የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14

14
የአቤሴሎም ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ
1ንጉሡ ዳዊት አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ተረዳ፤ 2ስለዚህም በተቆዓ የምትኖረውን አንዲት ብልኅ ሴት አስጠራ፤ እርስዋም በደረሰች ጊዜ “ሐዘንተኛ ለመምሰል ሞክሪ፤ የሐዘን ልብስሽን ልበሺ፤ ቅቤም አትቀቢ፤ ለብዙ ጊዜ በሐዘን ላይ የቈየሽ ሴት ለመምሰል ተዘጋጂ፤ 3ከዚያም በኋላ ወደ ንጉሡ ቀርበሽ እኔ የምነግርሽን ንገሪው” አላት፤ ከዚህ በኋላ እርስዋ ልትናገረው የሚገባትን ሁሉ ኢዮአብ ነገራት።
4ሴቲቱም ወደ ንጉሡ ቀርባ ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ ነሣችና “ንጉሥ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው።
5ንጉሡም “ምን ችግር አጋጠመሽ?” አላት፤ እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “እኔ ባሌ የሞተብኝ መበለት ሴት ነኝ፤ 6ንጉሥ ሆይ! እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ አንድ ቀን ገላጋይ በሌለበት ስፍራ ሁለቱ ልጆቼ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ አንዱ ሌላውን ገደለው፤ 7ንጉሥ ሆይ! እነሆ አሁን ዘመዶቼ ሁሉ በእኔ በአገልጋይህ ላይ ተነሥተው ‘ወንድሙን ስለ ገደለ ወራሽ እንኳ ብናጠፋ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን ሰው ስጪን’ እያሉ አስቸገሩኝ። ታዲያ፥ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ የቀረኝን አንድ ተስፋ ሊያጠፉብኝና በምድርም ላይ የባሌን ስምና ዘር ሊያሳጡ ነው።”
8ንጉሡም “ወደ ቤትሽ ተመልሰሽ ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ ጉዳይ አዛለሁ” አላት።
9እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! አንተ ስለምታደርገው ነገር ሁሉ እኔና ቤተሰቤ እንወቀስበት አንተና ዙፋንህ ግን ንጹሓን ሁኑ” አለችው።
10ንጉሡም “ማንም ሰው ማንኛውንም ችግር ቢያመጣብሽ ወደ እኔ አምጪው ዳግመኛ ሊያስቸግርሽም አይችልም” አላት።
11እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! የልጄን ሞት ለመበቀል ኀላፊነት የተቀበለው ዘመዴ ሌላውን ልጄን በመግደል የባሰ ወንጀል እንዳይፈጽም ታደርገው ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ማልልኝ” አለችው።
ንጉሥ ዳዊትም “በልጅሽ ላይ ጒዳት መድረስ ይቅርና ከራስ ጠጒሩ እንኳ አንዲቱ መሬት ላይ እንደማትወድቅ በሕያው እግዚአብሔር ስም ቃል እገባልሻለሁ” አላት።
12ሴቲቱም “ንጉሥ ሆይ! እንደገናም እኔ አገልጋይህ አንድ ነገር እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው።
እርሱም “እሺ ተናገሪ” አላት።
13እርስዋም እንዲህ አለችው፤ “በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ይህን የመሰለ በደል የፈጸምከው ስለምንድን ነው? ልጅህ ከተሰደደበት አገር ተመልሶ እንዲመጣ አልፈቀድክለትም፤ ስለዚህ አሁን በተናገርከው ቃል በራስህ ላይ ፈርደሃል፤ 14እኛ ሁላችን መሞታችን የማይቀር ነው፤ እኛ በመሬት ላይ እንደ ፈሰሰና ተመልሶም ሊታፈስ እንደማይችል ውሃ ነን፤ እግዚአብሔር ግን በስደት ላይ የሚገኝ ሰው ከእርሱ እንደ ራቀ እንዳይቀር የሚመለስበትን መንገድ ያዘጋጅለታል እንጂ ሕይወቱ በከንቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም። 15አሁንም ንጉሥ ሆይ፥ እኔ ወደ አንተ የመጣሁት በዚህ ነገር ሰዎች ያስፈራሩኝ መሆኑን ልነግርህ ነው፤ ‘የጠየቅሁትን ሁሉ ያደርግልኛል’ በሚል ተስፋም በፊትህ ቀርቤአለሁ፤ 16የምነግርህን አድምጠህ ልጄንና እኔን በማጥፋት እግዚአብሔር የራሱ ካደረገው ምድር ሊያስወግደን ከሚፈልገው ሰው ታድነኛለህ ብዬ አስቤ ነው። 17እንዲሁም ንጉሥ ሆይ! ንጉሥ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆነና መልካሙን ከክፉው ለይቶ ስለሚያውቅ የተስፋ ቃልህ በሰላም እንድኖር ይረዳኛል ብዬ አስቤ ነው እንግዲህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን!” #2ሳሙ. 19፥27።
18ንጉሡም “አንድ ጥያቄ እጠይቅሻለሁ፤ አንቺም እውነቱን በሙሉ ንገሪኝ” አላት።
እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! የፈለግኸውን ጠይቀኝ” አለችው።
19እርሱም “ይህን እንድታደርጊ ያዘዘሽ ኢዮአብ ነውን?” ሲል ጠየቃት።
እርስዋም እንዲህ ስትል መልስ ሰጠች፤ “ንጉሥ ሆይ! አንተ ከምትለው ሁሉ ፈጽሞ ሊወጣ የሚችል እንደሌለ በአንተ ስም እምላለሁ፤ በእርግጥም ምን ማድረግና ምን ማለት እንዳለብኝ የመከረኝ የአንተ የጦር አዛዥ የሆነው ኢዮዓብ ነው። 20እርሱም ይህን ያደረገው ነገሮችን ሁሉ ለማስተካከል በማሰብ ነው፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ጥበበኛ ነህ፤ የሚሆነውንም ነገር ሁሉ ታውቃለህ።”
21ንጉሡም ዘግየት ብሎ ኢዮአብን “ተስማምቼአለሁና ሄደህ ያንን ወጣት አቤሴሎምን ፈልገህ ወደዚህ አምጣው” አለው።
22ኢዮአብም በዳዊት ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት በአክብሮት ንጉሡን አመሰገነ፤ “የፈለግኹትን እንዳደርግ በመፍቀድህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አሁን ተረዳሁ” አለ። 23ተነሥቶም ወደ ገሹር ሄደ፤ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አመጣው፤ 24ይሁን እንጂ ንጉሡ፥ አቤሴሎም በቤተ መንግሥት ውስጥ እንዳይኖር ትእዛዝ ሰጠ፤ ደግሞም ንጉሡ “ከቶ እርሱን ማየት አልፈልግም” አለ። ስለዚህ አቤሴሎም በራሱ ቤት ኖረ፤ ወደ ንጉሡም ፊት ቀርቦ አልታየም።
የአቤሴሎም ከዳዊት ጋር መታረቅ
25የአቤሴሎምን ያኽል በመልከ መልካምነቱ የታወቀ ሰው በእስራኤል ምድር ከቶ አልነበረም፤ አቤሴሎም ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩ ምንም እንከን የሌለበት ሰው ነበር፤ 26የራሱ ጠጒር እጅግ ብዙ ነበር፤ ስለሚረዝምበትና ስለሚከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ የጠጒሩም ክብደት በቤተ መንግሥት ሚዛን ሲለካ ከሁለት ኪሎ በላይ ነበር። 27አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ነበሩት፤ የሴት ልጁም ስም ትዕማር ሲሆን እርስዋም እጅግ ውብ ነበረች።
28አቤሴሎም ንጉሡን ሳያይ በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ኖረ፤ 29ከዚያን በኋላ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንዲጠይቅለት ኢዮአብን አስጠራ፤ ኢዮአብ ግን መምጣት አልፈቀደም፤ አቤሴሎም እንደገና ኢዮአብ እንዲመጣለት መልእክት ላከ፤ ኢዮአብ ግን አሁንም ሳይመጣ ቀረ፤ 30ስለዚህም አቤሴሎም አገልጋዮቹን “ተመልከቱ፤ የኢዮአብ እርሻ ከእኔ እርሻ ቀጥሎ ሲሆን የገብስ ሰብል ይገኝበታል፤ ስለዚህም ሂዱና በእሳት አቃጥሉት” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ሄደው ሰብሉን በእሳት አቃጠሉ።
31ኢዮአብም ወደ አቤሴሎም ቤት ገሥግሦ ሄደና “አገልጋዮችህ የእርሻዬን ሰብል ያቃጠሉት ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
32አቤሴሎምም “አንተ እኔ ስጠራህ ስላልመጣህ ነው፤ ወደ ንጉሡ ሄደህ ‘ከገሹር ወጥቼ ወደዚህ ለምን መጣሁ? እዚያው ቈይቼ ብሆን ኖሮ በተሻለኝ ነበር’ ብለህ ስለ እኔ ሁኔታ ጠይቅልኝ፤ እንዲሁም ከንጉሡ ጋር መገናኘት እችል ዘንድ ሁኔታዎችን አመቻችልኝ፤ እኔ በደለኛ ሆኜ ከተገኘሁ ሞት ይፍረድብኝ” አለው።
33ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ንጉሥ ዳዊት ሄደና አቤሴሎም ያለውን ሁሉ ነገረው፤ ንጉሡም አቤሴሎምን አስጠራ፤ አቤሴሎምም ሄዶ በንጉሡ ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም ሳመው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ