የሉቃስ ወንጌል 9
9
ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ለማስተማር መላኩ
(ማቴ. 10፥5-15፤ ማር. 6፥7-13)
1ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በአንድነት ጠርቶ፥ በአጋንንት ሁሉ ላይ፥ እንዲሁም ደዌን እንዲፈውሱ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ 2የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ሕሙማንን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ 3እንዲህም አላቸው፦ “ለመንገድ ምንም አትያዙ፤ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን፤ ሁለት እጀ ጠባብም አይኑራችሁ። 4በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ፤ ከዚያም ካረፋችሁበት ቤት ወጥታችሁ ሂዱ። 5#የሐዋ. 13፥51።#ሉቃ. 10፥4-11።ሰዎች በማይቀበሉአችሁ ጊዜ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው በእግራችሁ ላይ ያለውን ትቢያ አራግፉ።” 6ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በሁሉ ስፍራ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።
የሄሮድስ ግራ መጋባት
(ማቴ. 14፥1-12፤ ማር. 6፥14-29)
7 #
ማቴ. 16፥14፤ ማር. 8፥28፤ ሉቃ. 9፥19። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች፦ “ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፤” 8ሌሎችም “ኤልያስ ተገለጠ፤” ሌሎችም “ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤” ይሉ ስለ ነበር ግራ ተጋባ። 9ሄሮድስም፦ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈረጥሁ፤ ታዲያ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ይህ ማን ነው?” አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር።
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መመገቡ
(ማቴ. 14፥13-21፤ ማር. 6፥30-44፤ ዮሐ. 6፥1-14)
10ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። እነርሱን ይዞ፥ ለብቻው ወደ ገለልተኛ ሰፈር፥ ቤተሳይዳ ወደምትባል ከተማ፥ ሄደ። 11ሕዝቡም ይህንን አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስም ያስፈልጋቸው የነበሩትንም ፈወሳቸው። 12ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ ዐሥራ ሁለቱም ቀርበው፦ “በዚህ በምድረ በዳ ስላለን በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት፤” አሉት። 13እርሱ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው። እነርሱም፦ “ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን በቀር ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም፤” አሉት፤ 14አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ፦ “በሃምሳ በሃምሳ እየከፈላችሁ አስቀምጡአቸው፤” አላቸው። 15እንዲህም አደረጉና ሁሉንም አስቀመጡአቸው። 16አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። 17ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከእነርሱም የተረፈውን ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ።
ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ጴጥሮስ መመስከሩ
(ማቴ. 16፥13-19፤ ማር. 8፥27-29)
18ለብቻውም ሲጸልይ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እርሱም፦ “ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። 19#ማቴ. 14፥1፤2፤ ማር. 6፥14፤15፤ ሉቃ. 9፥7፤8።እነርሱም መልሰው፦ “ ‘መጥምቁ ዮሐንስ፥’ ሌሎችም ‘ኤልያስ፥’ ሌሎችም ‘ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤’ ይላሉ፤” አሉት። 20#ዮሐ. 6፥68፤69።እርሱም፦ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ “የእግዚአብሔር መሢሕ ነህ፤” አለ።
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው አስቀድሞ መናገሩ
(ማቴ. 16፥20-28፤ ማር. 8፥34-38)
21እርሱ ግን ይህንን ለማንም እንዳይናገሩ እነርሱን አስጠንቅቆ በማዘዝ፦ 22“የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች፥ በጻፎችም ይናቃል፥ እንዲሁም ይገደላል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አለ። 23#ማቴ. 10፥38፤ ሉቃ. 14፥27።ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ በየዕለቱም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ። 24#ማቴ. 10፥39፤ ሉቃ. 17፥33፤ ዮሐ. 12፥25።ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። 25ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? 26በእኔና በቃሎቼ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩና በአባቱ ክብር እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። 27እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።”
የኢየሱስ መልክ እንደ ተለወጠ
(ማቴ. 17፥1-8፤ ማር. 9፥2-8)
28ኢየሱስም እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ፥ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 29ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ ፀዳል አብረቅርቆ ነጭ ሆነ። 30እነሆም፥ ሁለት ሰዎች ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ፤ 31በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ሊፈጽመው ስላለ ሞቱ ይናገሩ ነበር። 32ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ነበር፤ ነቅተውም ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። 33ከእርሱም ሁለቱ ሰዎች በተለዩ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ “አቤቱ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ፥ አንድም ለሙሴ፥ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤” አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። 34ይህንም ሲናገር ሳለ ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ። 35#ኢሳ. 42፥1፤ ማቴ. 3፥17፤ 12፥18፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22።#2ጴጥ. 1፥17፤18።ከደመናውም፦ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤” የሚል ድምፅ መጣ። 36ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። እነርሱም ዝም አሉ፥ ያዩትንም ምንም ዓይነት ነገር በነዚያ ቀናት ለማንም አላወሩም።
ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን ልጅ መፈወሱ
(ማቴ. 17፥14-18፤ ማር. 9፥14-28)
37በማግስቱም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኘው። 38እነሆም፥ ከሕዝቡ አንድ ሰው እንዲህ እያለ ጮኸ፦ “መምህር ሆይ! ለእኔ ብቸኛ ልጄ ነውና፥ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። 39እነሆም፥ ርኩስ መንፈስ ይይዘዋል፤ ድንገትም ይጮኻል፤ አረፋም እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ አድቅቆ በጭንቅ ይለቀዋል፤ 40ደቀ መዛሙርትህንም እንዲያወጡት ለመንሁ፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” 41ኢየሱስም መልሶ፦ “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው፤” አለ። 42ልጁም በመምጣት ላይ ሳለ ጋኔኑ ጣለውና አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ብላቴናውን ፈወሰው፤ ልጁንም ለአባቱ መልሶ ሰጠው።
ኢየሱስ ስለ ሞቱ ዳግመኛ መናገሩ
(ማቴ. 17፥22-23፤ ማር. 9፥30-32)
43ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ። ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ሁሉ ሲደነቁ ሳሉ፥ እርሱ ለደቀ መዛሙርቱ፦ 44“የሰው ልጅ በሰው እጅ ተላልፎ የሚሰጥ ስለሆነ እናንተ እነዚህን ቃላት በጆሮዎቻችሁ አኑሩ፤” አለ። 45እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፤ እንዳይገባቸውም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህም ነገር እርሱን ለመጠየቅ ፈሩ።
ስለ ትሕትና
(ማቴ. 18፥1-5፤ ማር. 9፥33-40)
46 #
ሉቃ. 22፥24። ከእነርሱም መካከል ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ። 47ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ አንድ ሕፃን ወሰደና፥ በአጠገቡም አቁሞት፦ 48#ማቴ. 10፥40፤ ሉቃ. 10፥16፤ ዮሐ. 13፥20።“ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ በእናንተ መካከል ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና፤” አላቸው።
49ዮሐንስም መልሶ፦ “አቤቱ! አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፤ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው” አለው። 50ኢየሱስ ግን፦ “የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት፤” አለው።
51ኢየሱስ የሚያርግበት ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፤ 52እርሱም አስቀድሞ መልክተኞችን ላከ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንዲት የሳምራውያን መንደር ገቡ፤ 53ነገር ግን ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ ፊቱን አቅንቶ ስለ ነበረ የመንደሩ ሰዎች አልተቀበሉትም። 54#2ነገ. 1፥9-16።ደቀመዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው፦ “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እንዲበላቸው እንድናዝዝ ትወዳለህን?” አሉት። 55እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸው። 56ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።
ኢየሱስን ለመከተል የፈለጉ ሰዎች
(ማቴ. 8፥19-22)
57እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ ሳሉ አንድ ሰው ኢየሱስን፦ “አንተ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ፤” አለው። 58ኢየሱስም፦ “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች ጎጆ አላቸው፤ ለሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ምንም ስፍራ የለውም፤” አለው። 59ሌላውንም፦ “ተከተለኝ፤” አለው። እርሱ ግን፦ “ጌታ ሆይ! መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፤” አለ። 60ኢየሱስም፦ “ሙታኖቻቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት አስተምር፤” አለው። 61#1ነገ. 19፥20።እንዲሁም ሌላው፦ “ጌታ ሆይ! እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ሄጄ በቤቴ ያሉትን እንድሰናበት ፍቀድልኝ፥” አለ። 62ኢየሱስ ግን፦ “የሞፈሩን ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ማንም ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም፤” አለው።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ