የሉቃስ ወንጌል 9
9
ስለ ሐዋርያት መላክ
1ዐሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት ጠራና፦ በአጋንንት ሁሉ ላይ፥ ድውያንንም ይፈውሱ ዘንድ ኀይልንና ሥልጣንን ሰጣቸው። 2የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩ፥ ድውያንንና ሕሙማንንም ሁሉ እንዲፈውሱ ላካቸው። 3#ሉቃ. 10፥4-11፤ የሐዋ. 13፥51። እንዲህም አላቸው፥ “በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ወርቅም ቢሆን፥ ሁለት ልብስም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ። 4በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ፤ እስክትሄዱም ድረስ ከዚያ አትውጡ።#አንዳንድ ዘርዕ “ከዚያም ዉጡ” ይላል። 5የማይቀበሉአችሁ ቢሆን ግን ከዚያች ከተማ ወጥታችሁ ምስክር ሊሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።” 6ወጥተውም በየአውራጃዉ መንደሮች ዞሩ፤ በስፍራውም ሁሉ ወንጌልን ሰበኩ፤ ድውያንንም ፈወሱ።
ስለ ሄሮድስ ዐሳብ
7የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ሁሉ ሰምቶ የሚናገረውን ያጣ ነበር፤ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ የሚሉ ነበሩና። 8#ማቴ. 16፥14፤ ማር. 8፥28፤ ሉቃ. 9፥19። ኤልያስ ተገለጠ የሚሉም ነበሩ፤ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል የሚሉም ነበሩና። 9ሄሮድስም፥ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈረጥሁ፤ እንግዲህ ስለ እርሱ ሲወራ የምሰማው ይህ ማነው?” አለ፤ ሊያየውም ይሻ ነበር።
10ሐዋርያትም በተመለሱ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ለብቻቸው ይዞአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ አለ ምድረ በዳ ወጡ። 11ሕዝቡም ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀበላቸው፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም አስተማራቸው፤ ሊፈወሱ የሚሹትንም አዳናቸው።
ኅብስትን ስለ ማበርከቱ
12ቀኑም በመሸ ጊዜ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መጥተው፥ “ያለንበት ምድረ በዳ ነውና በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩ የሚበሉትንም እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት” አሉት። 13እርሱ ግን፥ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው” አላቸው፤ እነርሱም፥ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ልንገዛ ካልሄድን ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር ሌላ በዚህ የለንም” አሉት። 14ሰዎቹም አምስት ሺህ ያህሉ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱንም፥ “አምሳ አምሳውን በየክፍላቸው አስቀምጡአቸው” አላቸው። 15እንዲሁም አደረጉ፤ ሁሉም ተቀመጡ። 16አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ተመለከተ፤ ባረከ፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው። 17ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ያነሡትም የተረፈው ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞላ።
ሰው ማን ይለኛል? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ስለ መጠየቁ።
18ከዚህም በኋላ ብቻውን ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ሳሉ፥ “ሰዎች ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። 19#ማቴ. 14፥1-2፤ ማር. 6፥14-15፤ ሉቃ. 9፥7-8። እነርሱም መልሰው፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉህ አሉ፤ ኤልያስ ነው የሚሉህም አሉ፤ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል የሚሉህም አሉ” አሉት። 20#ዮሐ. 6፥68-69። እርሱም፥ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው፤ ጴጥሮስም መልሶ፥ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ” አለው። 21ይህንም ለማንም እንዳይናገሩ ገሠጻቸውና ከለከላቸው።
ስለ ሕማሙና ስለሚከተሉት የተናገረው
22“ለሰው ልጅ ብዙ መከራ ያጸኑበት ዘንድ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ይፈትኑት ዘንድ፥ ይገድሉትም ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ አለው” አላቸው። 23#ማቴ. 10፥38፤ ሉቃ. 14፥27። ሁሉንም እንዲህ አላቸው፥ “ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ይሸከም፤ ዕለት ዕለትም ይከተለኝ። 24#ማቴ. 10፥39፤ ሉቃ. 17፥33፤ ዮሐ. 12፥25። ሰውነቱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ይጥላታል፤ ስለ እኔ ሰውነቱን የጣለ ግን ያድናታል። 25ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱንም ካጣ ምን ይረባዋል? 26በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅ በክብሩ፥ በአባቱም ክብር፥ ቅዱሳንመላእክትን አስከትሎ ሲመጣ ያፍርበታል። 27እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩአት ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።”
በደብረ ታቦር ክብሩን ስለ መግለጡ
28ከዚህም ነገር በኋላ በስምንተኛው ቀን ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞአቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 29ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆነ፤ እንደ መብረቅም አብለጨለጨ። 30እነሆም፥ ሁለት ሰዎች መጥተው ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር። እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ። 31በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ይደረግ ዘንድ ያለውን ክብሩንና#በግሪኩ “ክብሩን ...” አይልም። መውጣቱን ተናገሩ፤ 32ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ፈዝዘው አገኘ፤ በነቁም ጊዜ ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። 33ከዚህም በኋላ ከእርሱ ሲለዩ ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስን፥ “መምህር፥ ሆይ፥ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ሦስት ሰቀላዎችንም እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፥ አንዱንም ለሙሴ፥ አንዱንም ለኤልያስ” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር። 34ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ። 35#ኢሳ. 42፥1፤ ማቴ. 3፥17፤ 12፥18፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22። ከደመናውም ውስጥ፥ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ቃል መጣ። 36ቃሉም ከመጣ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ብቻውን ተገኘ፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ፤ ያዩትንና የሰሙትንም በዚያ ጊዜ ለማንም አልተናገሩም።
ጋኔን ይጥለው የነበረውን ስለ ማዳኑ
37በሁለተኛውም ቀን ከተራራው ወረዱ፤ ብዙ ሕዝብም ተቀበሉት። 38አንድ ሰውም በሕዝቡ መካከል ጮኾ እንዲህ አለው፥ “መምህር ሆይ፥ እርሱ ለእኔ አንድ ነውና ልጄን ታይልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። 39እነሆ፥ ጋኔን ሊነጥቀኝ ነው፤#“ሊነጥቀኝ ነው” የሚለው በግሪኩ አይገኝም። ድንገትም ያስጮኸዋል፤ ጥሎም ያፈራግጠዋል፤ አረፋም ያስደፍቀዋል፤ ቀጥቅጦ በጭንቅ ይተወዋል። 40እንዲያወጡትም ደቀ መዛሙርትህን ለመንሁአቸው፤ ነገር ግን ማውጣት ተሳናቸው።” 41ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “የማታምን ከዳተኛ ትውልድ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለው። 42ሲያመጣውም ጋኔኑ ጣለውና አፈራገጠው፤ ጌታችን ኢየሱስም ያን ክፉ ጋኔን ገሠጸው፤ ልጁንም አዳነው፤ ለአባቱም ሰጠው። ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ አደነቁ።
ስለ ሕማሙ
43እነርሱም ጌታችን ኢየሱስ ባደረገው ተአምራት ሁሉ ሲደነቁ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው። 44“እናንተስ ይህን ነገር በልባችሁ#በግሪኩ “በጆሮአችሁ አኑሩት” ይላል። አኑሩት፤ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ አለውና።” 45እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉትም፤ እንዳይመረምሩት ከእነርሱ የተሰወረ ነውና፤ ስለዚህ ነገርም እንዳይጠይቁት ይፈሩት ነበርና።
ስለ ትሕትና
46 #
ሉቃ. 22፥24። እርስ በርሳቸውም ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ ዐሰቡ። 47ጌታችን ኢየሱስም በልቡናቸው የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና አንድ ሕፃን ወስዶ በመካከላቸው አቆመው። 48#ማቴ. 10፥40፤ ሉቃ. 10፥16፤ ዮሐ. 13፥20። እንዲህም አላቸው፥ “በስሜ እንደዚህ ያለውን ሕፃን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፤ ራሱን ከሁሉ#በግሪኩ “ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ይሆናል” ይላል። ዝቅ የሚያደርግ እርሱ ታላቅ ይሆናል።”
49ዮሐንስም መልሶ፥ “መምህር ሆይ፥ በስምህ ጋኔን ሲያወጣ ያየነው አንድ ሰው አለ፤ ከእኛም ጋር አልተከተለህምና ከለከልነው፤” አለው። 50ጌታችን ኢየሱስም፥ “አትከልክሉት፤ ባለጋራችሁ ካልሆነ ባልንጀራችሁ#በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ከእናንተ ጋር ነውና” ይላል። ነውና” አላቸው። 51የመውጣቱ ወራትም በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና። 52በፊቱም መልእክተኞችን ላከ፤ ሄደውም ያዘጋጁለት ዘንድ ወደ ሰማርያ ከተማ ገቡ። 53ነገር ግን አልተቀበሉትም፤ ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅንቶ ነበርና። 54#2ነገ. 1፥9-16። ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስም ይህን ባዩ ጊዜ፥ “አቤቱ፥ ኤልያስ እንደ አደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንድንል ትፈቅዳለህን?” አሉት። 55እርሱ ግን ዘወር ብሎ፥ “ከምን መንፈስ እንደ ሆናችሁ አታውቁም” ብሎ ገሠጻቸው። 56የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም። ወደ ሌላም መንደር ሄዱ።
ሊከተሉት ስለ ጠየቁት ሰዎች
57ከዚህ በኋላ በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው፥ “መምህር፥ ወደምትሄድበት ልከተልህን?” አለው። 58ጌታችን ኢየሱስም “ለቀበሮዎች ጕድጓድ አላቸው፤ ለሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” አለው። 59ሌላውንም፥ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱ ግን፥ “አቤቱ፥ በፊት ሄጄ አባቴን እንድቀብረው ፍቀድልኝ” አለው። 60ጌታችን ኢየሱስም፥ “ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዉአቸው፤ አንተ ግን ሂድና የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው። 61#1ነገ. 19፥20። ሦስተኛውም፥ “አቤቱ፥ ልከተልህን? ነገር ግን ሄጄ ቤተ ሰቦችን ሁሉ እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለው። 62ጌታችን ኢየሱስም፥ “ማንም ዕርፍ ይዞ እያረሰ ወደ ኋላው የሚመለከት#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ዕርፍ ይዞ ወደኋላ የሚያርስ የለም የእግዚአብሔር መንግሥት የቀናች ናትና” ይላል። ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይሆንም” አለው።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 9: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ