የሉቃስ ወንጌል 9
9
ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለማስተማር መላካቸው
(ማቴ. 10፥5-15፤ ማር. 6፥7-13)
1ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ወደ እርሱ ጠርቶ አጋንንትን የማውጣትና ደዌንም ሁሉ የመፈወስ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው። 2የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ለሰው ሁሉ እንዲነግሩ፥ በሽተኞችን እንዲፈውሱ ላካቸው። 3እንዲህም አላቸው፦ “ለመንገዳችሁ የሚሆን ምንም አትያዙ፤ በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ ስንቅም ቢሆን፥ ገንዘብም ቢሆን፥ ቅያሬ ልብስም እንኳ ቢሆን አትያዙ። #ሉቃ. 10፥4-11፤ ሐ.ሥ. 13፥51። 4በእንግድነት በምትገቡበት ቤት ሁሉ ከዚያ መንደር ወጥታችሁ እስክትሄዱ ድረስ በዚያው ቈዩ። 5ሰዎች የማይቀበሉአችሁ ከሆነ ግን ያችን ከተማ ለቃችሁ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ሂዱ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።”
6ስለዚህ ሐዋርያቱ ከዚያ ወጥተው ወንጌልን እያስተማሩና በሽተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ሁሉ ያልፉ ነበር።
ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ ዝና መስማቱ
(ማቴ. 14፥1-12፤ ማር. 6፥14-29)
7አንዳንድ ሰዎች “መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶአል” እያሉ ያወሩ ስለ ነበረ የገሊላ አገረ ገዢ የነበረው ሄሮድስ ኢየሱስ ያደረገውን ሁሉ በመስማቱ ተደናገረ። 8እንዲሁም አንዳንዶቹ “ነቢዩ ኤልያስ ተመልሶ መጥቶአል፤” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሞት ተነሥቶአል፤” ይሉ ነበር። #ማቴ. 16፥14፤ ማር. 8፥28፤ ሉቃ. 9፥19። 9ሄሮድስም በበኩሉ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈርጬ ነበር፤ ታዲያ፥ ይህን ሁሉ ነገር ያደርጋል እየተባለ የሚነገርለት እርሱ ማን ነው?” ይል ነበር። ሊያየውም ይፈልግ ነበር። #ማቴ. 14፥1-2፤ ማር. 6፥14-15፤ ሉቃ. 9፥7-8።
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መመገቡ
(ማቴ. 14፥13-21፤ ማር. 6፥30-44፤ ዮሐ. 6፥1-14)
10ሐዋርያት ከተላኩበት ተመልሰው መጡና ያደረጉትን ሁሉ ለኢየሱስ ነገሩት። እርሱም በቤተ ሳይዳ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው ገለልተኛ ቦታ ብቻቸውን ይዞአቸው ሄደ። 11ሕዝቡም ኢየሱስ የት እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ ተከተሉት፤ እርሱም ተቀበላቸውና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማራቸው፤ ከበሽታ መዳን ፈልገው የመጡትንም በሽተኞች ሁሉ ፈወሳቸው።
12ቀኑ ሊመሽ ሲል፥ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ይህ ያለንበት ቦታ በረሓ ነው፤ ስለዚህ ሰዎቹ በአካባቢው ወዳሉት ከተሞችና ገጠሮች ሄደው ምግብና ማደሪያ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው፤” አሉት።
13ኢየሱስ ግን “እናንተ ራሳችሁ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው።
እነርሱም “እኛ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው፤ ስለዚህ ሄደን ምግብ ካልገዛን በቀር ለዚህ ሁሉ ሕዝብ አይበቃም፤” አሉት። 14የሰዎቹም ብዛት አምስት ሺህ ያኽል ነበር።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎቹ በኀምሳ፥ በኀምሳ ተከፋፍለው እንዲቀመጡ አድርጉአቸው” አላቸው።
15ደቀ መዛሙርቱም ልክ እርሱ እንዳዘዛቸው ሰዎቹን እንዲቀመጡ አደረጉ። 16ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ 17ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ከሕዝቡ የተረፈውን ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ።
ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ጴጥሮስ መግለጡ
(ማቴ. 16፥13-19፤ ማር. 8፥27-29)
18አንድ ቀን ኢየሱስ ብቻውን ሲጸልይ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው ከእርሱ ጋር ሆኑ፤ እርሱም፦ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ጠየቃቸው።
19እነርሱም “አንዳንዶች ‘አጥማቂው ዮሐንስ ነው፤’ ሌሎች ‘ኤልያስ ነው፤’ ይሉሃል፤ ‘ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሞት ተነሥቶአል፥’ የሚሉም አሉ፤” ብለው መለሱለት።
20እናንተስ፥ “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤
ጴጥሮስም፥ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። 21ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው።
ክርስቶስን መከተል የሚጠይቀው መሥዋዕትነት
(ማቴ. 10፥38-39፤ 16፥24-28፤ ማር. 8፥34-38፤ ሉቃ. 14፥25-27)
22ቀጥሎም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች፥ በሕግ መምህራን ዘንድ ይናቃል፤ ይገደላልም፤ ይሁን እንጂ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።”
23ለሁሉም ደግሞ እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ በየቀኑም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ፤ #ማቴ. 10፥38፤ ሉቃ. 14፥27። 24ከእኔ ይልቅ ለሕይወቱ የሚሳሳ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል። #ማቴ. 10፥39፤ ሉቃ. 17፥33፤ ዮሐ. 12፥25። 25ሰው የዓለምን ሀብት ሁሉ ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? 26በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም በራሱ ክብርና በአባቱ ክብር፥ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። 27በእውነት እላችኋለሁ፤ አሁን እዚህ ካሉት መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ የማይሞቱ አንዳንዶች አሉ።”
የኢየሱስ መልክ መለወጥ
(ማቴ. 17፥1-8፤ ማር. 9፥2-8)
28ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና ያዕቆብን አስከትሎ ለመጸለይ ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ። 29በሚጸልይበትም ጊዜ መልኩ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ አንጸባረቀ፤ 30እነሆ፥ በድንገት ሁለት ሰዎች መጥተው ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ። 31በክብር ተገልጠው ይነጋገሩ የነበሩትም፥ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት ነበር። 32በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና ጓደኞቹ በእንቅልፍ ተሸንፈው ተኝተው ነበር፤ በነቁ ጊዜ ግን የኢየሱስን ክብርና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሁለቱን ሰዎች አዩ። 33ሁለቱ ሰዎች ከኢየሱስ ተለይተው በሄዱ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ!” አለው፤ ጴጥሮስ ይህን ሲናገር የሚለውን አያውቅም ነበር።
34ጴጥሮስ ይህን ሲናገር ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ደመናውም በጋረዳቸው ጊዜ ፈሩ። 35ከደመናውም ውስጥ፥ “የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። #ኢሳ. 42፥1፤ ማቴ. 3፥17፤ 12፥18፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22።
36ድምፁም ከተሰማ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያዩትን ሁሉ በዚያን ጊዜ ለማንም ሳይናገሩ ዝም አሉ።
ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ያደረባትን ልጅ መፈወሱ
(ማቴ. 17፥14-18፤ ማር. 9፥14-27)
37በማግስቱ ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ከተራራው በወረዱ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን ተገናኙት። 38ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጮኸ! “መምህር ሆይ፥ ይህ ለኔ አንድ ልጅ ነውና እንድታድንልኝ እለምንሃለሁ፤ 39እነሆ! ርኩስ መንፈስ በድንገት ይዞ ያስጮኸዋል፤ በመሬት ላይ ጥሎ ዐረፋ እያስደፈቀ ያንፈራግጠዋል፤ ሰውነቱንም እያቈሰለ በአሳር ይለቀዋል። 40ርኩሱን መንፈስ እንዲያስወጡለት ደቀ መዛሙርትህን ጠይቄአቸው ነበር፤ ነገር ግን አልቻሉም።”
41ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እናንተ እምነት የሌላችሁ ጠማማ ትውልድ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጅህን ወዲህ አምጣው።”
42ልጁም ወደ ኢየሱስ በቀረበ ጊዜ ጋኔኑ በመሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው፤ ልጁንም ፈውሶ ለአባቱ ሰጠው። 43ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅ ኀይል በማየታቸው ተገረሙ፤
ኢየሱስ ስለ ሞቱ ለሁለተኛ ጊዜ መናገሩ
(ማቴ. 17፥22-23፤ ማር. 9፥30-32)
ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ነገር በመደነቅ ላይ ሳሉ እርሱ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 44“ይህን የምነግራችሁን ቃል ልብ ብላችሁ አስተውሉ! እነሆ፥ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል።” 45እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፤ የንግግሩም ምሥጢር ተሰውሮባቸው ነበር፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።
ከሁሉ የሚበልጥ
(ማቴ. 18፥1-5፤ ማር. 9፥33-37)
46ደቀ መዛሙርቱ “ከእኛ ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” በማለት ክርክር አንሥተው ነበር። #ሉቃ. 22፥24። 47ኢየሱስ ግን የልባቸውን ሐሳብ ዐውቆ አንድ ሕፃን ልጅ አመጣና በአጠገቡ አቆመው፤ 48እርሱም “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ የላከኝን ይቀበላል። ከእናንተ መካከል ከሁላችሁም የሚያንስ እርሱ ከሁሉ የሚበልጥ ይሆናል፤” አላቸው። #ማቴ. 10፥40፤ ሉቃ. 10፥16፤ ዮሐ. 13፥20።
የማይቃወም ሁሉ ተባባሪ መሆኑ
(ማር. 9፥38-40)
49ከዚህም በኋላ ዮሐንስ ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፤ ነገር ግን ከእኛ ጋር ስላልሆነ ከለከልነው፤” አለ።
50ኢየሱስም “የማይቃወማችሁ ሁሉ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነ ተዉ፤ አትከልክሉት!” አለ።
የሰማርያ ሰዎች ኢየሱስን ለመቀበል አለመፈለጋቸው
51ኢየሱስ የሚያርግበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ። 52ከእርሱ በፊት ቀድመው የሚሄዱትንም መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ሁሉን ነገር ለማዘጋጀት በሰማርያ ወደምትገኘው ወደ አንዲት መንደር ሄዱ። 53ነገር ግን እርሱ በዚያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄድ መሆኑን ዐውቀው ስለ ነበር የዚያች መንደር ሰዎች ሊቀበሉት አልፈለጉም። 54ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እነዚህን ሰዎች ያቃጥላቸው ዘንድ እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። #2ነገ. 1፥9-16። #9፥54 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “ኤልያስ እንዳደረገ” የሚል ቃል ይጨምራሉ።
55ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ ገሠጻቸው። [እናንተ ከምን ዐይነት መንፈስ እንደ ሆናችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የመጣው የሰውን ሕይወት ለማዳን ነው እንጂ፥ ለማጥፋት አይደለም።] 56ከዚያም ተነሥተው ወደ ሌላ መንደር ሄዱ።
የኢየሱስ ተከታዮች የሚገጥማቸው ችግር
(ማቴ. 8፥19-22)
57ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጒዞ ቀጥለው በመንገድ ላይ ሳሉ አንድ ሰው ኢየሱስን “እኔ ወደምትሄድበት ሁሉ ልከተልህ እፈልጋለሁ፤” አለው።
58ኢየሱስም “ቀበሮዎች ጒድጓድ አላቸው፤ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ አስጠግቶ የሚያሳርፍበት ስፍራ የለውም፤” ሲል መለሰለት።
59ሌላውንም ሰው “ተከተለኝ!” አለው። ሰውየው ግን “ጌታ ሆይ! መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፤” አለው።
60ኢየሱስም “ሙታንን ተዋቸው፤ ሙታኖቻቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ግን ሂድና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተምር!” ሲል መለሰለት።
61አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “ጌታ ሆይ፥ እኔ ልከተልህ እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ሄጄ ቤተሰቤን እንድሰናበት ፍቀድልኝ፤” አለው። #1ነገ. 19፥20።
62ኢየሱስም “ለማረስ በእጁ ዕርፍ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም፤” ሲል መለሰለት።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997