ ንጽሕና ከደፈረበት ጊዜ አንሥቶ እንደ ነበር ፊቱን አይተህ መረዳት ትችላለህ። 33አሁንም ልዑላን በሙሉ እንደ ተገደሉ ሆኖ የተነገረህን ወሬ አትመን። የተገደለው አምኖን ብቻ ነው።”
34በዚህም ጊዜ አቤሴሎም ሸሽቶ አምልጦ ነበር፤ ለዘብ ጥበቃ ተረኛ የነበረውም ወታደር ልክ በዚያን ሰዓት ከሖርናይም ወደዚህ በሚመጣው መንገድ ላይ ካለው ኮረብታ ብዙ ሕዝብ ወደ ታች ሲወርድ አየ፤ ወደ ንጉሡም ቀርቦ ያየውን ሁሉ ተናገረ፤ 35ዮናዳብም ዳዊትን “ልክ እኔ አገልጋይህ እንዳልኩት እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤” አለው። 36እርሱ ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የዳዊት ልጆች ገብተው መላቀስ ጀመሩ፤ ዳዊትና መኳንንቱም በመረረ ሁኔታ አለቀሱ።
37-38አቤሴሎምም ሸሽቶ የገሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ታልማይ ሄደ፤ በዚያም ሦስት ዓመት ቈየ፤ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አምኖን ሞት ለረዥም ጊዜ በማዘን አለቀሰ፤ #2ሳሙ. 3፥3። 39ነገር ግን ስለ አምኖን ሞት የነበረበት ሐዘን እየተረሳ በሄደ ቊጥር ልጁን አቤሴሎምን መናፈቅ ጀመረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ