ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ወደ እርሱ ጠርቶ አጋንንትን የማውጣትና ደዌንም ሁሉ የመፈወስ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው። የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ለሰው ሁሉ እንዲነግሩ፥ በሽተኞችን እንዲፈውሱ ላካቸው። እንዲህም አላቸው፦ “ለመንገዳችሁ የሚሆን ምንም አትያዙ፤ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ ስንቅም ቢሆን፥ ገንዘብም ቢሆን፥ ቅያሬ ልብስም እንኳ ቢሆን አትያዙ። በእንግድነት በምትገቡበት ቤት ሁሉ ከዚያ መንደር ወጥታችሁ እስክትሄዱ ድረስ በዚያው ቈዩ። ሰዎች የማይቀበሉአችሁ ከሆነ ግን ያችን ከተማ ለቃችሁ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ሂዱ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።” ስለዚህ ሐዋርያቱ ከዚያ ወጥተው ወንጌልን እያስተማሩና በሽተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ሁሉ ያልፉ ነበር። አንዳንድ ሰዎች “መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶአል” እያሉ ያወሩ ስለ ነበረ የገሊላ አገረ ገዢ የነበረው ሄሮድስ ኢየሱስ ያደረገውን ሁሉ በመስማቱ ተደናገረ። እንዲሁም አንዳንዶቹ “ነቢዩ ኤልያስ ተመልሶ መጥቶአል፤” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሞት ተነሥቶአል፤” ይሉ ነበር። ሄሮድስም በበኩሉ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈርጬ ነበር፤ ታዲያ፥ ይህን ሁሉ ነገር ያደርጋል እየተባለ የሚነገርለት እርሱ ማን ነው?” ይል ነበር። ሊያየውም ይፈልግ ነበር። ሐዋርያት ከተላኩበት ተመልሰው መጡና ያደረጉትን ሁሉ ለኢየሱስ ነገሩት። እርሱም በቤተ ሳይዳ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው ገለልተኛ ቦታ ብቻቸውን ይዞአቸው ሄደ። ሕዝቡም ኢየሱስ የት እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ ተከተሉት፤ እርሱም ተቀበላቸውና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማራቸው፤ ከበሽታ መዳን ፈልገው የመጡትንም በሽተኞች ሁሉ ፈወሳቸው። ቀኑ ሊመሽ ሲል፥ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ይህ ያለንበት ቦታ በረሓ ነው፤ ስለዚህ ሰዎቹ በአካባቢው ወዳሉት ከተሞችና ገጠሮች ሄደው ምግብና ማደሪያ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው፤” አሉት። ኢየሱስ ግን “እናንተ ራሳችሁ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው። እነርሱም “እኛ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው፤ ስለዚህ ሄደን ምግብ ካልገዛን በቀር ለዚህ ሁሉ ሕዝብ አይበቃም፤” አሉት። የሰዎቹም ብዛት አምስት ሺህ ያኽል ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎቹ በኀምሳ፥ በኀምሳ ተከፋፍለው እንዲቀመጡ አድርጉአቸው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ልክ እርሱ እንዳዘዛቸው ሰዎቹን እንዲቀመጡ አደረጉ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ከሕዝቡ የተረፈውን ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። አንድ ቀን ኢየሱስ ብቻውን ሲጸልይ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው ከእርሱ ጋር ሆኑ፤ እርሱም፦ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶች ‘አጥማቂው ዮሐንስ ነው፤’ ሌሎች ‘ኤልያስ ነው፤’ ይሉሃል፤ ‘ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሞት ተነሥቶአል፥’ የሚሉም አሉ፤” ብለው መለሱለት። እናንተስ፥ “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ ጴጥሮስም፥ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች፥ በሕግ መምህራን ዘንድ ይናቃል፤ ይገደላልም፤ ይሁን እንጂ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።” ለሁሉም ደግሞ እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ በየቀኑም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ከእኔ ይልቅ ለሕይወቱ የሚሳሳ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል። ሰው የዓለምን ሀብት ሁሉ ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም በራሱ ክብርና በአባቱ ክብር፥ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። በእውነት እላችኋለሁ፤ አሁን እዚህ ካሉት መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ የማይሞቱ አንዳንዶች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና ያዕቆብን አስከትሎ ለመጸለይ ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ። በሚጸልይበትም ጊዜ መልኩ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ አንጸባረቀ፤ እነሆ፥ በድንገት ሁለት ሰዎች መጥተው ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ። በክብር ተገልጠው ይነጋገሩ የነበሩትም፥ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት ነበር። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና ጓደኞቹ በእንቅልፍ ተሸንፈው ተኝተው ነበር፤ በነቁ ጊዜ ግን የኢየሱስን ክብርና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሁለቱን ሰዎች አዩ። ሁለቱ ሰዎች ከኢየሱስ ተለይተው በሄዱ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ!” አለው፤ ጴጥሮስ ይህን ሲናገር የሚለውን አያውቅም ነበር። ጴጥሮስ ይህን ሲናገር ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ደመናውም በጋረዳቸው ጊዜ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፥ “የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከተሰማ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያዩትን ሁሉ በዚያን ጊዜ ለማንም ሳይናገሩ ዝም አሉ።
የሉቃስ ወንጌል 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 9:1-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos