ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በአንድነት ጠርቶ፥ በአጋንንት ሁሉ ላይ፥ እንዲሁም ደዌን እንዲፈውሱ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ሕሙማንን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ለመንገድ ምንም አትያዙ፤ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን፤ ሁለት እጀ ጠባብም አይኑራችሁ። በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ፤ ከዚያም ካረፋችሁበት ቤት ወጥታችሁ ሂዱ። ሰዎች በማይቀበሉአችሁ ጊዜ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው በእግራችሁ ላይ ያለውን ትቢያ አራግፉ።” ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በሁሉ ስፍራ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች፦ “ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፤” ሌሎችም “ኤልያስ ተገለጠ፤” ሌሎችም “ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤” ይሉ ስለ ነበር ግራ ተጋባ። ሄሮድስም፦ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈረጥሁ፤ ታዲያ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ይህ ማን ነው?” አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። እነርሱን ይዞ፥ ለብቻው ወደ ገለልተኛ ሰፈር፥ ቤተሳይዳ ወደምትባል ከተማ፥ ሄደ። ሕዝቡም ይህንን አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስም ያስፈልጋቸው የነበሩትንም ፈወሳቸው። ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ ዐሥራ ሁለቱም ቀርበው፦ “በዚህ በምድረ በዳ ስላለን በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት፤” አሉት። እርሱ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው። እነርሱም፦ “ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን በቀር ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም፤” አሉት፤ አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ፦ “በሃምሳ በሃምሳ እየከፈላችሁ አስቀምጡአቸው፤” አላቸው። እንዲህም አደረጉና ሁሉንም አስቀመጡአቸው። አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከእነርሱም የተረፈውን ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ። ለብቻውም ሲጸልይ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እርሱም፦ “ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው፦ “ ‘መጥምቁ ዮሐንስ፥’ ሌሎችም ‘ኤልያስ፥’ ሌሎችም ‘ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤’ ይላሉ፤” አሉት። እርሱም፦ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ “የእግዚአብሔር መሢሕ ነህ፤” አለ። እርሱ ግን ይህንን ለማንም እንዳይናገሩ እነርሱን አስጠንቅቆ በማዘዝ፦ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች፥ በጻፎችም ይናቃል፥ እንዲሁም ይገደላል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አለ። ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ በየዕለቱም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሎቼ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩና በአባቱ ክብር እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” ኢየሱስም እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ፥ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ ፀዳል አብረቅርቆ ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ፤ በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ሊፈጽመው ስላለ ሞቱ ይናገሩ ነበር። ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ነበር፤ ነቅተውም ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከእርሱም ሁለቱ ሰዎች በተለዩ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ “አቤቱ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ፥ አንድም ለሙሴ፥ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤” አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ሳለ ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ። ከደመናውም፦ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። እነርሱም ዝም አሉ፥ ያዩትንም ምንም ዓይነት ነገር በነዚያ ቀናት ለማንም አላወሩም።
የሉቃስ ወንጌል 9 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 9
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 9:1-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos