መዝሙር 39:9-13
መዝሙር 39:9-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህን ያደረግህ አንተ ነህና፣ ዝም እላለሁ፤ አፌንም አልከፍትም። ክንድህን አንሣልኝ፤ ከእጅህ ምት የተነሣ ደክሜአለሁ። ሰዎችን ስለ ኀጢአታቸው ለመቅጣት ትገሥጻቸዋለህ፤ ሀብታቸውንም ብል እንደ በላው ታደርጋለህ፤ በርግጥ ሰው ሁሉ ተን ብቻ ነው። ሴላ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤ ጩኸቴን አድምጥ፤ ልቅሶዬንም ቸል አትበል፤ በአንተ ፊት እኔ መጻተኛ ነኝና፤ እንደ አባቶቼም እንግዳ ነኝ። ላለመመለስ ከመሰናበቴ በፊት፣ ዳግመኛ ደስ ይለኝ ዘንድ ዐይንህን ከላዬ አንሣ።”
መዝሙር 39:9-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ፤ እነሆ፥ ከንፈሮችን አልከለክልም፤ አቤቱ፥ አንተ ጽድቄን ታውቃለህ። ቅንነትህን በልቤ ውስጥ አልሰወርሁም፥ ማዳንህንም ተናገርሁ፤ ይቅርታህንና ምሕረትህን ከታላቅ ጉባኤ አልሰወርሁም። አቤቱ አንተ ይቅርታህን ከእኔ አታርቅ፤ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ያግኙኝ። ቍጥር የሌላት ክፋት አግኝታኛለችና፤ ኀጢአቶቼ ተገናኙኝ፥ ማየትም ተስኖኛል፤ ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዙ፥ ልቤም ተወኝ። አቤቱ፥ ታድነኝ ዘንድ ፍቀድ፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ተመልከት።
መዝሙር 39:9-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህ ሁሉ እንዲደርስብኝ ያደረግኸው አንተ ስለ ሆንክ ዝም እላለሁ፤ አንድ ቃል እንኳ አልናገርም። ከጽኑ አመታትህ የተነሣ በጣም ስለ ተዳከምኩ መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ። ሰውን በኃጢአቱ ትገሥጸዋለህ፤ ትቀጣዋለህም፤ የሚወደውንም ነገር እንደ ብል ታጠፋበታለህ፤ በእርግጥ ሰው ከነፋስ ሽውታ የሚሻል አይደለም። እግዚአብሔር ሆይ! ጸሎቴን ስማ፤ ጩኸቴንም አድምጥ፤ ሳለቅስም ቶሎ ብለህ እርዳኝ፤ እኔ ለጥቂት ጊዜ የአንተ እንግዳ ነኝ፤ እንደ ቀድሞ አባቶቼም በስደተኛነት የምኖር ነኝ። ወደማልመለስበት ወደ ሞት ሳልሄድ ጥቂት ደስታ እንዳገኝ እባክህ ታገሠኝ።
መዝሙር 39:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከመተላለፌ ሁሉ አድነኝ፥ የሞኞች መሳለቂያ አታድርገኝ። አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም። መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና። በተግሣጽህ ስለ ኃጢአቱ ሰውን ዘለፍኸው፥ የሚመኘውንም እንደ ብል ታጠፋበታለህ፥ በእውነት ሰው ሁሉ ከንቱ ነው። አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ፥ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፥ እንደ አባቶቼም እንግዳ ነኝና።