ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ወደ ራሱ ጠርቶ አጋንንትን ሁሉ እንዲያወጡ፣ ደዌንም እንዲፈውሱ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ለመንገዳችሁ በትር፣ ከረጢት፣ እንጀራ፣ ገንዘብ፣ ወይም ትርፍ እጀ ጠባብ መያዝ አትያዙ። ከዚያ ከተማ እስከምትወጡ ድረስ መጀመሪያ በገባችሁበት በማንኛውም ቤት ቈዩ። የከተማው ሰዎች ሳይቀበሏችሁ ቀርተው ከተማቸውን ለቅቃችሁ ስትሄዱ፣ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።” እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም፣ በዚህ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ ሰምቶ በሁኔታው ተደናገረ፤ ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ዮሐንስ ከሙታን እንደ ተነሣ ያወሩ ነበር፤ ሌሎች ኤልያስ እንደ ተገለጠ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሙታን እንደ ተነሣ ይናገሩ ነበር። ሄሮድስም፣ “መጥምቁ ዮሐንስን እኔው ራሴ ዐንገቱን አስቈርጬው ሞቷል፤ ታዲያ፣ ስለ እርሱ እንዲህ ሲወራ የምሰማው ይህ ሰው ማነው?” አለ፤ በዐይኑም ሊያየው ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው በመጡ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ይዟቸው ቤተ ሳይዳ ወደምትባል ከተማ በመሄድ ለብቻው ገለል አለ። ሕዝቡም ይህንኑ ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀብሏቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው። ቀኑም ሊመሽ ሲል፣ ዐሥራ ሁለቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ያለነው በምድረ በዳ ስለ ሆነ፣ ሕዝቡ ወደ አካባቢው መንደርና ገጠር ሄደው ማደሪያና ምግብ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው” አሉት። እርሱ ግን፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ሄደን ካልገዛን በቀር፣ እኛ ያለን ከዐምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ አይበልጥም” አሉት፤ ዐምስት ሺሕ ያህል ወንዶች በዚያ ነበሩና። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሕዝቡን በዐምሳ፣ በዐምሳ ሰው መድባችሁ አስቀምጧቸው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በታዘዙት መሠረት ሰዎቹ እንዲቀመጡ አደረጉ። እርሱም ዐምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ባረካቸው፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከእነርሱ የተረፈውን ቍርስራሽ እንጀራ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ይጸልይ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ከርሱ ጋራ ነበሩ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞ ነቢያት አንዱ ከሙታን ተነሥቷል ይላሉ” አሉት። እርሱም፣ “እናንተስ ማን ነው ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ክርስቶስ ነህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት ዘንድ መናቅ፣ መገደልና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መነሣት አለበት” አላቸው። ከዚያም ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው? ማንም በእኔና በቃሌ ቢያፍር፣ የሰው ልጅ በግርማው እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ግርማ ሲመጣ ያፍርበታል። “እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳያዩ ሞትን የማይቀምሱ ሰዎች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ። በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እጅግ የሚያንጸባርቅ ሆነ። እነሆም፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋራ ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር። ጴጥሮስና ዐብረውት የነበሩት ግን እንቅልፍ ተጭኗቸው ነበር፤ ሲነቁ ግን ክብሩንና ከርሱ ጋራ የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ። ሰዎቹም ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናል” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር። ይህንም እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፣ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ነገሩን በልባቸው ያዙ እንጂ ስላዩት ነገር በዚያ ወቅት ለማንም አልተናገሩም።
ሉቃስ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 9
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 9:1-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos