ሉቃስ 9:1-36
ሉቃስ 9:1-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዐሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት ጠራና፦ በአጋንንት ሁሉ ላይ፥ ድውያንንም ይፈውሱ ዘንድ ኀይልንና ሥልጣንን ሰጣቸው። የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩ፥ ድውያንንና ሕሙማንንም ሁሉ እንዲፈውሱ ላካቸው። እንዲህም አላቸው፥ “በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ወርቅም ቢሆን፥ ሁለት ልብስም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ። በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ፤ እስክትሄዱም ድረስ ከዚያ አትውጡ። የማይቀበሉአችሁ ቢሆን ግን ከዚያች ከተማ ወጥታችሁ ምስክር ሊሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።” ወጥተውም በየአውራጃዉ መንደሮች ዞሩ፤ በስፍራውም ሁሉ ወንጌልን ሰበኩ፤ ድውያንንም ፈወሱ። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ሁሉ ሰምቶ የሚናገረውን ያጣ ነበር፤ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ የሚሉ ነበሩና። ኤልያስ ተገለጠ የሚሉም ነበሩ፤ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል የሚሉም ነበሩና። ሄሮድስም፥ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈረጥሁ፤ እንግዲህ ስለ እርሱ ሲወራ የምሰማው ይህ ማነው?” አለ፤ ሊያየውም ይሻ ነበር። ሐዋርያትም በተመለሱ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ለብቻቸው ይዞአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ አለ ምድረ በዳ ወጡ። ሕዝቡም ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀበላቸው፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም አስተማራቸው፤ ሊፈወሱ የሚሹትንም አዳናቸው። ቀኑም በመሸ ጊዜ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መጥተው፥ “ያለንበት ምድረ በዳ ነውና በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩ የሚበሉትንም እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት” አሉት። እርሱ ግን፥ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው” አላቸው፤ እነርሱም፥ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ልንገዛ ካልሄድን ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር ሌላ በዚህ የለንም” አሉት። ሰዎቹም አምስት ሺህ ያህሉ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱንም፥ “አምሳ አምሳውን በየክፍላቸው አስቀምጡአቸው” አላቸው። እንዲሁም አደረጉ፤ ሁሉም ተቀመጡ። አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ተመለከተ፤ ባረከ፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ያነሡትም የተረፈው ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞላ። ከዚህም በኋላ ብቻውን ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ሳሉ፥ “ሰዎች ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉህ አሉ፤ ኤልያስ ነው የሚሉህም አሉ፤ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል የሚሉህም አሉ” አሉት። እርሱም፥ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው፤ ጴጥሮስም መልሶ፥ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ” አለው። ይህንም ለማንም እንዳይናገሩ ገሠጻቸውና ከለከላቸው። “ለሰው ልጅ ብዙ መከራ ያጸኑበት ዘንድ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ይፈትኑት ዘንድ፥ ይገድሉትም ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ አለው” አላቸው። ሁሉንም እንዲህ አላቸው፥ “ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ይሸከም፤ ዕለት ዕለትም ይከተለኝ። ሰውነቱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ይጥላታል፤ ስለ እኔ ሰውነቱን የጣለ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱንም ካጣ ምን ይረባዋል? በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅ በክብሩ፥ በአባቱም ክብር፥ ቅዱሳንመላእክትን አስከትሎ ሲመጣ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩአት ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” ከዚህም ነገር በኋላ በስምንተኛው ቀን ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞአቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆነ፤ እንደ መብረቅም አብለጨለጨ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች መጥተው ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር። እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ። በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ይደረግ ዘንድ ያለውን ክብሩንና መውጣቱን ተናገሩ፤ ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ፈዝዘው አገኘ፤ በነቁም ጊዜ ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከዚህም በኋላ ከእርሱ ሲለዩ ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስን፥ “መምህር፥ ሆይ፥ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ሦስት ሰቀላዎችንም እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፥ አንዱንም ለሙሴ፥ አንዱንም ለኤልያስ” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፥ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ቃል መጣ። ቃሉም ከመጣ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ብቻውን ተገኘ፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ፤ ያዩትንና የሰሙትንም በዚያ ጊዜ ለማንም አልተናገሩም።
ሉቃስ 9:1-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ወደ ራሱ ጠርቶ አጋንንትን ሁሉ እንዲያወጡ፣ ደዌንም እንዲፈውሱ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ለመንገዳችሁ በትር፣ ከረጢት፣ እንጀራ፣ ገንዘብ፣ ወይም ትርፍ እጀ ጠባብ መያዝ አትያዙ። ከዚያ ከተማ እስከምትወጡ ድረስ መጀመሪያ በገባችሁበት በማንኛውም ቤት ቈዩ። የከተማው ሰዎች ሳይቀበሏችሁ ቀርተው ከተማቸውን ለቅቃችሁ ስትሄዱ፣ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።” እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም፣ በዚህ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ ሰምቶ በሁኔታው ተደናገረ፤ ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ዮሐንስ ከሙታን እንደ ተነሣ ያወሩ ነበር፤ ሌሎች ኤልያስ እንደ ተገለጠ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሙታን እንደ ተነሣ ይናገሩ ነበር። ሄሮድስም፣ “መጥምቁ ዮሐንስን እኔው ራሴ ዐንገቱን አስቈርጬው ሞቷል፤ ታዲያ፣ ስለ እርሱ እንዲህ ሲወራ የምሰማው ይህ ሰው ማነው?” አለ፤ በዐይኑም ሊያየው ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው በመጡ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ይዟቸው ቤተ ሳይዳ ወደምትባል ከተማ በመሄድ ለብቻው ገለል አለ። ሕዝቡም ይህንኑ ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀብሏቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው። ቀኑም ሊመሽ ሲል፣ ዐሥራ ሁለቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ያለነው በምድረ በዳ ስለ ሆነ፣ ሕዝቡ ወደ አካባቢው መንደርና ገጠር ሄደው ማደሪያና ምግብ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው” አሉት። እርሱ ግን፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ሄደን ካልገዛን በቀር፣ እኛ ያለን ከዐምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ አይበልጥም” አሉት፤ ዐምስት ሺሕ ያህል ወንዶች በዚያ ነበሩና። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሕዝቡን በዐምሳ፣ በዐምሳ ሰው መድባችሁ አስቀምጧቸው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በታዘዙት መሠረት ሰዎቹ እንዲቀመጡ አደረጉ። እርሱም ዐምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ባረካቸው፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከእነርሱ የተረፈውን ቍርስራሽ እንጀራ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ይጸልይ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ከርሱ ጋራ ነበሩ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞ ነቢያት አንዱ ከሙታን ተነሥቷል ይላሉ” አሉት። እርሱም፣ “እናንተስ ማን ነው ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ክርስቶስ ነህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት ዘንድ መናቅ፣ መገደልና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መነሣት አለበት” አላቸው። ከዚያም ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው? ማንም በእኔና በቃሌ ቢያፍር፣ የሰው ልጅ በግርማው እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ግርማ ሲመጣ ያፍርበታል። “እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳያዩ ሞትን የማይቀምሱ ሰዎች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ። በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እጅግ የሚያንጸባርቅ ሆነ። እነሆም፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋራ ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር። ጴጥሮስና ዐብረውት የነበሩት ግን እንቅልፍ ተጭኗቸው ነበር፤ ሲነቁ ግን ክብሩንና ከርሱ ጋራ የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ። ሰዎቹም ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናል” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር። ይህንም እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፣ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ነገሩን በልባቸው ያዙ እንጂ ስላዩት ነገር በዚያ ወቅት ለማንም አልተናገሩም።
ሉቃስ 9:1-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ፥ ሁለት እጀ ጠባብም አይሁንላችሁ። በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ ከዚያም ውጡ። ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ። ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ አንዳንድ ሰዎች፦ ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፥ ሌሎችም፦ ኤልያስ ተገለጠ፥ ሌሎችም፦ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይሉ ስለ ነበሩ አመነታ። ሄሮድስም፦ ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው? አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። ከእርሱ ጋርም ወስዶአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ ምድረ በዳ ለብቻው ፈቀቅ አለ። ሕዝቡም አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፥ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው። ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ አሥራ ሁለቱም ቀርበው፦ በዚህ በምድረ በዳ ነንና በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት። እርሱ ግን፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። እነርሱም፦ ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን፥ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም አሉት፤ አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ፦ በየክፍሉ አምሳ አምሳውን አስቀምጡአቸው አላቸው። እንዲህም አደረጉ ሁሉንም አስቀመጡአቸው። አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛርሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ ከእነርሱም የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ወሰዱ። ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና፦ ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው፦ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም፦ ኤልያስ፥ ሌሎችም፦ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይላሉ አሉት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ። እርሱ ግን፦ የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊጣል ሊገደልም በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባዋል ብሎ ለማንም ይህን እንዳይናገሩ አስጠንቅቆ አዘዘ። ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ። ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር። ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም።
ሉቃስ 9:1-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ወደ እርሱ ጠርቶ አጋንንትን የማውጣትና ደዌንም ሁሉ የመፈወስ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው። የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ለሰው ሁሉ እንዲነግሩ፥ በሽተኞችን እንዲፈውሱ ላካቸው። እንዲህም አላቸው፦ “ለመንገዳችሁ የሚሆን ምንም አትያዙ፤ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ ስንቅም ቢሆን፥ ገንዘብም ቢሆን፥ ቅያሬ ልብስም እንኳ ቢሆን አትያዙ። በእንግድነት በምትገቡበት ቤት ሁሉ ከዚያ መንደር ወጥታችሁ እስክትሄዱ ድረስ በዚያው ቈዩ። ሰዎች የማይቀበሉአችሁ ከሆነ ግን ያችን ከተማ ለቃችሁ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ሂዱ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።” ስለዚህ ሐዋርያቱ ከዚያ ወጥተው ወንጌልን እያስተማሩና በሽተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ሁሉ ያልፉ ነበር። አንዳንድ ሰዎች “መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶአል” እያሉ ያወሩ ስለ ነበረ የገሊላ አገረ ገዢ የነበረው ሄሮድስ ኢየሱስ ያደረገውን ሁሉ በመስማቱ ተደናገረ። እንዲሁም አንዳንዶቹ “ነቢዩ ኤልያስ ተመልሶ መጥቶአል፤” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሞት ተነሥቶአል፤” ይሉ ነበር። ሄሮድስም በበኩሉ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈርጬ ነበር፤ ታዲያ፥ ይህን ሁሉ ነገር ያደርጋል እየተባለ የሚነገርለት እርሱ ማን ነው?” ይል ነበር። ሊያየውም ይፈልግ ነበር። ሐዋርያት ከተላኩበት ተመልሰው መጡና ያደረጉትን ሁሉ ለኢየሱስ ነገሩት። እርሱም በቤተ ሳይዳ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው ገለልተኛ ቦታ ብቻቸውን ይዞአቸው ሄደ። ሕዝቡም ኢየሱስ የት እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ ተከተሉት፤ እርሱም ተቀበላቸውና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማራቸው፤ ከበሽታ መዳን ፈልገው የመጡትንም በሽተኞች ሁሉ ፈወሳቸው። ቀኑ ሊመሽ ሲል፥ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ይህ ያለንበት ቦታ በረሓ ነው፤ ስለዚህ ሰዎቹ በአካባቢው ወዳሉት ከተሞችና ገጠሮች ሄደው ምግብና ማደሪያ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው፤” አሉት። ኢየሱስ ግን “እናንተ ራሳችሁ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው። እነርሱም “እኛ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው፤ ስለዚህ ሄደን ምግብ ካልገዛን በቀር ለዚህ ሁሉ ሕዝብ አይበቃም፤” አሉት። የሰዎቹም ብዛት አምስት ሺህ ያኽል ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎቹ በኀምሳ፥ በኀምሳ ተከፋፍለው እንዲቀመጡ አድርጉአቸው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ልክ እርሱ እንዳዘዛቸው ሰዎቹን እንዲቀመጡ አደረጉ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ከሕዝቡ የተረፈውን ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። አንድ ቀን ኢየሱስ ብቻውን ሲጸልይ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው ከእርሱ ጋር ሆኑ፤ እርሱም፦ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶች ‘አጥማቂው ዮሐንስ ነው፤’ ሌሎች ‘ኤልያስ ነው፤’ ይሉሃል፤ ‘ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሞት ተነሥቶአል፥’ የሚሉም አሉ፤” ብለው መለሱለት። እናንተስ፥ “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ ጴጥሮስም፥ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች፥ በሕግ መምህራን ዘንድ ይናቃል፤ ይገደላልም፤ ይሁን እንጂ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።” ለሁሉም ደግሞ እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ በየቀኑም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ከእኔ ይልቅ ለሕይወቱ የሚሳሳ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል። ሰው የዓለምን ሀብት ሁሉ ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም በራሱ ክብርና በአባቱ ክብር፥ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። በእውነት እላችኋለሁ፤ አሁን እዚህ ካሉት መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ የማይሞቱ አንዳንዶች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና ያዕቆብን አስከትሎ ለመጸለይ ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ። በሚጸልይበትም ጊዜ መልኩ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ አንጸባረቀ፤ እነሆ፥ በድንገት ሁለት ሰዎች መጥተው ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ። በክብር ተገልጠው ይነጋገሩ የነበሩትም፥ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት ነበር። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና ጓደኞቹ በእንቅልፍ ተሸንፈው ተኝተው ነበር፤ በነቁ ጊዜ ግን የኢየሱስን ክብርና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሁለቱን ሰዎች አዩ። ሁለቱ ሰዎች ከኢየሱስ ተለይተው በሄዱ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ!” አለው፤ ጴጥሮስ ይህን ሲናገር የሚለውን አያውቅም ነበር። ጴጥሮስ ይህን ሲናገር ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ደመናውም በጋረዳቸው ጊዜ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፥ “የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከተሰማ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያዩትን ሁሉ በዚያን ጊዜ ለማንም ሳይናገሩ ዝም አሉ።
ሉቃስ 9:1-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በአንድነት ጠርቶ፥ በአጋንንት ሁሉ ላይ፥ እንዲሁም ደዌን እንዲፈውሱ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ሕሙማንን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ለመንገድ ምንም አትያዙ፤ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን፤ ሁለት እጀ ጠባብም አይኑራችሁ። በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ፤ ከዚያም ካረፋችሁበት ቤት ወጥታችሁ ሂዱ። ሰዎች በማይቀበሉአችሁ ጊዜ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው በእግራችሁ ላይ ያለውን ትቢያ አራግፉ።” ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በሁሉ ስፍራ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች፦ “ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፤” ሌሎችም “ኤልያስ ተገለጠ፤” ሌሎችም “ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤” ይሉ ስለ ነበር ግራ ተጋባ። ሄሮድስም፦ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈረጥሁ፤ ታዲያ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ይህ ማን ነው?” አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። እነርሱን ይዞ፥ ለብቻው ወደ ገለልተኛ ሰፈር፥ ቤተሳይዳ ወደምትባል ከተማ፥ ሄደ። ሕዝቡም ይህንን አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስም ያስፈልጋቸው የነበሩትንም ፈወሳቸው። ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ ዐሥራ ሁለቱም ቀርበው፦ “በዚህ በምድረ በዳ ስላለን በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት፤” አሉት። እርሱ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው። እነርሱም፦ “ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን በቀር ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም፤” አሉት፤ አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ፦ “በሃምሳ በሃምሳ እየከፈላችሁ አስቀምጡአቸው፤” አላቸው። እንዲህም አደረጉና ሁሉንም አስቀመጡአቸው። አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከእነርሱም የተረፈውን ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ። ለብቻውም ሲጸልይ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እርሱም፦ “ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው፦ “ ‘መጥምቁ ዮሐንስ፥’ ሌሎችም ‘ኤልያስ፥’ ሌሎችም ‘ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤’ ይላሉ፤” አሉት። እርሱም፦ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ “የእግዚአብሔር መሢሕ ነህ፤” አለ። እርሱ ግን ይህንን ለማንም እንዳይናገሩ እነርሱን አስጠንቅቆ በማዘዝ፦ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች፥ በጻፎችም ይናቃል፥ እንዲሁም ይገደላል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አለ። ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ በየዕለቱም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሎቼ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩና በአባቱ ክብር እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” ኢየሱስም እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ፥ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ ፀዳል አብረቅርቆ ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ፤ በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ሊፈጽመው ስላለ ሞቱ ይናገሩ ነበር። ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ነበር፤ ነቅተውም ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከእርሱም ሁለቱ ሰዎች በተለዩ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ “አቤቱ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ፥ አንድም ለሙሴ፥ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤” አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ሳለ ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ። ከደመናውም፦ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። እነርሱም ዝም አሉ፥ ያዩትንም ምንም ዓይነት ነገር በነዚያ ቀናት ለማንም አላወሩም።